መንግሥት አባያ እርሻን ሙሉ በሙሉ ወደ ግሉ ዘርፍ ለማዞር ሙሉ ጨረታ ማውጣቱን የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
አንድ ሺሕ ሔክታር መሬት የሚሸፍነው እና በደቡብ ክልል ከወላይታ ሶዶ ከተማ 50 ኪሎሜትር ርቆ የሚገኘው አባያ እርሻ፣ በዋናነት ሙዝ የሚመረትበት መንግሥታዊ እርሻ እንደሆነ ኤጀንሲው አስታውቋል። የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወንድአፍራሽ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ በመንግሥት ስር የሚገኘው አባያ ጠቅላላ ስፋት አንድ ሺሕ ሔክታር ነው።
ሕዝብ ግንኙነቱ አያይዘው እንደጠቀሱት፣ ከዚህ አንድ ሺሕ ሔክታር መካከል 975 ሔክታር የሚሆነው የለማ ሲሆን፣ ከዛም በተጨማሪ ከአባያ እርሻ መካከል ከአንድ ሺሕ ሔክታሩ 25 ሔክታር የሚሆነው በግምንታ የተሸፈነ እና ቤቶችም ጭምር ያለው ነው። በተጨማሪም በአባያ እርሻ ዙሪያ መስኖ እንዳለና በመንግሥት ስር የነበረው አባያ እርሻ ሙዝ የሚለማበት እንደነበር ያስረዱት ወንዳፍራሽ፣ ከዚህ ቀደም ለጥቂት ጊዜያት ‹ሚድል አዋሽ› የተሰኘ ድርጅት በኪራይ ይዞት ሲያስተዳድረው እንደነበርም አስታውሰዋል።
በኪራይ ሲያስተዳድረው የነበረው ድርጅት ውሉን ባቋረጠበት ወቅትም የሚያስተዳድረው እንዳይታጣ በሚል ኤጀንሲው መልሶ እንደወሰደው እና በግብርና ኮርፖሬሽን እንዲቆይ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል። በመንግሥት ስር የነበረውን አባያ እርሻን ወደ ግል እንዲዞር ለማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት ምንድን ነው ለሚለው ወንድአፍራሽ ለአዲስ ማለደ ሲመልሱ ‹‹ያለው ፖሊሲ ሁኔታ ያስገድደናል፣ እርሻን ይዞ ለረጅም ጊዜ በመንግሥት ስር ማቆየት አይቻልም።›› በማለት ይናገራሉ።
ከዛም በተጨማሪ ወንድአፍራሽ እንደገለፁት አሁን ላይ በመንግሥት ስር ምንም ዓይነት የእርሻ መሬት የለም። አባያ እርሻም የቆየው ኪራይ ላይ ስለነበረ እንደሆነ አያይዘው ጠቅሰው፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ እና አስተዳደር ኤጀንሲ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የጨረታው ሰነድም መሸጥ የሚጀምረው ከሚያዚያ 30 ጀምሮ ሲሆን፣ የጨረታው ሰነድ መሸጫ ቀን የሚያልቀው ደግም ሰኔ 30 እንደሆና ሽያጩ ከኹለት ወር እንደሚልቅ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ እና አስተዳደር ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። ከዛም በተጨማሪ ለጨረታው የሚያስፈልገውን ሰነድ የአንዱ ዋጋ ሦስት መቶ ብር እንደሚሆንም ተገልጿል። በዚህም አሁን መንግሥት ባወጣው ጨረታ ላይ ለመሳተፍ የሚያስፈልገውን ሰነድ በኹለት ወር ውስጥ በመግዛት መሳተፍ እንደሚቻል በመጥቀስ፣ ሰነዱም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ እና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ቢሮ መግዛት የሚችሉ መሆኑን ኤጀንሲው አስታውቋል።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ በሚኒስትሮች ደንብ ቁጥር 445/2011 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የአባያ እርሻን በጨረታ ሽያጭ ወደ ግል ለማዛወር ያወጣው ግልጽ ጨረታ ከሚያዚያ 30/2012 ጀምሮ እስከ ሰኔ 30/2012 ክፍት እንደሚሆን ይጠበቃል።
ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012



