የሚኒ ባስ ታክሲ ተጠቃሚዎችን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን እንዲጠቀሙ የሚያስገድደው አዋጅ በዛሬው ቀን ሙሉ በሙሉ መተግበር እንደሚጀምር ተገለፀ

0
554

ከዛሬ አርብ ሚያዚያ 30/2012 ጀምሮ የሚኒ ባስ ታክሲ ተጠቃሚዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን ማድረግ እንደሚገደዱ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ እንዳስታወቀው በአዲስ አበባ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን የማያደርጉ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ላይ ከማስተማር እስክ ሕጋዊ እርምጃ የሚደርስ ቅጣትን እንደሚጥል አስጠንቅቋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ጭምብል እንዲጠቀሙ ይደረጋል ያሉት የቢሮ ኃላፊው ስጦታው አካለ፤ ይሁንና በቸልተኝነትም ይሁን በሌላ መልኩ ጭምብል ያላደረጉ ተሳፋሪዎች በመጀመሪያ ትምህርት ይሰጣቸዋል ሲሉም ለኢዜአ አስታውቀዋል፡፡

እንደ ኃላፊውም ገለጻ ተጠቃሚዎች ተሽከርካሪ ውስጥ ሲገቡ ብቻ ሳይሆን፤ ሰልፍ ላይም ሆነው ጭምብል እንዲያደርጉ ይገደዳሉ ይህንን በማያደርጉ ተጠቃሚዎች ላይ ግን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ መሠረት እንደሚዳኙና የትራንስፖርት አገልግሎትም ማግኘት እንደማይችሉ ኃላፊው አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚወጡ መመሪያዎችን በትክክል በመተግበር ጥንቃቄ ማድረግ ወሳኝነት እንዳለው ያሳሰቡት ኃላፊው “በከተማዋ የሚስተዋለው የኅብረተሰቡ ቸልተኝነት ከበሽታው ስርጭት ጋር የሚቃረን ሆኖ አግኝተነዋል” ስለሆነም መንግሥት የወረርሽኙን ስርጭት በመቆጣጠር አገርንና ሕዝብን ለማዳን የሚያደርገው ጥረት ጥቅሙ ለራስ መሆኑን ህብረተሰቡ መረዳት ይገባል ብለዋል።

የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ከዕሮብ ጀምሮ ተሳፋሪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን በአስገዳጅ ሁኔታ እንዲጠቀሙ ማድረግ መጀመሩም የሚታወስ ነው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here