በድኅረ ኮሮና ሊያጋጥም የሚችለውን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ ችግኞች ሊከፋፈሉ ነው

0
400

የአዲስ አበባ ከተማ የከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥመውን የምግብ እጥረት ለመቋቋም 500 ሺሕ የምግብ ችግኞችን አዘጋጅቶ ለከተማው ነዋሪዎች በየቤታቸው እንዲያለሙ ለማድረግ ማዘጋጀቱን አስታወቀ። ለኅብረተሰቡ የሚከፋፈሉት ችግኞች በዋናነት የጓሮ አትክልቶች ሲሆኑ በአጭር ጊዜ አድገው ለምግብነት የሚውሉ እንደሆነም ተገልጿል።

ኮሚሽኑ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፤ በቀጣይ ኹለት ሳምንታት ውስጥ የመጀመሪያው ዙር ግማሽ ሚሊዮን ችግኝ የሚከፋፈል ሲሆን ከኅብረተሰቡ የሚገኘውን ምላሽ ታሳቢ በማድረግ በቀጣይ ዙር በሚደረገው የችግኝ ማከፋፈል ላይ መጠኑ እንደሚወሰንም ታውቋል።

ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት በዋናነት በኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት የተቀዛቀዘውን የምጣኔ ሀብትና አልምቶ እራስን የመመገብ ሥራ ፈተና ውስጥ መግባቱን ተከትሎ፣ ኅብረተሰቡ ሊያጋጥመው የሚችለውን የምግብ እጥረት ለመቋቋም የሚያስችል እና ከኮሮና ቫይረስ ኋላም የኅብረተሰቡ የገቢ ምንጭ ስለሚቀዛቀዝ ኅብረተሰቡ በተለይ የአትክልት ምርቶችን በቤቱ አምርቶ እንዲጠቀም ለማስቻል ትኩረቱን አድርጎ እየሠራ መሆኑን ገልጿል።

የከተማ ግብርና ኮሚሽነር ፈትያ መሐመድ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ኮሚሽኑ በ2012 በጀት ዓመት ከሰባት ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ እድል እንደፈጠረ እና በአትክልት ምርት፣ በንብ ማነብ፣ በከብት ማድለብና በተመሳሳይ የሥራ ዘርፎች አሰማርቶ ወጣቶቹ በማኅበር በመደራጀት እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በግብርና ዘርፍ ተመርቀው ሥራ ላይ ያልተሰማሩ የግብርና ባለሙያዎች በከተማ ግብርና ልማት ለመሳተፍ እንዲዘጋጁ ያቀረቡት ጥሪ በአዲስ አበባ በዐስሩም ክፍለ ከተሞች በተለያዩ ባዶ ቦታዎች ላይ በበጎ ፍቃደኝነት በሙያተኞች የታገዘ የግብርና ልማት እንዲያለሙ ለማድረግ መሆኑን ፈትያ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። ይህንም ተከትሎ ሚያዚያ 22/2012 ጀምሮ በከተማ ግብርና ላይ ለሚሰማሩ አንድ መቶ ሰዎች የመሬት ርክክብ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ለከተማ ግብርና ልማት ሥራ የሚያስፈልግ በጀት በየክፍለ ከተማው ተበጅቶ እየተሠራ እንደሆነ የገለጹት ፈትያ፣ በየክፍለ ከተማው የሚገኙ ክፍት ቦታዎችን በሙያተኞች የተደገፈ የግብርና ልማት በማልማት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ቢገታም እንኳን ያሳደረውና የሚያሳድረው የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ ስለሚኖር ኅብረተሰቡ ራሱን እንዲመግብ ለማስቻል ከወዲሁ መሥራት አስፈላጊ መሆኑንም አመላክተዋል።

በሌላ በኩል የግብርና ኮሚሽኑ የሥራ እድል የመፍጠር ተግባርና ኃላፊነት የለውም ያሉት ፈትያ፣ የፋይናንስ እና የባለሙያ ሥራ ተብለው የሚሠሩ ሥራዎችና ድጋፎች ባለመኖራቸው በዘርፉ ሰፊ ሥራ መሥራት እየተቻለ አለመሠራቱን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በከተማው የልማት ተነሽ ለሆኑ አርሶ አደሮች በ30 ማኅበራት ተደራጅተው ወደ ከተማ ግብርና ልማት መግባታቸውን ኮሞሽነሯ ጠቅሰዋል። አርሶ አደሮቹ ለማልማት የሚያስችላቸውን የፋይናንስ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ኮሚሽነሯ አክልው ተናግረዋል።

እንደ ኮሚሽነሯ ገለጻ ኮሚሽኑ በቫይረሱ ምክንያት የሚፈጠረውን የምግብ ፍላጎትና አቅርቦት እጥረት ለማመጣጠን እና ኅብረተሰቡ ሊከሰት የሚችለውን አደጋ በራሱ ልማት ለመቋቋም እንዲችል በትኩረት እየሠራ መሆኑን አንስተዋል።

አዲስ አበባ ከተማ በምግብ ራሷን እንድትችል የሚያደርግ እና የከተማ ግብርናን የሚያበረታታ አዲስ ስትራቴጂ እየተዘጋጀ መሆኑን የከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ማስታወቅን አዲስ ማለዳ መዘገቧ የሚታወስ ነው። ኮሚሽኑ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገረው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደርና የከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን በአዲስ አበባ የከተማ ግብርና ልማትን ለማጠናከር እንዲሁም በከተማዋ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት እቅድ አየተዘጋጀ መሆኑን ይፋ አድርጓል።

የከተማ ግብርና ሥራው ዕቅዱ ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ 50 ሺሕ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ፈቲያ ጠቁመዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here