በቀጣይ ዓመት 600 ሺሕ ተማሪዎች የምገባ መርሀ ግብሩ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተባለ

0
908

በተያዘው ዓመት ለተማሪዎች የተደረገው ድጋፍ በቀጣዩ ዓመት በጥራትም በቁጥርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ገለጹ። በቀጣዩ 2013 የትምህርት ዘመን ለ600 ሺሕ ተማሪዎችን የምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ ይሆናሉም ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ አማካኝነት በቴሌቪዥን እየተሰጠ ባለው ‹ትምህርት በቤቴ› መርሃ ግብር በአጭር የጽሑፍ መልእክት ለተሳተፉና ጥሩ ውጤት ላመጡ ተማሪዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ሽልማቱን ያበረከቱት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት መደበኛ የመማር ማስተማሩ ሂደት ቢስተጓጎልም ቴክኖሎጂን በተከተለና ተማሪዎችንም ባሳተፈ መልኩ የመማር ማስተማሩ መቀጠል ተችሏል ብለዋል።
በተማሪዎች ላይ የሚደረገው ኢንቨስትመንት ትውልድ መገንባት እንደመሆኑ ከጥቅሙ አንፃር ወጪው አነስተኛ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት የሚሰጠው ትኩረትም በተጠናከረ መንገድ የሚቀጥል መሆኑን ምክትል ከንቲባው አመልክተዋል።
በተያዘው ዓመት የተጀመረው ለ300 ሺሕ ተማሪዎች እየተደረገ ባለው የምገባ መርሃ ግብርም ቀጥሎ በቀጣዩ ዓመት 600 ሺሕ ተማሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ተናግረዋል። በዚህ ዓመት ለተማሪዎች የተደረገው የዩኒፎርም፣ የደብተር፣ መማሪያ ቁሳቁስና የምገባ መርሃ ግብር በቀጣዩ የትምህርት ዘመን በጥራትም በቁጥርም ጨምሮ እንደሚቀጥል ታከለ ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ እና በአፍሪ ሄልዝ ቴሌቪዥን በትብብር እየተሰራጨ ያለው ‹ትምህርት በቤቴ› መርሃግብር ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ ቀኑ 9:30 በመተላለፍ ላይ ሲሆን፣ ተማሪዎችም 8455 የአጭር የጽሑፍ መልእክት በመላክ መሳተፍ ይችላሉ ተብሏል።
ግንቦት 14/2012 ውድድር አሸናፊ ለሆኑ 41 ተማሪዎች የላፕቶፕ ስጦታ የተበረከተ ሲሆን፣ ልጆቻቸውን በጥንካሬ ለደገፉ ወላጆችም የቴሌቪዥን ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here