በዘጠኝ ወራት ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ የመንግሥት ግዥ ተፈጽሟል

0
605

የኢፌዴሪ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በ2012 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወር ውስጥ ከ3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ግዥ መፈጸሙን አስታወቀ።
በ2012 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በግዥ አፈጻጸም ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች እና የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚጠቀሙባቸው የተመሳሳይ እቃዎች አምስት ሎቶችን (የኢንፎርሜሽን ቴክሎጂ እቃዎች፣ የጽሕፈት መሣሪያዎች፣ የጽዳት እቃዎች፣ የፈርኒቸር እቃዎች እና የፕሪንተርና ፎቶ ኮፒ ማሽን ቶነሮች ግዥ) አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ውል የመፈራረም ሥራ መሠራቱ የአገልግሎቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መልካሙ ደፋሊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የስትራቴጂክ ግዥዎች ስንዴ በብር አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር ውል ተፈርሞ ውሉን እንዲያስተዳድሩ ለብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መተላለፉን መልካሙ ጠቅሰዋል። ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የ6 ተሽከርካሪዎችን ግዥ በ9 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ውል በመፈጸም ተሽከርካሪዎቹ ገቢ ተደርገው ለተጠቃሚው መሥሪያ ቤት መተላለፋቸውን መልካሙ ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ በዘጠኝ ወሩ 3.1 ቢሊዮን ብር በላይ ከ27 አቅራቢ ድርጅቶች ጋር 54 ውሎች መፈረማቸውንና ግዥ መፈጸሙን መልካሙ አስረድተዋል። የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ያለባቸውን የተሽከርካሪ ችግር ለማቃለል 305 ተሽከርካሪዎችን ከኹለት አቅራቢዎች ጋር ውል በመዋዋል የተሽከርካሪዎቹ ዋጋ ብቻ በስምንት ሚሊዮን ዶላር ግዥ ተፈጽሞ ተሸከርካሪዎቹ ተጭነው ጅቡቲ ወደብ በመጓጓዝ ላይ መሆናቸውን መልካሙ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በ2012 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ለማከናወን ካቀዳቸው ሥራዎች መካከል 84 ነጥብ 3 በመቶ ያክሉን ማከናወኑንም መልካሙ ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል የገበያ ዋጋ ጥናትን በተመለከተ በሽያጭ የሚወገዱ የ16 መሥሪያ ቤቶች 68 የተለያዩ ሞዴል ተሸከርካሪዎች፣ በሽያጭ የሚወገዱ 33 መደብ ንብረቶች እንዲሁም ለአገልግሎቱ 135 ዓይነት የተሽከርካሪ ጥገና አገልግሎት ግዥ፣ ለሥራ አመቺ የሆኑ የ48 ጠረጴዛዎች ግዥ፣ 19 የተለያዩ የኔትወርክ አክሰሰሪዎች ግዥ፣ የስምንት ዓይነት ሞዴል አዲስ ተሽከርካሪዎች ግዥ እና 11 ልዩ ልዩ ዕቃዎች ወቅታዊ የገበያ ዋጋ ጥናት መደረጉ ተገልጿል።

በተጨማሪም በማዕቀፍ ስምምነት ግዥ ለፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች እና ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚገዙ የተለያዩ ዕቃዎች ላይ ለ11 አቅራቢዎች በ15 ዓይነት ዕቃዎች ላይ የዋጋ ማስተካከያ እንደተደረገ አዲስ ማለዳ ከአገልግሎቱ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከባለድርሻ አካላትና ከተገልጋዮች ጋር በተደረጉ ምክክሮች አገልግሎቱ በሚያከናወናቸው ሥራዎች ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር፣ በችግሮች ላይ ለመወያየትና መፍትሄ ለማስቀመጥ እንዲቻል 450 ከሚሆኑ ተጠቃሚ መሥሪያ ቤቶችና አቅራቢ ድርጅቶች ጋር በአገልግሎቱ ሥራዎች ላይ በቀጥታ ትስስርና ግንኙነት ካላቸው ባለድርሻ አካላት፣ ከፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችና የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች እንዲሁም ከተጫራቾች ጋር በማዕቀፍ ስምምነት ግዥ አፈጻጸም እና ግዥ ዝርዝር ውል በሚገባበት ጉዳይ እና በታዩ ችግሮች ዙሪያ፣ በተጨማሪም አገልግሎቱ ከፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶችና የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ የንብረት አስተዳደር ኃላፊዎች ጋር መድረኮችን በመፍጠር የምክክር መርሃ ግብሮች ተካሂደዋል።

በእነዚህ የባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ ተጠቃሚ መሥሪያ ቤቶችና አቅራቢዎችን በማገናኘት በችግሮችና መፍትሄዎች ዙሪያ ውይይት እንዲደረግ የተደረገ ሲሆን፣ የተገኙ ግብዓቶችን መነሻ በማድረግ የትግበራ ድርጊት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን አገልግሎቱ አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here