የጦር መሣሪያ ያለው ማንኛውም ተቋም ወይም ግለሰብ በሚቀጥሉት ኹለት ዓመታት ውስጥ የማስመዝገብ ግዴታ እንዳለበት የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።
የጦር መሣሪያን የመያዝ፣ የመግዛትና የመሸጥ ሥርዓቱ በመንግሥት እውቅና ብቻ የሚያደርግ ዓዋጅ ሥራ ላይ ውሏል። በቀጣዮቹ ኹለት ዓመታት በመንግሥት ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት አዋጁን በማስተግበር የጦር መሣሪያ ያለው ግለሰብም ይሁን ተቋም ምዝገባውን የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
የጦር መሣሪያ የያዘና ያላስመዘገበ ሁሉ እንዲይዝ እንደማይፈቀድና ፈቃድ የሚሰጠው ተቋም ወይም ግለሰብ በአዋጁ መሠረት ሕጋዊ የሚያደርጉትን መስፈርት አሟልቶ መገኘት እንደሚጠበቅበት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጓ አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ እስከ አሁን ድረስ የጦር መሣሪያዎችን የመሸጥና የማዘዋወር ሕጋዊ እውቅና የተሰጠው አካል ባለመኖሩ ግዥና ዝውውሩ የሚካሄደው ሕግን ባልተከተለ መንገድ ነበር። ይሁን እንጂ የጦር መሣሪያውን የገዛው አካል የምዝገባ መስፈርቱን ካሟላና ወንጀል ያልተሠራበት መሆኑ ከተረጋገጠ አስመዝግቦ መያዝ ይፈቀድለት እንደነበርም ይታወቃል።
አሁን ተግባር ላይ የዋለው አዋጅ የቀደመውን አሠራር ሙሉ በሙሉ እንደሚያስቀርና የጦር መሣሪያን ሽያጭና ዝውውር የሚከታተል በመንግሥት እውቅና የሚሰጠው አካል እንደሚኖርም አዳነች አስረድተዋል።
በአዋጁ መሠረት ለጦር መሣሪያ የሚሰጠው ፈቃድ በየዓመቱ ይታደሳል፤ ባለ ፈቃዱም በየዓመቱ ክፍያ ይፈጽማል ተብሏል።
ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012



