በአስቸጋሪ ወቅቶች ከሥራ ኃላፊዎች የሚጠበቁ የአመራር ስብዕናዎች

0
838

በኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ምክንያት የንግድ ተቋማትና ገንዘብ አንቀሳቃሽ ትልልቅ ድርጅቶች በራቸው ከተዘጋ ከራርሟል። በርን ዘጋግቶ ሕይወትን መቀጠል ግን ከጥቂት ወራት በዘለለ እንደማያስሄድ ሆኗል። እናም ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ወደ ሥራው እንቅስቃሴ መግባት ግድ እንደሚል አመላካች ጉዳዮች ታይተዋል የሚሉት አብርሐም ፀሐዬ፣ አንዳንድ አገራትም የወረርሽኙን ስጋት ዋጥ አድርገው የባሰ እንዳይመጣ በሚል ከጥንቃቄ ጋር እንቅስቃሴ እየጀመሩ ይስተዋላል። ይህ ሲሆን ታድያ ከሥራ ኃላፊዎች የሚጠበቅ ድርሻ አከ ሲሉ እንዲህ አብራርተዋል።

የኮሮና ወረርኝ የዓለምን የፖለቲካና የምጣኔ ሀብት እያዛባ ነው። አገራት ፖሊሲያቸውን ለመከለስ ተገደዋል፤ ተቋማት ባልጠበቁት መንገድ ውለዋል፤ ሥራቸው ባልፈለጉት አቅጣጫ እየሄደ ተቸግረዋል። ተደላድለው ለዓመታት ተቀምጠው የነበሩት ትላልቅ የቢዝነስ ድርጅቶች ተንገዳግደዋል። የተዘጉም ከቁጥር በላይ ናቸው።
በምጣኔ ሀብት ፊታውራሪ የሆነችው አሜሪካ ነዳጇን ውሰዱልኝ እያለች ለማጓጓዣ ጭምር ራሷ እየከፈለች ከዜሮ በታች በሆነ ዋጋ እየሸጠች ነው። ሳዑዲ አረቢያ የተጨማሪ እሴት ታክሷን አምስት በመቶ ያደረገችው በቅርቡ እንደነበር ይታወቃል። አሁን ላይ ግን ንጉሥ መሐመድ ቢን ሰልማን ወደ አስራ አምስት በመቶ ለማሳደግ መገደዳቸውን አሳውቀዋል። ለዜጎቿ የምትደጉመውንም እስከማንሳት ድረስ በመሄድ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ገብተዋል።

በአፍሪካ ግዙፉ የአየር ላይ መጓጓዣ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው። ይህ የአገራችን የማንነት ምልክት ጭምር የሆነው ድርጅት እስከመጪው ሰኔ ድረስ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እከስራለሁ በማለት አስታውቋል። ምክንያቱ ደግሞ ከመንገደኞች ያገኝ የነበረው ክፍያ በመቅረቱ ነው። የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ እንደገለጹት፣ መንግሥት ለአየር መንገዱ ድጋፍ እንደሚያደርግለትና እንዲሁም እንደ ዓለም ባንክ ያሉት የገንዘብ ተቋማት ጭምር እንደሚረዱ ገልጸዋል። አገር ያቀኑ የነበሩ ተቋማት ሌሎች እንዲያቀኗቸው እየለመኑ ነው።

ኮሮና ጣጣው ዘርፈ ብዙ ሆኗል። በርካታ ድርጅቶች አደጋ ውስጥ እንደሆኑ እየተናገሩ ነው። ሰዎች በሥራ እጥነት ኑሯቸው በህልውና ጥያቄ ውስጥ ስለመግባቱ መስማት የየዕለት ዜና ከሆነ ሰነበተ። እየሠሩ ያሉትም ቢሆኑ ከተፈለገው በታች በሆነ የሥራ አቅምና ክፍያ ውሎ መመለሱን ተላምደውታል። በዚያ ላይ ከሥራ ጸባያቸው የተነሳ የቫይረሱ አጋላጭነት ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል።

ባለፈው ሳምንት በዚሁ በአፍሪካችን የጋናው ፕሬዝደንት እንዳሳወቁት በአንድ የዐሳ ማቀነባበራያ ፋብሪካ ውስጥ በአንድ ሰው ምክንያት ብቻ 533 ሠራተኞች በቫይረሱ ተይዘዋል። አሃዙ በቀን ውስጥ በአገሪቷ ከተመረመሩት መካከል ሠላሳ በመቶ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የሚያመለክት ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበ ነው።

