ያለ እድሜ ጋብቻ = አስገድዶ መድፈር

0
913

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ እስከ አሁን በመንግሥት በጎ ሥራዎች ታይተዋል። ወረርሽኙ በጤና ላይ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ሕይወት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በመረዳት፣ የተለያዩ የፖሊሲ እርምጃዎችንም ወስዷል። ይህ መልካም ሆኖ ሳለ አካሄዶቹ በከተማም ሆነ በገጠር የሚኖሩ ሴቶች ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ በመረዳት ይህንኑ ታሳቢ ያደረጉ እርምጃዎች ላይ በቂ ትኩረት መስጠት ላይ ግን አሁንም ይቀራል። ለዚህም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣው ያለ እድሜ ጋብቻ ማሳያ ነው።

ያለ እድሜ ጋብቻ አንድ በእድሜ ከ18 ዓመት በታች የሆነ ሰው እውቅና ባለው መልኩም ሆነ በድብቅ በእድሜ ከ18 ዓመት ከሚበልጥ ወይንም ከሚያንስ ሰው ጋር ጋብቻ ሲፈጽም የሚከሰት ነው። ይህንን ሕገወጥ ድርጊት ለማስቆም የሚደረገው ጥረት ካልጨመረ በቀጣዮቹ ዐስር ዓመታት ውስጥ በዓለም ላይ 150 ሚሊዮን ሴቶች እድሜያቸው 18 ከመሙላቱ በፊት ጋብቻ እንደሚፈጽሙ ዩኒሴፍ አስታውቋል።

ዩኒሴፍ ባወጣው ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ 40 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች እድሜያቸው 18 ሳይሞላ ይዳራሉ። እንዲሁም 14 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ 15 ዓመት ሳይሞላቸው ትዳር ይመሰርታሉ። አሁንም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ታስቦ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ምክንያት ሊከወኑ የነበሩ፣ 540 ያለ እድሜ ጋብቻዎች ባለፉት ኹለት ወራት በአማራ ክልል ብቻ መክነዋል።

በተጨማሪም የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው በክልሉ ያለእድሜ ጋብቻ የሚፈጸምባቸው ሴቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ገልጿል። በጉዳዩ ላይ ሌሎች ክልሎች ያሉት ነገር ባይኖርም፣ ሁኔታው ተመሳሳይ የሚሆንበት አጋጣሚ ሰፊ ነው።
ይህንን ለመከላከል ግን ምን አይነት አቅጣጫ እንደተቀመጠ ግልጽ አይደለም። በመሆኑም እስከዛሬ ያለእድሜ ጋብቻን ለማስቀረት የተደረጉት ጥረቶች ወደ ኋላ ይመለሱ ይሆን የሚል ስጋት አለ።

ከሁሉም የሚከፋው ደግሞ ያለእድሜ ጋብቻን መሰል በሴት ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል የባህል ሽፋን ስለሚሰጣቸው፣ ማኅበረሰቡ ድርጊቱን ከመኮነንና ከመከላከል ይልቅ ‹ትክክለኛ ድርጊት› አድርጎ መውሰዱ ነው። ከዚህ ቀደም ያለድሜ ጋብቻን ለመከላከል መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ በስርአተ ጾታ ላይ የሚሠሩ ተቋማት ሴቶችን ወደ ትምህርት ቤት መላክን እንደመፍትሄ ቆጥረው ሲሠሩበት የነበረ ቢሆንም፣ በወረርሽኙ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው መፍትሄው ውጤታማነቱ ቀንሷል። ሴት ተማሪዎች ያሉበትን ሁኔታ ለመከታተልም አስቸጋሪ ሆኗል።

በመሆኑም እንዲህ ያሉ በገጠሩ የአገራችን ከፍል የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የመከላከል እርምጃ ላይ ጠንከራ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። እንዲሁም ሌሎች ክልሎችም በዚህ ጉዳይ ላይ የዳሰሳ ጥናት አድርገው ሁኔታውን በአስቸኳይ ማሳወቅ አለባቸው። ኮሮናን ለመከላከል መወሰድ ስላለባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች በመገናኛ ብዙኀን በተደጋጋሚ እንደሚነገረው ሁሉ፣ ሴቶች ቤት በሚውሉበት ወቅት ያለእድሜ ጋብቻን ጨምሮ ለጾታዊ ጥቃቶች እንዳይዳረጉ ማኅበረሰቡን የሚያስተምር፣ ጥቃቱ ከተፈጸመ ደግሞ ጥቃት የደረሰባት ሴት ስለሁኔታው እንዴት ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ እንዳለባት የሚገልጹ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶች ቢዘጋጁ መልካም ነው።

ያለእድሜ ጋብቻን መከላከልም የሁሉም የተቀናጀ ሥራን ይጠይቃልና፣ ሁሉም የድርሻውን ኃላፊነት መወጣት አለበት። ሕጻናት ወደ ትዳር ሳይሆን ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ነው የሚገባቸው። ያለእድሜ ጋብቻ አስገድዶ ከመድፈር ጋር የሚስተካከል ወንጀል ነው!
ኪያ አሊ

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here