ፆም የማያድሩ መሬቶች ትሩፋቶች እና መዘዞች

0
1000

መሬት የመንግሥት ሀብት ነው። ሀብቱን ለሕዝብ ጥቅምና አገልግሎት የሚያውል መንግሥት ታድያ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራባቸው ከሚገባ ጉዳዮች መካከል አንዱና ቀዳሚው የመሬት ጉዳይ እንዲሆን ይጠበቃል። በኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ ከመሬት ጋር በተገናኘ ትልልቅ አገራዊ ክስተቶች ተፈጥረዋል። ከ‹መሬት ለአራሹ› ጀምሮ ዛሬም ከሙስና እና ብልሹ አሠራር ጋር በተገናኘ የመሬት ጉዳይ ሳይነሳ ውሎ አያድርም።

በቅርቡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በምግብ ራስን ስለመቻል እንዲሁም ሊመጣ የሚችለውን ድኅረ ኮሮና (ኮቪድ 19 ወረርሽኝ) ፈተና ለመጋፈጥ፣ በየአካባቢው መሬት ባዶውን እንዳይሆንና እንዲዘራበት፣ እንዲተከልበት፣ ፆም እንዳያድር ሲሉ አሳስበዋል። ይህ በተባለ ማግስትም በተለያዩ ቦታዎች ሕገወጥ የመሬት ወረራዎች ከተኙበት እየባነኑ በአደባባይ ሲፈጸሙ ተስተውሏል። ይህንን ጉዳይ አዲስ ማለዳ የታዘበች ሲሆን፣ የአዲስ ማለዳው ኤርምያስ ሙሉጌታ አርሶ አደሮችንና የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት በማነጋገር፣ መዛግብትን በማገላበጥና ኹነቶችን በማውሳት፣ ያገኛቸውን መረጃዎች በማሰባሰብ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

ስፍራው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ክፍለ ከተማ ነው። ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ምክንያት የሆነው አጋጣሚ የተፈጠረውም በዚህ ቦታ ነው። ነገሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኩል በዘንድሮ የእርሻ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም አቅጣጫ ፆሙን የሚያድር መሬት እንደማይኖር መተላለፉን ተከትሎ አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውራ ያደረገችውን ምልከታ መሠረት ያደረገ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መልዕክት ከተሰማበት እና ወደ ትግበራም ከተገባ በኋላ አዲስ ማለዳ በተለያዩ አካባቢዎች ምልከታ አድርጋለች። በተጠቀሰው ስፍራ ከሰሚት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጀምሮ ወደ ቦሌ ለሚ ቁጥር አንድ እና ኹለት የሚወስዱ መንገዶች ግራ እና ቀኝ እርሻዎች እየተከናወኑ ተመለከትን። አካባቢው የግለሰቦች መኖሪያ እንደመሆኑ መጠን እና ከዚህ ቀደም በእርሻ ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦች የሚታዩበት ባለመሆኑ ቀልብን የሚስብ ስፍራ ሆኗል።

አዲስ ማለዳ በተጠቀሰው ስፍራ በመገኘት በእርሻ ላይ የሚገኙ አርሶ አደርን ለማነጋገር ችላለች። አርሶ አደር ጉታ በቀለ በአካባቢው ረጅም ጊዜ ጀምሮ ይኖሩ እንደነበርና ሲገኝ በቀን ሥራ፣ የእርሻ ወራት ሲደርስ ደግሞ አይሲቲ ፓርክ ተብሎ ወደ ሚጠራው አካባቢ በሚገኘው እርሻ መሬታቸው ላይ እርሻ እንደሚያከናውኑ ይናገራሉ። ጉታ በቅርቡ ግን በሚኖሩበት ወረዳ የሥራ ኃላፊዎች በመምጣት ጠፍ መሬት መሆኑን ገልጸው እንዲያርሱት እና ምርት እንዲያመርቱ ሰጥተዋቸው እንደሄዱ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከሥራ ኃላፊዎች የቀረበላቸውን በለስ ተቀብለው ጊዜ ሳይፈጁ ወደ ሥራ የገቡት ጉታ፣ በሬዎቻቸውን ጠምደው እያረሱ እና ለሚዘሩት ምርት የማለስለስ ሥራ እያከናወኑ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ። በ60ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት ጉታ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ መሬቱ ከረጅም ጊዜ በፊት በእርሳቸው ወንድም ባለቤትነት ስር ይተዳደር እንደነበርና ለቤት መሥሪያ ለሰዎች በተሰጠበት ወቅት እንዲነሱ ተደርገው እንደነበረ ያስታውሳሉ።

