ህገ-መንግስቱ ከደነገገው ስርአት ውጪ ያለምርጫ እና ህገ-መንግስታዊ እውቅና በሌለው ህገ-ወጥ ምርጫ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ እንቅስቃሴ ፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ
“በግልፅ መታወቅ ያለበት በኢትዮጵያ ያለው ለውጥ ሪፎርም እንጂ አቢዮት አይደለም፡፡ ህገ-መንግስት ቀይረን አዲስ ህገ-መንግስታዊ ስርአት እየገነባን አይደለም፡፡ ገዢው ፓርቲ ታድሶና የህዝብ ተቀባይነቱን ጨምሮ ገና ጀምበሩ እየወጣ ያለ አዲስ ጉልበትና አቅም ያለው በቀጣዩም ምርጫ እጅግ ሰፊ የማሸነፍ እድል ያለው እንጂ ተሰናባችና ጀንበሩ ያዘቀዘቀ ስብስብ አይደለም፡፡
ስለዚህ የሽግግር መንግስት የሚለው ሀሳብ ከህግ አንፃር ብቻ ሳይሆን አሁን ካለንበት ነባራዊ ሁኔታ በንድፈ ሀሳብም ሆነ ከሽግግር ተሞክሮ አንፃር ለኢትዮጵያ የሚሆንና የሚበጅ አይደለም፡፡ በተለይም የኮቪድ 19 ስጋት ባለበት እና የቀጠናችን ሁኔታ ለአገር ሉአላዊነት ስጋት በደቀነበት ወቅት የሽግግር መንግስት እንመሰርታለን ብሎ መቋጫ የሌለው ውይይት ይባል ድርድር መጀመር ሀላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ህገ-ወጥ ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነው፡፡
መገንባት የምንፈልገው ህገ-መንግስታዊ ዲሞክራሲ ነው፡፡ ይህም ማለት ህገ-መንግስታዊነት የሰፈነበት የህገመንግስት የበላይነት የሚከበርበት ስርአት ነው፡፡
ህገ-መንግስቱ ከደነገገው ስርአት ውጪ ያለምርጫም ህገ-መንግስታዊ እውቅና በሌለው ህገ-ወጥ ምርጫ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ እንቅስቃሴ ፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡
የኢ.ፌ.ድ.ሪ ህገ-መንግስት በአንቀፅ 50 የፌደራል መንግስትን ስልጣንና ተግባር ሲዘረዝር ቁጥር አንድ ብሎ ያስቀመጠው ህገ-መንግስቱን የመጠበቅና የመከላከል ሀላፊነት ነው፡፡ የህን ሀላፊነት ለመወጣት አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነን፡፡ ይህንን ማድረግ የማንደራደርበት ህገ-መንግስታዊ ግዴታችን ነው፡፡
በህገ-መንግስቱና በህገ-መንግስታዊ ስርአት ካልሆነ በስተቀር የጨረባ ምርጫ ለማድረግ መነሳት አገርን እና ህዝብን ለከፋ አደጋ የሚዳርግ በመሆኑ መንግስት የሀገርን እና የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ ሲል ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል፡፡”



