የኢትዮጵያ ኮምዩኒኬሽን ባለሥልጣን ኹለት ፈቃዶችንም ለመስጠት የፍላጎት መግለጫ መጠየቂያ አውጥቷል። ባለሥልጣኑ የፍቃድ አሰጣጥ ሂደቱን በኮምዩኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት አየመራ ሲሆን፣ ይህም የኢትዮጵያን የቴሌኮምዩኒኬሽን ዘርፍ የመክፈት ሂደት ዋናው አካል መሆኑን ተገለፀ።
ኢቲዮ ቴሌኮም ይዞ ከሚገኘው ፈቃድ በተጨማሪ ኹለት ፈቃዶችን በቴሌኮምዩኒኬሽን ሥራ ላይ ለተሰማሩ ኩባንያዎች የመስጠት ሂደት መንግሥት በዘርፉ ውድድርን ለመፍጠር ካቀዳቸው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዎች አንዱ መሆኑንም ጠቅሷል።
በዚህም የመንግሥት ዋና ዋና ዓላማዎች የቴሌ ኮምዩኒኬሽን አገልግሎቶችን ተደራሽና ቀልጣፋ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ማረጋገጥ እና የኢኮኖሚውን ለውጥ ለማፋጠን የሚያስፈልገውን የአገልግሎት ጥራትና ውጤታማነት በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ እና ከዲጂታል ኢኮኖሚ የሚገኘውን ጥቅም የበለጠ ለማስፋት መሆኑንም ባለሥልጣኑ አስታውቋል።
በዚህም ኹለት አገር ዐቀፍ የቴሌ ኮምዩኒኬሽን አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችሉ ፈቃዶች መስፈርቶችን ለሚያሟሉ የቴሌኮምዩኒኬሽን ኩባንያዎች በኮምዩኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 1148/2011 መሠረት በውድድር ላይ በተመሰረት ግልፅ ጨረታ የሚሰጡ መሆኑን ገልፀዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012