ይህ አስደንጋጭ ቁጥር የሥራ ቦታዎችን ከአደጋው የመከላከል ሥራ ገና እንደሆነ ማሳያ ነው። የሥራ አካባቢ ጥንቃቄዎች ተግባራዊነታቸው እምብዛም ነው። ይህን የመሰሉ ጉድለቶች በዓለም ዙሪያ እየተሰሙም እየተለመዱም መጥተዋል። የየዘርፉ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ከወቅታዊ ፈተናው ጋር በተያያዘ በጥናትና ምርምር ተጠምደዋል።

የዓለም ምጣኔ ሀብት ወደ አዘቅት እንዳይወስደን ስንል ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ወደ ሥራው እንቅስቃሴ መግባት እንዳለብን አመላካች ነገሮች እየተስተዋሉ ነው። ቤት በመቀመጥ ብቻ ሕይወትን ማስቀጠል ይከብዳልና። በተለይ አፍሪካ ከኮሮና በኋላ በረሃብ ትናጣለች እያለ ነው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት።
ነገሩ ለአፍሪካም ሆነ ለሌላው ዓለም እንደቀደመ አቅማቸው በተዋረድ ከተጽእኖው አያመልጡምና የየአገራቱ መሪዎች የተዘጉ ተቋማትን ሥራ የማስጀመር ውሳኔ ውስጥ እየገቡ ነው። አገራችንም ከዓለም የተለየ ነገር ይኖራታል ማለት አይቻልም። ድርጅቶች እስከመቼ ይዘጋሉ? ከጥንቃቄ ጋር መሥራት እንደአማራጭ የሚወሰድ መፍትሄም ነው። ከበሽታው በላይ ረሃብ አለ፤ ከቫይረሱ በባሰ ቀውስንም መፍራት ብልህነት ነው።

ከስጋት ጋር ተያይዞ ከሥራ መሪዎች የሚጠበቅ አመራር
በእርግጥ እስካሁን ድረስ ወደአፍሪካና ኢትዮጵያችን በከፋ ሁኔታ ቫይረሱ ለጥቃት ባያጋልጠንም የወደፊቱ ስጋት ግን እንዳለ በመሆኑ የተጠቁትን አገራት ተሞክሮና የጥናት ውጤት መውሰድ ይመከራል።

በሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ የቢዝነስ አስተዳደር ፕሮፌሰር ጆን ኤ. ኩዌልች የሥራ መሪዎች እንደ ኮሮና ያሉ አስቸጋሪ ወረርሽኞች በሚመጡበት ጊዜ፣ ከሠራተኞቻቸውና ሥራቸው ጋር በጥሩ የአመራር ስብዕና ሊያሳልፉ ይገባል በሚል ሰባት ጠቃሚ የጥናት ውጤቶችን እንደሚከተለው አቅርበዋል። (7 Leadership Principles for Managing in the Time of Coronavirus. By John A. Quelch)

እርጋታ
ቫይረሱ ሊያመጣ ከሚችለው ሥነ ልቦናዊ ጫና እና ማኅበራዊ አለመረጋጋት የተነሳ የሥራ መሪዎች ለሠራተኞቻቸው የሚያሳዩት የሰከነ ማንነት አዎንታዊ አስተዋጽኦ አለው። ከአቅራቢዎቻቸውም ይሁን ከገዢዎቻቸው ወይም ግንኙነት ማድረግ ካለባቸው አካላት ጋር የሚታይባቸው የአመራር ስብዕና በመረጋጋት የተሞላ ከሆነ አጋሮቻቸው በመልካም የሥራ መንፈስ ላይ እንዲገኙ አስተዋጽኦ ያደርጋል። ነገን እርግጠኛ መሆን በማይቻልበት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ፍቱን የሚባለው መድኃኒት የተረጋጋና የአጽናኝነት ገጽታን ይዞ መቅረብ ነው።

