የኤሌክትሪክ ትራንዛክሽን ኢትዮጵያ ያለችበትን ደረጃ ያላማከለ ነው ተባለ

0
819

በቅርቡ ተግባራዊ ለማድረግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክክር እየተደረገበት የሚገኘው የኤሌክትሪክ የገንዘብ ዝውውር ወይም ‹ኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽ› ኢትዮጵያ ያለችበትን የመሠረተ ልማት ደረጃ ያማከለ እንዳልሆነ ተገለጸ።

በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበው የኤሌክትሪክ የገንዘብ ዝውውር ረቂቅ አዋጅ ከቋሚ ኮሚቴው ስለ ተፈጻሚነቱ ጥያቄ ቀርቦበታል። በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የመሰረት ልማት ማለትም የመብራት፣ የኅብረተሰቡ የቴክኖሎጂ እውቀት፣ ልምድና ግብዓት እጥረት አንጻር ተጽዕኖ አይኖረውም ወይ የሚል ጥያቄ ቀርቦበታል። ከዚህም በተጨማሪ በቀረበው ረቂቅ ላይ የግልጽነትና የትርጓሜ ክፍተት እንዳለው ተገልጿል።

ከቋሚ ኮሚቴው ለቀረበው ጥያቄም የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አብረሐም በላይ (ዶ/ር) ምላሽ ሲሰጡ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከደረሰችበት የመሠረተ ልማት አንጻር አዋጁ ተፈጻሚነት ላይ እንደሚውል እና በዚህም እምነት አላቸው። ነገር ግን ‹‹ሥራ የሚጀመረው ሁሉም ሲሟላ ሳይሆን እየተሠራ ማሟላት የተሻለ ነው።›› ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

የኤሌክትሮኒክ ትራንዛክሽን ተንቀሳቃሽ ስልክንና መሰል መሣሪያዎችን ጨምሮ በኮምፕዩተር በመታገዝ የኢንፎርሜሽን መረብ ሥራን ማከናወን የሚያስችል እንዲሁም የኤሌክትሮኒክ ንግድንና የመንግሥት አገልግሎቶችን የሚጨምር ቴክኖሎጂ መሆኑን የጠቆሙት አብርሃም፣ አሁን የደረስንበት የቴክኖሎጅ መሠረተ-ልማት ደረጃ የተሟላ ነው ባይባልም ባለን አቅም ጀምረን እያጠናከርን መሄድ ይጠበቅብናል ብለዋል።

የረቂቅ አዋጁን ዓላማ አስመልክተውም ሚኒስትሩ ሲያስረዱ፣ ወረቀትንና ኮምፕዩተርን ማእከል ያደረጉ ሰነዶችንና መረጃዎችን የሚጠቀሙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በእኩል ለማስተናግድ፣ ኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክ ንግድን ጥቅም ላይ እንድታውልና ዜጎች በኢኮኖሚው ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ የዲጂታል ዘመኑን እንድትቀላቀል ለማስቻልና ኹሉን ዐቀፍ መንግሥታዊ ተቋማትን በመገንባት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚያስችል ሕግ በማስፈለጉ ነው ብለዋል።

ሚያዚያ 28/2012 በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ውይይት በሚደረግበት ወቅት ቋሚ ኮሚቴው በረቂቁ ላይ የቀረቡ ዝርዝር ጉዳዮች ለኹሉም የኅብረተሰብ ክፍል ግልጽ ያልሆኑ የቃላት ትርጓሜ ችግር እንዳለበት ተመልክቷል። እንዲሁም በአንዳንድ አንቀጾች ላይ ‹ሌሎች ሁኔታዎች› ተብለው በግልጽና በዝርዝር ያልተቀመጡ አንቀጾች በብዛት በመኖራቸው ለአዋጁ ተግባራዊነትና ለፈጻሚ አካላት የግልጽነት ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል ታውቋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እምየ ቢተው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ በስፋት የቃላት ትርጓሜ አሻሚነትና በዝርዝር መጠቀሰ ያለባቸው አንቀጾች በግልጽ አልተቀመጡም። ለቋሚ ኮሚቴው በግልጽ ያልገባው አዋጅ ለፈጻሚው ሕዝብ ከዚህ በላይ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል።

ሰብሳቢዋ አክለውም በውይይቱ ላይ በዝርዝር የቀረቡ ክፍተቶችን ማለትም የግልጽነት ችግር ኖሮባችው የታዩ ዳግመኛ በግልጽ ማብራሪያ ተስተካክለው እንዲቀርቡ፣ በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት በእንግሊዘኛ የቴክኖሎጂ ቋንቋ የተቀመጡ ቃላቶች አቻና ለሕዝብ ግልጽ በሆነ አማርኛ ቃላት መስተካከል እንዳለባቸው እንዲሁም በዝርዝር መቀመጥ ሲኖርባቸው ‹ሌሎች ሁኔታዎች› በሚል የተጠቀሱ አንቀጾች ሌሎች ሁኔታዎች ምንድን ናቸው የሚለውን መልስ መልሰውና በዝርዝር ሊቀመጡ እንደሚገባ አሳስበዋል። ሰብሳቢዋ አክለውም ይህ ካልሆነ አዋጁ ከጸደቀ በኋላ ክፍተቶች አንዳይከሰቱ ከወዲሁ ጊዜ ወስዶ በግልጽ እንዲሻሻል አሳስበዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ ግብዓቶችን እና የማስተካከያ ጥያቄዎችን ማብራሪያ ለሚፈልጉት ማብራሪያ እንዲሁም ትርጉም ለሚፈልጉት የትርጉም ማሻሻያ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ በአጭር ጊዜ እንደሚያቀርብ ገልጸዋል።

‹‹በኤሌክትሪክ ትራንዛክሽን›› በሚል ርዕስ የተቀመጠው ረቂቅ አዋጁ፣ የአርዕስተ ቃሉ የቴክኖሎጂና የእንግሊዘኛ የሙያ ቋንቋ በመሆኑ አቻ በሆነ የአማርኛ ቃል መስተካከል እንዳለበት ግብዐት ተሰጥቷል።

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ ረቀቅ አዋጁን አስመልክቶ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች የተሰጠው ማብራሪያ ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ፣ ከግልጽነትና ከቋንቋ አጠቃቀም እንዲሁም በዝርዝር መቀመጥ ስላለባቸው ጉዳዮች ላይ ያሉትን ነገሮች በድጋሚ በመፈተሽ የተስተካከለው ሰነድ አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲደርሰውና በምክር ቤቱ ጸድቆ ወደ ተግባር እንዲገባ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል በማለት አሳስቧል።

ይህ ረቂቅ አዋጅ ምክር ቤቱ ሚያዚያ 22 ቀን 2012 ባካሄደው 15ኛ መደበኛ ስብሰባው ለሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መመራቱ ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here