ረቡዕ ሚያዚያ 28/2012 በአዳማ ከተማ በተፈጸመው የዕውቁ ባለሀብት ከቢርሁሴን ዋቆ የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዲሪ መከላከያ ሚንስትር ለማ መገርሳ ንግግራቸው በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ኔትወርክ አየር ላይ እንዳይውል መደረጉ በሰራተኞች ዘንድ ቅሬታ አስነሳ፡፡
ረቡዕ እለት አዳማ ውስጥ በተፈጸመው የታዋቂው ባለሃብት ከቢርሁሴን ቀብር ላይ ለማ መገርሳ ተገኝተው አጭር ንግግር አድርገው ነበር።
በዚህም በርካታ ባለስልጣናትና ታዋቂ ሰዎች የተገኙበትን የቀብር ሥነ ሥርዓት ለመዘገብ ከተገኙት መገናኛ ብዙሃን መካከል አንዱ የነበረው ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን) በሥርዓተ ቀብሩ ላይ ለማ መገርሳ የተናገሩትን ድምጽ ከማስተላለፍ መቆጠቡ በድርጅቱ ጋዜጠኞች ዘንድ ጥያቄና ቅሬታን ፈጥሯል ሲል የቢቢሲ የአማርኛ ዜና ድህረ-ገፅ አስነብቧል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባም፤ የለማ መገርሳን ንግግርን የያዘው የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ዘገባ ረቡዕ ዕለት ምሳ ሰዓት ስድስት እና ሰባት ሰዓት ላይ እንደሚሰራጭ በዕለቱ የጣቢያው መርሃ ግብር ላይ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፤ ዜናው ወደ ምሽት እንዲተላለፍ መወሰኑን የድርጅቱ ሠራተኞች መናገራቸውን ገልፆ ነገር ግን በዕለቱ ምሽት 12 እና 1 ሰዓት ዜናዎች ላይ ከዘገባው የለማ ድምጽ እንዲወጣ ተደርጎ፤ የክልሉ የፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ድምጽ በማካተት እንዲተላለፍ ተደርጓል ብሏል።
የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቱ ዳይሬክተር አሉ እንደተባለው ‘የለማ መገርሳ ድምጽ ከላይ በመጣ ትዕዛዝ እንዳይተላለፍ ተከልክሏል’ በሚል ምክንያት ድምጻቸው ከዘገባው ተቆርጦ እንዲወጣ መደረጉን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሠራተኞች ተናግረዋል።
ይህ የዳይሬክተሩ ውሳኔ ከድርጅቱ ጋዜጠኞች ጋር አለመግባባትን ፈጥሮ እንደነበርም ቢቢሲ ያናገራቸው የኦቢኤን ጋዜጠኞች አረጋግጠዋል።
ከድርጅቱ ነባር ጋዜጠኞች መካከል አንዱ፤ ከዚህ ቀደምም የተመረጡ ሰዎች ድምጽ እና ምስል አየር ላይ እንዳይውል ክልከላ ይደረጋል ሲል ይህ የመጀመሪያ ክስተት እንዳልሆነ ለቢቢሲ አስታውቋል።