በራስ መቆም
የሥራ መሪዎች በተረጋጋ ማንነት ላይ መገኘታቸው እንዳለ ሆኖ ጸጥ እንዳለ ውሃ ባሉበት መቅረት አለመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ነገሮች ምንም ያህል ከባድ ቢሆኑም የችግሩ ተጽእኖ ብዙም ጎጂ እንዳልሆነ በሚያሳይ የአመራር ቁመና ላይ መገኘት ይመከራል። የሥራ መሪዎች ሥራዎችን በራስ መተማመን ሲከውኑ መታየት በሠራተኞችም ሆነ በሌሎች አጋሮች ትልቅ መተማመንን የሚያጎናጽፍ በመሆኑ፣ ሁሉም ባለድርሻዎች በሙሉ ልብ በየኃላፊነታቸው ላይ በትጋት ይሳተፋሉ፤ በአብሮነትና በእኔነት ስሜት ሆነው ውጤታማ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።

ተግባቦት
ዘመኑ የሰው ልጅ በከፋ ጭንቀት ውስጥ የሚገኝበት ነው። ይህ ሁኔታ ቅርበትን እንጂ ቁጣን ወይም የሻከረ ግንኙነትን አይፈልግም። ከሠራተኞችና ከሥራ አካባቢ መጥፋትም አሉታዊ ውጤት ይወልዳል። ስለሆነም የሥራ መሪዎች ቀደም ካለው የአመራር ልማዳቸው ለወጥ ባለ መልኩ የድርጅቱን ሠራተኞች እና ባለድርሻ አካላትን ቶሎ ቶሎ መገናኛት፤ መመሪያዎችንና ውሳኔዎችን ማሳለፍ መቻል በድርጅቱ የሥራ መንፈስ ላይ ትልቅ መነቃቃትን ይፈጥሩበታል።

በቅርብ የመወያየት፣ የማቀድና የመገምገም አተገባበሮችን በመዘርጋት ተግባቦትን መፍጠር አዋጭ ነው። እንደዚህ በመሳሰሉት ስልቶች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የግንኙነት መስመሮችን ዘርግቶ መሥራት ተስፋ ቢስ ስሜቶች በሠራተኛው መካከል እየተሰራጨ በሂደትም ከሚያስከትለው የምርታማነት ማነስ ችግርና የገንዘብ ኪሳራ የመውጫ መንገድ ሆኖ ያገለግላል።

ትብብር
እንደሥራ መሪ አቅጣጫ መስጠት ዋና ድርሻ ነው። መቼም ማንም እንደሚረዳው ለሁሉም ችግር መፍትሄ መስጠት አይቻልም። መሪ ግን ጥላ ነውና አሰባስቦ የመያዝ ስብዕና አለው። በዚህ የማሰባሰብና የማስተባበር መርህ ውስጥ ለችግሮች መፍትሄ ማምጣት መቻል የመሪዎች ትልቁ መለኪያ ነው።
ሠራተኞችን፣ ባለሙያዎችንና ባለድርሻዎችን አቅፎና አስተቃቅፎ ሁሉንም እንደየሥራውና ድርሻው ኃላፊነት በመስጠት አስቸጋሪውን ጊዜ በጋራ ማለፍ፣ ማንም ሰው ለችግሮች መፍትሄ መስጠት እንደሚችል በተግባር ማሳየት ይጠበቃል።

የአንድ ድርጅት ሠራተኞች ሊረዱ የሚገባው ተግዳሮቶችን የሚያልፉት በነሱ ኃይልና የሥራ ክሂል ጭምር መሆኑን ነው። በአጠቃላይ ትብብር ወይም አስተባብሮ በግልና በቡድን አቅም መጠን አስቸጋሪ ጊዜን ማሳለፍ መቻል፤ ለዚህም ቁርጠኛ መሆን የሥራ መሪዎች ኃላፊነት ነው።

ማኅበረሰባዊነት
በዘመናዊው የቢዝነስ ዓለም ውስጥ ኩባንያ፣ የትርፍ ስሌት እና ማኅበረሰብ የማይነጣጠሉ ሦስቱ የህልውና መዋቅሮች ናቸው። ማንኛውም ተቋም በማኅበረሰብ ውስጥ ያለ ነው። ከሰው ውጪ የሆነ ድርጅት የለም። የተቋማት ውስጣዊ አደረጃጀት ከውጫዊው ጋር የተሰናሰለ ነው። ይህ ወረርሽኝ ደግሞ በተለየ ሁኔታ ሰዎችን ከምንጊዜውም በላይ የሌላ እጅ እንዲያዩ እያደረጋቸው ይገኛል።