ነገር ግን መሬቱ ከስምንት ዓመታት በላይ ክፍት እንደሆነ እና ቤትም እንዳልተሠራበት ያስረዳሉ። በእርግጥ አዲስ ማለዳ በስፍራው ተዘዋውራ መመልከት እንደቻለችው ከባለ አንድ እስከ ባለ ሦስት ፎቅ ቤቶች በአካባቢው ተገንብተው ሰዎችም እንደሚኖሩበት ለማየት ቢቻልም፣ ጉታ ለእርሻ በሚጠቀሙበት ስፍራ ግን እምብዛም ቤቶች አይታዩም። ይሁን እንጂ የሚታረሰው መሬት ለእርሻ የተከለለ መሬት ለመሆኑ ጥርጣሬን የሚያጭር ነው።

አዲስ ማለዳ በስፍራው በሬ ጠምደው እርሻ ሲያርሱ የነበሩትን ጉታ በቀለን ከእርሻ መሬታቸው ቀጥሎ በእንጨት ታጥሮ የተከለለው ባዶ መሬት ተመልክታም ጥያቄ አቅርባ ነበር። ‹‹ምን እንደሆነ አላውቅም ግን ይህን መሬት እረስበት ተብዬ ሲሰጠኝ በማግስቱ የተወሰኑ ሰዎች መጥተው አጥረውት ሄዱ›› ሲሉ መልሰዋል።
አዲስ ማለዳ ቅኝቷን ከአርሶ አደሮች ወደ አካባቢው ነዋሪዎች መልሳ ጥያቄዎችን ስታቀርብ ቆይታለች። የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት ዜና ዓለማየሁ ለአዲስ ማለዳ እንደሚናገሩት፣ ስፍራው ከዓመታት በፊት ለቤት መሥሪያነት ለማኅበራት ተሰጥቶ የነበረ ሲሆን፣ የተወሰኑት ሠርተው ቀሪዎቹ ደግሞ መሥራት ባለመቻላቸው ክፍት እንደተተወ ይናገራሉ። ይህንም ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሦስት እና አራት ጊዜ በላይ ወጣት ልጆች በመምጣት አጥረውት እንደነበርና በተደጋጋሚ መንግሥትም እንደሚያስፈርሳቸው አስረድተዋል።

ነዋሪዋ አክለውም ከዛሬ 10 ዓመት በፊት በአካባቢው ቤት ሠርተው ሲገቡ እምብዛም ሰው ያልነበረበት አካባቢ ሲሆን፣ አርሶ አደሮች በርከት ብለው ይኖሩ እንደነበርና ካሳ ተከፍሏቸው መነሳታቸውን ግን መስማታቸውን ያስታውሳሉ። ይህንንም ተከትሎ በርካታ ገንዘብ ፈሰስ እንደተደረገም እንደሚያውቁ ተናግረው፣ ነገር ግን አብዛኞቹ እዛው አካባቢ የጭቃ ቤቶችን ሠርተው መኖር እንደመረጡ ለአዲስ ማለዳ ጠቅሰዋል።

‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወረዳ አስተዳደሮች በተቀያየሩ ቁጥር ይህን ስፍራ በተደጋጋሚ እንዲታጠር እንደሚያደርጉ እና ብዙም ሳይቆዩ በተለይም ደግሞ ምክትል ከንቲባው በመሬት ወረራ ዙሪያ በተናገሩ ወቅት እንዲፈርስ ተደርጎ ነበር›› ሲሉ ያስረዳሉ። በሕጋዊ መንገድ ሰዎች ለመኖሪያ ቤት መገንቢያ የተሰጣቸውን ቦታ ነው እየታረሰ የሚገኘው የሚሉት ነዋሪዋ፣ ጥብቅ ክትትል ከመንግሥት በኩል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዘንድሮው የምርት እና የእርሻ ዘመን በአገር ዐቀፍ ደረጃ ምንም አይነት ጾሙን የሚያድር መሬት እንደማይኖር አስታውቀው፤ በባለሀብቶች ተወስደው ወደ ሥራ ባልገቡ መሬቶችም ላይ፣ መሬቶቹ የሚገኙበት ክልል መንግሥት እንዲያርሰው እና ይህም ሊፈጠር የሚችለውን የምግብ ምርት ዕጥረት መቋቋም የሚቻልበት መንገድ አንዱ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች በከተማ አስተዳደሩ ዘንድ በሚነገሩ መረጃዎች መሰረት ከፍተኛ የመሬት ቅርምት እንዳለ እና ይህንም ተከትሎ አሁን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣው መመሪያ ቅርምቱን ወደ ሌላ ደረጃ እንዳያሸጋግረው ተፈርቷል።

በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ባንክ ልማት ድርጅት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ እና ሥማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ሰው ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፤ በመንግሥት ደረጃ ተግባራዊ የሆኑ እና ከዚህ ቀደም በወረራ ተይዘው ነገር ግን በተደረገ ዘመቻ ወደ መሬት ባንክ የተመለሱ እንዳሉ ሁሉ በጥቅም ትስስር አሁንም ቁጥራቸው የበዙ መሬቶች መሰብሰብ አልተቻለም።

በተለይም ደግሞ በቅርቡ በጠቅላይ ሚነስትሩ በኩል የተላለፈው እና በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ መሬቶችን የማረስ እና ምርት የማምረት እርምጃ ይህን ነገር ለማባባስ ትልቅ አቅም እንደሚኖረው እና ይህ ወቅት ሲያከትም እና መልካሙ ጊዜ ሲመጣ መንግሥት ተጨማሪ ዙር ካሳ ከፍሎ ሊያስነሳቸው እንደሚችል አልሸሸጉም።

መንግሥትን ለአላስፈላጊ ወጪ ከሚዳርጉት እና የመንግሥትን ዋነኛ ሀብት ከማሟጠጥ ባለፈ ካዝናን ባዶ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች እንደሚሆኑም ኃላፊው ጠቁመዋል። ‹‹መሬት በዋናነት የመንግሥት ትልቁ ሀብት ነው። ይህን ሀብት መንግሥት በአግባቡ የማይጠቀምበት ከሆነ ትልቅ አገራዊ ቀውስ ውስጥ ነው የሚገባው። ምክንያቱም መንግሥት ትልቁ ገቢው ከመሬት የሚገኘው እንደመሆኑ መጠን ያን ገቢውን በአንድም በሌላም ያጣዋል ማለት ነው›› ሲሉ ይገልጻሉ።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በቦሌ ለሚ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪ ይህንን ሐሳብ በሚገባ ይጋሩታል። መንግሥት በሌላ አገራዊ እና ዓለማቀፋዊ ጉዳይ ላይ በተጠመደበት ወቅት ይህን የመሬት ወረራ እየተፈጸመ እና እርሻ እየተካሄደ ባለበት ሁኔታ፣ ቦታውን እንዲለቁ በሚደረግበት ወቅት ድጋሚ ካሳ የሚጠይቁ እና የሚከፈላቸው ከሆነ ብልሹ አሰራሮችን አሁንም መቀረፍ አለመቻላቸው ምልክት እንደሆነ ያስረዳሉ።

የመሬት ባንክ ልማት ኃላፊው እንደሚሉት፣ በሕጋዊ መንገድ ተይዘው ነገር ግን ረጅም ዓመታት ምንም አይነት ሥራ ሳይሠራባቸው ታጥረው የተቀመጡ መሬቶችን መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ወደ መሬት ባንክ የማስገባት ሂደቱ ባለፈው ዓመት ጀምሮ ሲካሔድ ነበር።

