113 ቢሊዮን ጥሬ ብር ከባንክ ውጭ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር አስታወቀ

0
472

የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ከባንኮች በሚወጣ ገንዘብ ላይ ገደብ እንዲጣል ለዓመታት ሲያቀርብ የነበረው ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱ ሥራውን እንደሚያቀላጥፍለት ገልጿል። 113 ቢሊዮን ጥሬ ብር ከባንክ ውጭ እንደሚገኝም ማኅበሩ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ዋና ሥራ አስፈጻሚና የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ አቤ ሳኖ ግንቦት 13/2012 ከቦርድ አመራሮችና አባላት ጋር በመሆን በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ ማኅበሩ ከባንኮች የሚወጣው ጥሬ ገንዘብ ጣሪያ እንዲገድብ በተደጋጋሚ ሲያቀርብ የነበረው ጥያቄ ምላሽ ማግኘቱ የባንኮችን ሥራ እንደሚያቀላጥፈው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ ግንቦት 11/2012 በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ በሁሉም የንግድ ባንኮች በቀን የሚወጣው የጥሬ ገንዘብ መጠን ለግለሰብ 200 ሺሕ፣ ለኩባንያ ደግሞ 300 ሺሕ እንዲሆን መደረጉን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አንድ ግለሰብ አንድ ሚሊዮን፣ ለኩባንያ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድረስ ብቻ ማውጣት እንደሚችል ተገልጿል።
መመሪያው በሁሉም ባንኮች እና የፋይናንስ ተቋማት ተግባራዊ እንደሚደረግ የተገለጸ ሲሆን፣ ነገር ግን በልዩ ሁኔታ የሚታዩ አንዳንድ አግባቦችም ሊኖሩ እንደሚችሉ ታውቋል።
መመሪያው በቼክ፣ በሲፒኦ እና ሌሎች መንገዶች የሚካሄድ የገንዘብ ልውውጥ ላይ ገደብ አለመጣሉ ታውቋል።
በአዲሱ መመሪያ መሰረትም ባንኮች በየሳምንቱ ለብሔራዊ ባንክ ሪፖርትን የሚያቀርቡ ሲሆን፤ ከገደቡ በላይ የፈቀደ እና የሰጠ ባንክም የሰጠውን መጠን 25 በመቶ ወይንም አንድ አራተኛውን እንደሚቀጣም ተመላክቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here