ሰዎች በአካባቢያቸው ያለው ተቋም አንድ ነገር እንዲያበረክት መፈለጋቸው የሚገመት ጉዳይ ነው። ስለሆነም ማንኛውም ድርጅት እንደሠራተኞቹ ሁሉ በአካባቢው ያሉትን አጎራባች የማኅበረሰብ ክፍሎች ማገዝ ይጠበቅበታል። በአስቸጋሪ ጊዜ አብሮ የመሆን የውዴታ ግዴታ ይኖርበታልና ይህንን ኃላፊነት ከማኅበረሰቡ ጋር ተደጋግፎ መወጣት ከአመራሮች ይጠበቃል። ማኅበራዊ ኃላፊነት በአንድ ተቋም ውስጥ ራሱን የቻለ የሥራው አካል በመሆኑ በአግባቡ በመተግበር አብሮነትን ማሳየት የብልህ መሪዎች ድርሻ ነው።

ርህራሄ
ሰዎች እንዲታዘንላቸው የሚሹ ተሰባሪ ፍጡሮችም ናቸው። አውሬነት እንዳለ ሁሉ ስስ ባህሪም የሰው አፈጣጣር ነው። የኮሮና ወረርሽኝ ብዙዎችን እየጎዳ ያለ እንደመሆኑ ማንኛውም በአመራር ላይ የተቀመጠ መሪ ዙሪያውን ሊቃኝ ይገባል። ሠራተኞችን መከታተል ተገቢ ነው። ምናልባት ከቤተሰቦቻቸው መካከል በዚህ ቫይረስ የተጎዱ ካሉ፣ ወገንና ዘመዶቻቸው በተያያዥ አደጋ ውስጥ ከሆኑ፤ በአጠቃላይ ከባድ የሥነ ልቦና ጫና ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞች ላይ ክትትልና ምክክር በማድረግ መደገፍ ይገባል።

እንዳሉበት ችግር መጠን አማራጮችን መስጠት ያስፈልጋል። በጭንቀት የተነሳ በቤታቸው ውስጥ ሆነው መሥራት ከፈለጉ፣ መንከባከብ ያለባቸው የቤተሰብ አካልም ካለ በአጠቃላይ የቸገራቸውን ነገር በመጠየቅ፣ በመመርመርና በመመካከር እንዲሁም የወዳጅነትና የርህራሄ ድጋፍ በማሳየት መርዳት ተገቢ ነው። ነገ አብሮ መቀጠል፤ አብሮ መሥራት፣ በጋራ ማደግና መፈላለግ የሚሉት ነገር አለ። ‹ድልድዩን ስንደርስ እንሻገረዋለን› የሚለው ይትበሃል ለዚህ አይሆንም፤ ይልቁኑ ከወዲሁ ማሰብና ማስተዋል ግድ ነው።

ገንዘብ
‹ብር የደም ስር› እንደሚባለውም ነው፣ እንዲህ ባለው የሰቆቃ ዘመን ደግሞ ብር ቁልፉና የዘመኑ ኃያል መሆኑን የሚገልጥበት ወቅት ነው። የአንድ ተቋም መላወሻው ገንዘብ ነው። ተቋሙ ህልውናዬ ብሎ የሚሳሳለት ይህ ገንዘብ ሠራተኞች፣ አቅራቢዎችና ሌሎች ደንበኞችም መተንፈሻቸው ከገንዘብ ጋር የተቆራኘ ነው።
እነዚህ ባለድርሻ አካላት ከተቋሙ ጋር ያላቸው ትስስር በመተማመን ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ይሻሉ። ለጊዜው ተስፋ በመስጠት ሳይሆን በአስተማማኝ ውል ለአጭርም ይሁን ለረጅም ጊዜ ለሠሩት ሥራ ገንዘብ እንደሚከፈላቸው ወይም ለሚሰጡት ጊዜና ጉልበት ገንዘብ እንደሚያገኙ ማረጋገጥ ይፈልጋሉ። የሥራ መሪዎችም ይህንን ጉዳይ በአግባቡ ሊያሰሉና ሊተገብሩ እንደሚገባቸው እሙን ነው። ቸር ያሰማን!
አብርሃም ፀሐዬ፡ የቢዝነስ አማካሪና ጋዜጠኛ ሲሆኑ በኢ-ሜይል አድራሻቸው [email protected] ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here