ቪኢኮድ በአዲስ አበባ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ጀመረ

0
531

ቪዥን ኢትዮጵያን ኮንግረስ ፎር ዴሞክራሲ የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝን በተመለከተ ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተማዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴዎች መጀመሩን አስታወቀ።
ድርጅቱ ለዐስር ተከታታይ ቀናት ‹‹ፍም እሳት በመቆንጠጫ ይያዛል፤ አካላዊ ርቀትን አለመጠበቅ ግን ዋጋ ያስከፍላል›› በሚል መሪ ቃል የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች፣ አደባባዮች፣ የገበያ ሥፍራዎችና የትራንስፖርት መገልገያ ስፍራዎች ላይ በመኪና በመንቀሳቀስ በሙዚቃ የታጀቡ መልዕክቶች እንደሚያተላለፍ አዲስ ማለዳ ከአዘጋጆች ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
ቪኢኮድ ሚያዚያ 22/2012 ባወጣው መግለጫ እንደተናገረው፤ ከንብ ባንክ ጋር በጋራ በመሆን ያዘጋጁትን ግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴ በይፋ አስጀምሯል። በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከሰተውን ወረርሽኝ በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ የሚደረገውን ርብርብ ለማስፈጸም አስፈላጊውን ወጪ ለመሸፈን እና በመንግሥት የቀረበውን ጥሪ በመቀበል አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉ ተጠቅሷል።
ቪኢኮድ ላለፉት 17 ዓመታት ከሙስና እና ከብልሹ አሰራር የጸዳ ትውልድ ለመፍጠር በመልካም አስተዳደርና በሰላም ዙሪያ በመላው ኢትዮጵያ በመንቀሳቀስ ከ16 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ከሦስት እስከ ስድስት ወር የሚቆይ መደበኛ የአቅም ግንባታ ሥልጠና የሰጠ ድርጅት ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here