የቪዲዮ ስብሰባዎችን ከጥቃት የሚከላከል ‹ደቦ› የተሰኘ መተግበሪያ ይፋ ተደረገ

0
697

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ አዲስ እና በዓይነቱ ልዩ የሆነ የቪዲዮ ስብሰባዎችን ከጥቃት የሚከላከል እና ስብሰባዎችንም ማካሄድ የሚያስችል ‹ደቦ› የተሰኘ መተግበሪያ ይፋ ማድረጉን አስታወቀ።

ደቦ መተግበሪያ የተዘጋጀው በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የምታደርጋቸውን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ውይይት እንዲሁም በተለያዩ ተቋማት የሚደረጉትን የቪዲዮ ስብሰባዎች ቀድመው ከአገር እንዳይወጡ እና እንዳይመዘበሩ የሚረዳ ሲሆን፣ የመቆጣጠሪያ ሰርቨሩንም የሚቆጣጠረው ኤጀንሲው እንደሆነ ተጠቅሷል።

የቪዲዮ ኮንፈረንስ መተግበሪያ የተዘጋጀበት ምክንያት ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ የወቅቱ የመንግሥት ትልልቅ ስብሰባዎች በቪዲዮ አማካኝነት እንዲከወኑ አስገዳጅ ስለሆነ ነው። ይህንንም ተከትሎ ዓለም ዐቀፍ የሳይበር ጥቃቶች እየተበራከቱ ስለመጡ በአገር ምስጢር ላይ የሚከሰተውን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል እና የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሲባል ሰዎች በቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ በሚደረግበት ጊዜ፣ በቀላሉ ከሳይበር ጥቃት ነፃ በሆነ መልኩ መሥራት ለማስቻል ታስቦ መሆኑን የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የሳይቨር ዴቨሎፕመንት ዳይሬክተር በኃይሉ አዱኛ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ እንደገለጹት ኢትዮጵያ እስከ አሁን ስትጠቀምበት የነበረው የቪዲዮ መገናኛ ዘዴ የመቆጣጠሪያ ሰርቨሩ በአገር ውስጥ ስላልነበር መተግበሪያውን የሚቆጣጠረው ከአገር ውጭ የሚገኝ ኩባንያ ስለነበር የአገር ምስጢር የተጠበቀ እንዳልነበር ተናግረዋል። ዳይሬክተሩ ምክንያቱን ሲያስረዱ የግንኙነት መስመሩ መተግበሪያውን ተጠቅመው ለሚገናኙት ሰዎች መረጃው የሚደርሰው በቅድሚያ በተቆጣጣሪዎቹ አልፎ መሆኑን አስረድተዋል።

በዚሁ ምክንያት የመረጃ ልውውጡን የሚቆጣጠሩ የሰርቨሩ ተቆጣጣሪ አገራት የአገራቶችን መረጃ ቀድመው በመጥለፍ ለተለያዩ የጥቃት ዓላማ እንደሚጠቀሙ ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ተሠርቶ አስተማማኝነቱ ተረጋግጦ ለመንግሥት ሚኒሰቴር መሥሪያ ቤቶች የዋለው የቪዲዮ ኮንፍረንስ መተግበሪያ ስርአቱ፣ የመቆጣጠሪያ ሰርቨሩ በአገር ውስጥ እንደሆነና በሌሎች አገሮች እንዳይጠለፍ ተደርጎ መሠራቱን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

እንዲሁም የመተግበሪያውን የመረጃ ደኅንነት በአገር ውስጥ ጠላፊዎች እንዳይጠለፍም የደኅንነት አጠባበቁ ስለሚደረገው የመረጃ ልውውጥ ከግንኙነቱ ዉጭ ለሆነ ሰው መረጃ እንዳያሳይ ተደርጎ ተሠርቷል ተብሏል። በተጨማሪም መተግበሪያው በአገር ውስጥ ቋንቋዎች እንዲሠራ ማድርግ እንደሚቻልም ተነግሯል።
‹ደቦ› በኢትዮጵያ ውስጥ እስከ አሁን አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ለሚሠሩ አካላት፣ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ለተለያዩ ብሔራዊ ኮሚቴዎች እና ለራሱ ለኤጀንሲው ከፍተኛ ኃላፊዎች መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

‹ደቦ› ማንኛውም ሰው ከወቅቱ አስገዳጅ ሁኔታ አንጻር በሥራ ቦታ ተገኝቶ ሥራን የማከናወን ችግር በ‹ደቦ› አማካኝነት እንዲሠሩና እንዲግባቡ እንዲሁም ሁሉም ሰው እንደ አንድ የመገናኛ ዘዴ እንዲጠቀመው ከኹለት ሳምንታት በኋላ እንደሚለቀቅ እና ክፍት እንደሚሆን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ኤጀንሲው ከላኪው እና ከተቀባዩ ውጭ ሦስተኛ ወገን የመረጃ ልውውጦችን መመልከት የሚከለክል የምስጢር ቴክኖሎጂን የተጠቀመ ‘ሲርኩኒ’ የሚባል መተግበሪያ አዘጋጅቶ የሙከራ ሥራ እየሠራ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

በኤጀንሲው ‹‹የኢትዮጵያ የተቀናጀ የኮቪድ19 መቆጣጠሪያ ስርዓት›› የተሰኘ ስለ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተለያዩ አገራዊና ዓለም ዐቀፋዊ መረጃዎችን የሚሰጥና የተለያየ እርዳታዎችን በገንዘብና በአይነት ለማስባሰብ የሚያገለግል ድረ ገጽ ይፋ አድርጎ ሥራ ላይ ማዋሉ ይታወሳል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን ባስጨነቀበት የአገሪቱ መሪዎችና የተለያዩ የመንግሥት እንዲሁም የግል ድርጅቶች አመራሮች የሚከውኗቸውን የስብሰባ እና የውይይት ሥራዎች በአካል ተገናኝተው እንዳይከውኑ ማድረጉን ተከትሎ፣ የግንኙነት ዘዴያቸውን በቪድዮ ኮንፈረንስ እያደረጉ ይገኛሉ። ጊዜው የሚጠይቀውን ሁኔታ ለማሟላትም የዓለም የቴክኖሎጂ ተቋማት አዳዲስ ሥራቸውን እያስተዋወቁ ወደ ሥራ እያስገቡ ይገኛሉ ሲሉ ኃላፊው አስታውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here