የታላቁ የህዳሴ ግድብ ውሃ የሚያርፍበትን ቦታ ለመመንጠር ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ከ25 ሺሕ በላይ ወጣቶች ተደራጅተው ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለክልሉ ባስተላለፈው መልዕክት የህዳሴ ግድቡ ውሃ የሚያርፍበትን አንድ ሺሕ ሄክታር ስፋት ያለው ቦታ የክልሉ መንግሥት በክልሉ የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶችን አደራጅቶ የደን ምንጠራው እንዲያከናውን ኃላፊነት እንደተሰጠው የክልሉ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር መለስ በየነ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ የደን ምንጠራ ሥራውን የክልሉ መንግሥት በ33 ሚሊዮን ብር ወጭ እንዲያሠራ እና በ45 ቀን ውስጥ አጠናቆ እንዲያስረክብ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አቅጣጫ አስቀምጧል።
የደን ምንጠራው በ33 ሚሊዮን ብር በጀት ይጠናቀቃል ተብሎ በጀት ቢያዝለትም፣ የክልሉ መንግሥት ሥራውን ለማከናወን ከኤሌክትሪክ ኃይል የተበጀተው ገንዘብ በቂ አይደለም በማለት ማሻሻያ እንዲደረግበት ክልሉ በደብዳቤ መጠየቁን ዳይሬክተሩ አንስተዋል። ከበጀት ማሻሻያው በተጨማሪ ምንጠራውን ለማጠናቀቅ የተሰጠው ጊዜ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ሲታይ በቂ ባለመሆኑ ወደ ኹለት ወራት ከፍ ብሎ እንዲሻሻል መጠየቁንም መለስ አክለው ገልጸዋል።
በደን ምንጠራው ላይ የሚሳተፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከዩኒቨርሰቲ ተመርቀው ሥራ ያልያዙ ወጣቶች ሲሆኑ፣ የተሳታፊዎች ቁጥር እንደሚጨምር ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። በምንጠራው ላይ የሥራ እድል የሚፈጠርላቸው ለአካባቢው ቅርበት ያላቸው ስድስት ወረዳዎች 60 በመቶ እድል የተሰጣቸው ሲሆን፣ ቀሪ 40 በመቶ የሚሆነው የሥራ ዕድል በክልል ለሚገኙ ወረዳዎች የተሰጠ መሆኑ ተገልጿል። ይህም የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፣ ዳይሬክተሩ።
የክልሉ መንግሥት ካቢኔ ሚያዚያ 23/2012 ባካሄደው አስቸኳይ ስብስባ፣ በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ የተደራጁ ወጣቶችን ወደ ሥራ በማስገባት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃው የሚርፍበትን አካባቢ በምንጣሮ ሥራ ላይ በመሳተፍ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ በሚሆኑበት ጉዳይ ላይ ውይይት አካሂዶ ውሳኔ ማሳለፉንም ነው መለስ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።
የክልሉ መንግሥት ካቤኔ በክልሉ የሚስተዋለውን የወጣቶች መሠረታዊ የሥራ አጥ ችግር ለመፍታት በሚያስችል እቅድና መነሻ ሐሳብ ላይ ጊዜ ወስዶ በሰፊው ከተወያየ በኋላ፣ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በፍጥነት አጠናቅቀው ወደ ሥራ እንዲገባ ውሳኔ ማሳለፉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌት በቀጣይ የክረምት ወራት ላይ እንደምትጀምር የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒሰቴር ማስታወቁ ይታወሳል። ግድቡ በመጪው ክረምት ወቅት ውሃ ሙሌቱ ካልተጀመረ የኃይል ማመንጫ ጊዜውን እንደሚያራዝመው የግድቡን ዘጠነኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በተደረገው የፓናል ውይይት ላይ ተገልጿል። በመሆኑም ውሃ ለመያዝ በትጋት እየተሠራ መሆኑም ተመላክቷል።
የታላቅ ሕዳሴ ግድብ በአሁኑ ወቅት የሲቪል ሥራው 86.6 በመቶ፣ የኤሌክትሪክና መካኒካል ሥራው 44 በመቶ እና የብረታ ብረት ሥራው 20 በመቶ፣ አጠቃላይ የግንባታው ሂደት 72.4 በመቶ መድረሱ ተገልጿል። ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር ተያይዞ ፕሮጀክቱ ችግር እንዳይገጥመው በትኩረት እየተሠራ መሆኑም ተጠቅሷል።
ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተከሰተበት የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ውስጥ ከግንባታ ግብዓቶች ከቻይና ዉሃን ግዛት ወደ አገር ቤት ማስገባት ባለመቻሉ የግንባታው ፍጥነት በጥቂቱ ተገትቶ እንደነበር አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም መዘገቧ የሚታወስ ነው።
ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012