አዲስ ማለዳም በ23ኛ እትሟ በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ትንታኔ ማውጣቷ ይታወሳል። ለሪል እስቴት ቤት ልማት ተሰጥተው በቤት ፈንታ ዳዋ ሲውጣቸው የኖሩ የከተማዋን ቦታዎች ከ29 የሪል እስቴት አልሚ ኩባንያዎች ለመንጠቅ መወሰኑን ተከትሎ፣ ወደ መሬት ባንክ የገቡት ቦታዎች መጠን ከዚህም እንደሚልቅ እሙን ነው።
ታዲያ በያኔው የለውጡ የለጋነት ዘመን በተደረጉ ግምገማዎች ምክትል ከንቲባው ሲናገሩ አይደፈሩም የተባሉ ቦታዎችን አስተዳደራቸው ሲነጥቅ ከሚኒስትሮችም ጭምር ‹ተው ይቅርባችሁ!› ሲባሉ ነበር። በዚህም የቦታ መንጠቅ ሂደቱ በርካታ ችግሮችና ፈተናዎች የነበሩበት እንጂ አልጋ በአልጋ እንዳልነበር በመጠቆም አስተዳደራቸው ይህን በድፍረት በማድረጉ ታላቅ ኩራት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል። ይህም በቀደሙት የአስተዳደሩ የበላዮች ያልተሞከረ በመሆኑ ለአዲሱ አስተዳደር አንዱ የጥንካሬ ማሳያ መሆኑን በመጥቀስ ከነዋሪዎች በኩልም በርቱ ሊባሉ እንደሚገባ ያምናሉ።

ዳንኤል ሌሬቦ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ልማትና ምህንድስና ኮሌጅ ዲን ናቸው። ዳንኤል እንደሚሉት ያልለሙ ቦታዎችን ነጠቃው እጅግ የዘገየ ቢሆንም አዲሱ አስተዳደር የወሰደው እርምጃና ቁርጠኝነት ግን ሊደነቅ ይገባዋል። ከዓመታት በፊት በአዲስ አበባ መሬት ልማት ማኔጅመንት የአንድ ክፍለ ከተማ መምሪያ ኃላፊ የነበሩት ዳንኤል፣ ለልማት ተብለው ከተሰጡ ቦታዎች መካከል ለ20 ዓመታት ያለጠያቂ ታጥረው የነበሩ ቦታዎች በቅርቡ በተወሰደው እርምጃ መነጠቃቸውን በመጥቀስ፣ ትልቅ እምርታ ነው ይላሉ። ግን ደግሞ እርምጃው የዘመቻና የአንድ ወቅት ሥራ ሆኖ እንዳይቀር ይሰጋሉ።

በእርግጥ አስተዳደሩ ሲባክኑ የነበሩ ቦታዎችን ወደ መሬት ባንክ ማስገባቱ ቢደነቅለትም ምንድነው ሊሠራባቸው ያቀደው፣ አሁንስ ምን ላይ ናቸው የሚለው ጥያቄ መልሶ እየተነሳበት ነው። አስተዳደሩ ቦታዎቹን ለምን ለምን ዓይነት ልማት አቅዷቸዋል ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የጠየቅናቸው በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ተስፋዬ ጥላሁን፣ ጥያቄውን በበርካታ የመገናኛ ብዙኀን አውታሮች በየቀኑ እየተጠየቁ ስለመሆኑ በመግለፅ የተለየ ዕቅድ እንደሌለ ተናግረዋል።

ይህም ማለት አስተዳደሩ ቦታዎቹን የነጠቀው አቅዶ አይደለም ማለት ነው። ቦታዎቹን ወደ መሬት ባንክ ከማስገባት ባሻገር ምን ይሠራባቸዋል የሚለውን እስከ አሁን የወጣ ዕቅድ የለም ወይ ለሚለው ጥያቄም ተስፋዬ ‹‹አዎን›› የሚል ምላሽ ሰጥተውናል። እንዴትና በምን ምክንያት ነው አስተዳደሩ ረጅም ዓመታትን ያለ ጥቅም የቆዩ ቦታዎችን ወደ ልማትና ጥቅም ለመመለስ ዕቅድ የማያወጣው የሚለውን ጥያቄ ብናስከትልም፣ ሥራ አስኪያጁ ከዚህ በላይ ምላሽ ሊሰጡ አልፈቀዱም።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ ወደ መሬት ባንክ ከገቡ ከዓመት በላይ ስለሆናቸው ቦታዎች ባለፈው ሳምንት ሲናገሩ አስተደደሩ ከመንጠቅ ባለፈ ቦታዎቹን አሁንም ወደ ምጣኔ ሀብት ማስገባት አለመቻሉን ገልጸዋል። ይህ ታዲያ በኹሉም ሥራ ኃላፊዎች ዘንድ የሚነሳ ቅሬታ ነው። አዲስ ማለዳ ይህን ጽሑፍ በሚዘጋጅበት ወቅት ያናገረቻቸው በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎችም ይህንኑ ይጋራሉ።

