አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አገኘ

0
816

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ያቀረበውን የድጋፍ ጥሪ ተከትሎ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማግኘቱን አስታወቀ።
ሚያዚያ 22/2012 የተደረገውን ድጋፍ ጨምሮ 89 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በገንዘብ፣ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ደግሞ በዓይነት ድጋፍ መደረጉን የከተማ አስተዳደሩ የማኅበራዊ ትረስት ፈንድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ፍቅርተ ነጋሽ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከተለያዩ ባለሀብቶች 92 የሚደርሱ ሕንፃዎች፣ ሆቴሎችና መጋዘኖች የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል እንዲያገለግሉ በጊዜያዊነት መበርከቱን ፍቅርተ ጠቅሰዋል።
ጠቅላላ ድጋፉ ይፋ በሆነበት ወቅት ሰንሻይን ኮንስትራክሽን የ6 ሚሊዮን ብር የተለያዩ ምግብ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ቃለሕይወት ቤተክርስትያንን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ማድረጋቸውን ፍቅርተ አስታውቀዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ኢንጅነር እንዳወቅ አብቴ ድጋፉን ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ሌሎች አካላትም መሰል ድጋፎችን አጠናክረው እንድቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ድጋፍ ያደረጉት የሰንሻይን ኮንስትራክሽን ባለቤት ሳሙኤል ታፈሰ ተጨማሪ 10 ሚሊዮን ብር በደቡብ፣ ኦሮሚያና አማራ ክልል በቀጣዮቹ ቀናት ድጋፍ እንደሚያደርጉ የተናገሩ ሲሆን፣ የቃለሕይወት ቤተክርስትያንም መሰል ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የቤተክርስትያኑ ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here