ግብጽ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ከላይኞቹ ተፋሰስ አገራት ሱዳን እና ኢትዮጵያ ጋር አቋርጣው የነበረውን ውይይት ለመቀጠል መስማማቷ ከወደ ካይሮ ተሰምቷል።
ኢትዮጵያ በመጭው ክረምት የህዳሴው ግድብ ውሀ መያዝ ይጀምራል ማለቷን ተከትሎ ግብጽ የኢትዮጵያን እቅድ ለማሰናከል የተለያዩ ተንኮሎችን ስታቀነባብር ቆይታለች።
ከተንኮሎቹ መካከልም ኢትዮጵያ የአባይ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን በውሀ ድርቅ ልታስመታ የናይል ወንዝን ልትዘጋ ነው በሚል ለአረብ አገራት እና ለዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ የተሳሳተ መረጃ ስትሰጥ ቆይታለች።
ላለፉት 8 ዓመታት ከኢትዮጵያ ጎን የነበረችው ሱዳንን በግድቡ ላይ ያላትን አቋም ለማስቀየር የተለያዩ ሴራዎችንም ከአሜሪካ እና ሌሎች አገራት ጋር በመሆን ጫና ስታደርግም ቆይታለች።
እንዲሁም ኢትዮጵያ ከግብጽ እና ሱዳን ጋር ሳትወያይ በቀጣይ ክረምት የህዳሴው ግድብ ውሀ መያዝ ልጀምር በማለቷ የተባበሩት መንግሥታት የጽጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያን ከዚህ ድርጊቷ ያስቁምልኝ ስትልም ከስሳ ነበር።
ኢትዮጵያም በኒውዮርክ በሚገኘው አምባሳደሯ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በወንዜ ላይ ከእኔ ውጭ ማንም የመወሰን ሥልጣን የለውም ስትል ምላሽ መስጠቷ ይታወሳል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝም ግብጽ በዚህ ጉዳይ ላይ ከአራት ዓመት በፊት ማለትም እንደ ጎርጎሮሲያውያን ዘመን አቆጣጠር በ2015 በካርቱም በፈረሙት ስምምነት መሰረት ዳግም ወደ ውይይት ብትመለስ ሲል ምክረ ሐሳቡን ሰንዝሯል።
በመጨረሻም አማራጭ ያጣችው ግብጽ ከኢትዮጵያ እና ሱዳን ጋር ወደ ውይይት ለመመለስ መስማማቷን የግብጽ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012