የከተማ ልማትና ምህንድስና ምሁሩ ዳንኤል ‹‹የከተማ ሀብት እጅግ ውስን የሆነው መሬት ነው›› ካሉ በኋላ፣ ይህን ውስን ሀብት በጠንካራ ሕግና ቁጥጥር ማስተዳደር እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ። ከዚህ ቀደም አንድም ለቦታዎች ረጅም ጊዜ ታጥሮ መቆየት ምክንያቱ የመሬት ዘርፍ ባለሙያዎች ከባለሀብቶች ጋር የሚኖራቸው አላስፈላጊ (የጥቅም) ግንኙነት ነውም ይላሉ።

ዋናው ግን በከተማዋ ከማእከል እስከ ወረዳ ባለው መዋቅር ፍፁም መናበብ አለመኖር ነው። ለልማት የሚተላለፉ ቦታዎችን ውል መነሻ በማድረግ ‹መቼ ይለማሉ? እስከመቼስ ተጠናቅቀው ለተፈለገው አገልግሎት ይውላሉ?› የሚለውን የተግባር ዕቅድ (action plan) አውጥቶ ከከንቲባ እስከ ወረዳ አመራር በጥብቅ መናበብ ከመከታተል ይልቅ ውልን መደርደሪያ (ሼልፍ) ላይ ሰቅሎ ነገር ዓለሙን የመርሳት አባዜ ቦታዎቹን ለረጅም ዓመት ከልማት ውጭ ስለማድረጉ በማንሳትም ይህ ልማድ ሊታረም እንደሚገባው ዳንኤል አፅንኦት ይሰጣሉ።

መሬትን ከመስጠት ባለፈ ‹ማን ይከታተለዋል? መቼስ ያልቃል?› የሚለው ላይ አስተዳደሩ በርትቶ መሥራት እንዳለበት ያስገነዝባሉ። ያልለሙ የሪል እስቴት ቦታዎችን በተመለከተ ውሳኔ ለማሳለፍ ምክትል ከንቲባው ካቢኔያቸውን በሰበሰቡበት ወቅት ቦታዎቹ እስከ ዛሬ እንዴት ጦማቸውን አደሩ ያልናቸው ተስፋዬ ደግሞ፣ ለዚህ አንዱና ዋናው ምክንያት በመንግሥት በኩል ክትትል አለመደረጉ እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል።

ሌላው ቦታ ስላለ ብቻ እያነሱ ማልማት ለማይችሉና አቅሙ ለሌላቸው፣ ሲብስም የተረከቡትን ቦታ አሳልፈው ለሚሸጡ አካላት ከመስጠት መቆጠብን እንደሚጠይቅ የሚመክሩት ምሁሩ፣ ዘርፉም በባለሙያ መመራት እንዳለበት ያሰምሩበታል። ከዚህ ቀደም መሬት ዘርፍ ላይ እውቀቱም፣ ልምዱም የሌላቸው ሰዎች እየተመደቡ በክህሎት ማነስ በሠሩት ስህተት ቤተሰባቸውን በትነው እስር ቤት የገቡም እንዳሉ ያስታውሳሉ።

