የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የካዛ ግድብ የግንባታ ሥራን ከ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ለመገንባት ሚያዝያ 26 ቀን 2012 ከኢትዮጵያ መስኖ ልማት ኮሚሽን ጋር ተፈራረመ።
የካዛ ግድብ የግንባታ ሥራ ፕሮጀክት የዋና ግድብ ግንባታ፣ የውሃ ማስተንፈሻ፣ የውሃ መቆጣጠሪያ ማማ፣ ወደ ግድቡ የውሃ ማስገቢያ ቦይ እና የመስኖ ዋና ቦይ ግንባታን ያካትታል። ግንባታው 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በሆነ የኮንትራት ዋጋ በአራት ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የውል ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት ተገልጿል።
የውል ስምምነቱ የኢትዮጵያ መስኖ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሚካኤል መሃሪ (ዶ/ር) ኮሚሽኑን፣ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው ደግሞ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽንን በመወከል ተፈራርመዋል።
ኮሚሽነር ሚካኤል መሃሪ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የመስኖ ግድብ ሥራን ከጀመረች በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረችና በተለይ ባለፉት 10 ዓመታት ከፍተኛ የአገር ሀብት የፈሰሰባቸው ግድቦች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። አያይዘውም ከዘርፉ መንግሥትና ሕዝብ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ከመስኖ የሚገኘውን ተጠቃሚነት እንደ አዲስ ለማስጀመር ኮሚሽኑ መቋቋሙን ገልጸው፣ እስከ አሁን ከተቋቋመበት ጀምሮ ጊዜ ከ6 በላይ አዳዲስ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በማስገንባት ላይ ይገኛል ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ ያካበተውን ልምዱን ተጠቅሞ ፕሮጀክቱን በጥራት ሠርቶ በኮንትራት ውል ስምምነት የጊዜ ገደቡ እንደሚያስረክብም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል:: የካዛ ግድብ ግንባታ በትግራይ ክልል ጸለምት እና ወልቃይት ወረዳዎች ከዳንሻ ከተማ 2 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ማሂት ዳኛው በተባለ ቦታ 737 ሜትር ከፍታ ካለው ወንዝ ላይ የሚገነባ ግድብ ነው።
ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012