ይህን ለአብነት አነሳን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግሥት በኩል የተላለፈው ኹሉንም መሬቶች የማረስ እና ምርት መሰብሰብ ስትራቴጂ ይህን በሕገ ወጥ መንገድ መሬትን የመውረር ስልትን የሚያረቅ እና ለሌላ ውስብስብ በመሬት ዙሪያ ለሚደረጉ ትስስሮች በር ይከፍታል ብለው የሚያምኑ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።
በዚህ ዙሪያ በአዲስ አበባ ከተማ የከተማ ግብርና ኮሚሽን ኮሚሽነር ፈቲያ መሐመድ ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ፤ ኮሚሽኑ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆን ለከተማ ግብርና የተለዩ ስፍራዎችን ያዘጋጀ ሲሆን ከዚህ ውጪ ያሉ እና እርሻ እየተከናወነባቸው የሚገኙ ስፍራዎችን ኮሚሽኑ እንደማያውቀው ያስረዳሉ። መረጃው እንዳላቸው እና አንዳንድ ጊዜም ለሥራ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ሰፋፊ እርሻዎችን እንደሚያዩ እና ከኮሚሽኑ እውቅና ውጪ የሆኑ ሳይቶች መሆናቸውንም አልሸሸጉም።

በተባበሩት መንግሥታት ዩኤን ሀቢታት ʻTHE STATE OF ADDIS ABABA 2017ʼ በሚል ኹለት ዓመታትን የፈጀ ጥናት ይፋ በሆነበት ሰነድ፣ በአዲስ አበባ መሃል ከተማ ውስጥ 80 በመቶው እንደገና ፈርሶ ሊገነባ የሚገባው ወይም ያልለማ (ቆሻሻ) አካባቢ የሚባል እንደሆነ ያስረዳል። 70 በመቶ ቤቶችም መሰረታዊ የሚባል የልማት አቅርቦት የሌላቸውና አብዛኞቹም የቀበሌ ቤቶች ናቸው።

ይህን ገፅ ለመቀየር መጠነ ሰፊ የመልሶ ማልማት ሥራ ቢጀመርም በአንድ በኩል ነዋሪዎችን ከመሃል ከተማ ወደ ዳር በመግፋት እንዲሁም አካባቢውን በስሜት አፍርሶ ሳያለሙ ረጅም ዓመታትን በማቆየት አስተዳደሩ ይወቀሳል። በመሆኑም አሁንም ያንን ማረም እንጂ አዲስ ጥፋት ከመፈፀም መቆጠብ እንደሚገባ ምክረ ሐሳቦች ተቀምጠዋል።

በዚህ የምርት ዘመን በከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ ይፋ የተደረገው የከተማ ግብርና ፕሮጀክት ከ100 በላይ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን እና በሕጋዊ መንገድ በግብርናው ዘርፍ ለሚሰማሩ እንደሚተላለፉ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ አስታውቀዋል።

ወጣት ባለሙያዎች እንዲሳተፉ በቀረበው ጥሪ መሰረትም በኦንላይን ምዝገባው እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን፣ ከተለዩ ቦታዎች የተወሰኑትን የጎበኙት ታከለ የከተማ ግብርና ሐሳብ ነዋሪዎች ባላቸው ክፍት ቦታ ላይ በመጠቀም ለምግብነት አትክልትና ፍራፍሬ እንዲያመርቱ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

አልፎም ከተማዋ በአትክልት እና ፍራፍሬ ራሷን የምትመግብበት እንዲሁም ከፍ ሲልም በምግብ ራሷን የምትችልበት ፕሮጀክት መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ተደምጠዋል። የከተማ ግብርና በከተማዋ በተለያየ ወቅት የሚፈጠሩ እጥረቶችንም ለመቅረፍ ይረዳል፣ እንደ ምክትል ከንቲባው ገለጻ።
አዲስ አበባ ከዚህ ቀደም እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን ፍጆታዋን ከከተማ ግብርና ታገኝ እንደነበርም ጥናቶች ያመላክታሉ።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዑመር ሁሴን፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለከተማ አስተዳደሩ የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል የገቡ ሲሆን፤ የከተማ ግብርና ፕሮጀክቱ በተለይም በከተማዋ የሚገኙ የወንዝ ፍሰቶችን በመከተል የሚተገበር እንደሚሆንም አቅጣጫ ተቀምጦለታል። ይሁን እንጂ ለዚህ ጽሑፍ ግብኣት እንዲሆን አዲስ ማለዳ በተንቀሳቀሰችባቸው አካባቢዎች ምንም አይነት ወንዝ በሌለበት ወይም ለወንዝ ቅርብ ባልሆነበት ሁኔታ እና መኖሪያ መንደሮች ውስጥ በሚገኙ ክፍት ቦታዎች እርሻ ሥራዎች ሲከናወኑ አስተውላለች።

በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎችንም ባነጋገረችበት ወቅት ለመኖሪያ መንደሮች የተሰጡ የአረንጓዴ ስፍራዎች መሆናቸውን እና በአንድ አዳር ታጥረው ወደ እርሻ ስፍራነት መለወጣቸውን ይናገራሉ።

ከኢትዮጵያ ቢዝነስ ሪቪው መጽሔት ተወስዶ በትርጉም በአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ላይ ለንባብ በበቃው እና ‹‹አዲስ አበባን ምድረ ገነት የማድረግ ጉዞ› የሚል ርዕስ የተሰጠው ጽሑፍ በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያሉ ሐሳቦች የተነሱበት ዘገባ ነበር። ከዚህም ጋር ተያይዞ በመዲናዋ አዲስ አበባ እየታየ የመጣውን የሕዝብ ቁጥር እድገት መሰረት አድርጎ የከተማዋ የምግብ ፍላጎት መጨመሩን ያስረዳል።

እስካለፈው ዐስር ዓመት ድረስም አዲስ አበባ ራሷን የቻለችበት ምርት ቢኖር ወተት ነበር፣ እንደ ዘገባው። በኋላ ግን በአነስተኛ ደረጃ ሆነው በግለሰብ ደረጃም የወተት ምርት ላይ የሚሠሩት ከንግድ ውጪ እንዲሆኑ ተገፍተዋል። ይህንንም ያደረገው አንድም የከተማነት መስፋፋት ነው። እናም አሁን ከተማዋ ብዙ የወተት ምርትን በዙሪያ ካሉ ከተሞች እየተቀበለች ትገኛለች። በአንጻሩ ደግሞ የአዲስ አበባ አባወራ ቁጥር ባለፈው አምስት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ጭማሬ አሳይቷል።

የወተት ምርቱን ማሳያ ተጠቀሰ እንጂ በድምሩ የከተማ ገበሬዎች ቁጥር ባለፉት ዓመታት በእጅጉ ቀንሷል። ይህ የቁጥራቸው መቀነስ ቀጥሎ አሁን ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት 86 ሺሕ የሚጠጉ በአነስተኛ ደረጃ የሚያርሱ ገበሬዎች በአዲስ አበባ ይገኛሉ። ከሰባት ወራት በፊት የአዲስ አበባ ከተማ ግብርና ኮሚሽን መመሥረቱን ተከትሎ ጥሩ ተስፋ የታየ ሲሆን፣ ቢያንስ ቁልቁል እየወረደ የነበረው የከተማ ገበሬዎች ቁጥር የመቀነስ ፍጥነትን አርግቦታል።

በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ለአዲስ አበባ የግብርና ቢሮ ባለመኖሩ ምክንያት የከተማዋን የግብርና ውጤት፣ ምርት፣ የገበያ ሁኔታ፣ ፋይናንስና ግብዓት፣ ሥልጠና እና የግብር እፎይታን በተመለከተ የሚያስተባብርና የሚከታተል አካል እንዳይኖር አድርጓል። በዚህም ምክንያት የከተማ ግብርናን በቢዝነስ መልክ ለመሥራት የሚኖረውንና ሊኖር የሚችለውን ፍላጎት ቀንሷል።

ከላይ እንደተገለጸው ኮሚሽኑ ከተቋቋመ በኋላ ሁኔታው የተቀየረ ይመስላል። ይህም የሆነው በተለይም ምርት፣ የገበያ አቅርቦትና ለሥልጠና አስፈላጊው ግብዓት የማሟላት እንቅስቃሴ ስለተጀመረ ነው።

በጸጋዬ ደምሴ የተሠራ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው በግብርና ላይ ያልተሰማሩና አትክልቶች የማያመርቱ አባወራዎች ብዛት በአዲስ አበባ 99.7 በመቶ ሲሆን በአንጻሩ በአፋር 94.9 በመቶ እንዲሁም በድሬዳዋ 94.2 ነው። በተመሳሳይ ፍራፍሬ የማያመርቱት ሲታይ፣ አዲስ አበባ መቶ በመቶ ፍራፍሬ አይመረትም። በድሬዳዋ 95.3 በመቶ እንዲሁም በአፋር 92.9 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።

በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በምግብና ግብርና ድርጅት (FAO) እንዲሁም በዓለም ጤና ድርጅት የተቀመጠውን ዝቅተኛውን መስፈርት እንኳ አታሟላም። ይህም የሆነው አዲስ አበባ የከተማ ግብርና ፖሊሲን ዋጋ እንደሌለው ትታ በመቆየቷ ነው።

ይህ መሬትን በሕግ አግባብ ከሆነ አካሔድ ውጪ መያዝ እና ለግል ጥቅም ማዋል አዲስ አበባን እንደማሳያ አደረግን እንጂ በኹሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ በስፋት እንደሚስተዋል አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባህርዳር የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች አስረድተዋል። በባህር ዳር እና ዙሪያዋ አሁንም ድረስ በሕገ ወጥ የመሬት ወረራዎች እንደሚስተዋሉ እና በቀጥታ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ጋርም የጥቅም ትስስር ያላቸው ሰዎች መኖራቸውን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሥራ ኃላፊዎች ይናገራሉ።

በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበውን እና ኹሉንም ክፍት መሬት የማረስ እና ምርታማነትን መጨመር ሂደትን ተከትሎ በክልላቸው እና በከተማቸው መንግሥት በዋናነት እንደሚያከናውን እና ምርቱም በመንግሥት ስር እንደሚሆን ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙት መሬቶች በአንድ አርሶ አደር ሥም ይመዘገብ እና ለረጅም ዓመት የመሬት ግብር ሲከፍልበት እንደቆየ በማስመሰል መንግሥት ለኢንቨስትመንት ቦታውን በሚፈልግበት ጊዜ የጥቅም ተጋሪዎች አርሶ አደሮች ካሳ እንዲከፈላቸው በማድረግ ከመንግሥት ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ እንደሚመዘብሩ በእርግጠኝነት ይናገራሉ።

በመሆኑም የእርሻ ሥራው ከመጀመሩ በፊት ቁርጠኛ እርምጃ ካልተወሰደ ወደ ፊት ከፍተኛ የሆነ ኪሳራ በመንግሥት ላይ እንደሚደርስ ያሳስባሉ። እንደ ምክንያት የሚጠቅሱት ደግሞ መሬቶች ከዚህ ቀደም በመንግሥት የተነሽነት ካሳ ተከፍሎባቸው በመሬት አስተዳደር ስር የሚገኙ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ወጪ ያስወጣሉ የሚል ሐሳብ እንዳላቸው ተናግረዋል።

በመሬት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ምርምር ያደረጉት ፋና ገብረሰንበት (ረ/ፕ) ከአዲስ ማለዳ እህት መጽሔት ኢትዮጵያ ቢዝነስ ሪቪው ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በአገር ዐቀፍ ደረጃ የመሬት ክፍፍሉ እና ለአንድ አባውራ የሚደርሰው መሬት መጠን እጅግ እያሽቆለቆለ መምጣቱን ይናገራሉ። ፋና አያይዘውም መሬት እጦቱ እጅግ አስጊ ደረጃ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ ከኹለት ዐስርት ዓመታት በፊት የነበረው በአንድ የመሬት ባለንብረት ኹለት ሔክታር መሬት አሁን ወደ ግማሽ ሔክታር ማሽቆልቆሉ አንዱ እና ትልቁ ማሳያ እንደሆነ ይናገራሉ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሰላም እና ደኅንነት ጥናት ተቋም ምሁሩ ፋና በመሬት እና ተያያዥ ጉዳዮች ሰፊ ጥናት አካሒደዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ ጊዜያት የተሠሩ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚያሳዩት፣ በክልሎች በወጣቱ ዘንድ የሚታየው መሬት እጦት ከፍተኛ እንደሆነ ነው። በዚህም መሰረት በትግራይ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል መሬት እጦቱ ጎልቶ ከሚታይባቸው ክልሎች ውስጥ ግንባር ቀደምት መሆናቸው ታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here