የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ከአውስትራሊያ መንግሥት ጋር የ120 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው 400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለመግዛት የሚያስችል ስምምነት መፈራረሙን አስታወቀ።
የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፣ ከተፈረመው የ120 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ በመጀመሪያ ዙር በ30 ሚሊዮን ዶላር 100 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ በተያዘው በጀት ዓመት ለማስገባት ስምምነት ላይ መደረሱ ታውቋል።
ከአውስትራሊያ መንግሥት ጋር የተደረገው ስምምነት የኢትዮጵያ መንግሥት ቅድሚያ ስንዴውን ከክፍያ ነጻ ካስገባ በኋላ በአንድ ዓመት ውስጥ የሚከፈል መሆኑን የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ መልካሙ ደፋሊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በዚሁ አግባብ 30 ሚሊዮን ዶላር በተያዘው በጀት ዓመት የሚከፈል ነው ተብሏል።
ምናልባትም ቀሪው የ90 ሚሊዮን ዶላር ግዥ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቀዛቀዘው የሎጂስቲክስ ሥራ ወደ ነበረበት በቅርቡ ሊመለስ የሚችል ከሆነ፣ በተያዘው በጀት ዓመት የግዥ ሂደቱ አልቆ ሙሉ በሙሉ ወደ አገር ውስጥ የማጓጓዝ ሥራው ሊጠናቀቅ እንደሚችል መልካሙ ጠቁመዋል።
የግዢ ሂደቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአውስትራሊያ አምራቾች ስንዴውን በአውስትራሊያ መንግሥት በኩል ገዝቶ በማስገባት ስንዴው ሙሉ በሙሉ ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ከተጠናቀቀ ጊዜ ጀምሮ በአንድ ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት ለአውስትራሊያ መንግሥት ክፍያ እንደሚፈጽምና የአውስትራሊያ መንግሥት ደግሞ ለኢትዮጵያ ስንደ ለሸጡ አምራቾች ክፍያውን እንዲፈጽም የተደረገ ስምምነት ነው ተብሏል።
ከአውስትራሊያ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ስንዴ መንግሥት ገበያ ለማረጋጋት ለሚሠራው ሥራ እና በተለያዩ ምክንያቶች አስቸኳይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ ሊውል እንደሚችል ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የምትፈጽመውን የስንዴ ግዥ ከሌሎች አገራት መንግሥታት ጋር ለማድረግ በተለያዩ አገራት ጥናት ተደርጎ የተሻለ አማራጭ ማቅረብ የሚችሉ አገራት ተለይተዋል ተብሏል። ለኢትዮጵያ ስንዴ ለመሸጥ ከተመረጡ አገራት ውስጥ አውስትራሊያና ሩስያ የመጀመሪያዎቹ ተመራጮች ሆነዋል። በዚሁ መሠረት ከአውስትራሊያ መንግሥት ጋር ስምምነቱ ተደርጎ ስንዴውን ከአውስትራሊያ ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን መልካሙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ከሩስያ ጋር የስንዱ ግብይት ስምምነት ለማድረግ ኹለቱ አገራት በሂደት ላይ እንደሆኑና በቅርቡ ስምምነቱ ተጠናቅቆ ስምምነት ላይ ይደረሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ መልካሙ አክለው ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት በተደረገ የጨረታ ሥነ ሥርዓት ለ600 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ ከወጣው ጨረታ ለ200 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ብቻ ውል ማሰር ቢቻልም፣ በ400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ላይ ቅሬታ ቀርቦበት በግዥ ቦርድ ውሳኔ እንዲሰረዝ መደረጉን አገልግሎቱ አስታውቋል። በዚህም የካቲት 20/2012 እንደ አዲስ 600 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ጨረታ ወጥቶ አቅራቢዎች መሳተፋቸው ተጠቅሷል።
በቀጣዩ ዓመት የምርት መቀነስ ከኮቪድ 19 እና በረሃ አንበጣ ጋር ተያይዞ ሊከሰት ስለሚችል እና ይህንንም ምክንያት አድርጎ ቁጥሩ የበዛ ዜጋ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ስለሚታመን የስንዴው ግዢ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት መሆኑ ተጠቁሟል። በተለይም ከወረርሽኙ ባለፈ ከፍተኛ ስጋት የደቀነው የበረሃ አንበጣ መሆኑ በግብርና ሚኒስቴር ተጠቁሟል። በዚህም ረገድ የግብርና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የተከሰተውን የበረሃ አንበጣ ለመከላከልና ለመቆጣጠርና 63 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ማስታወቁ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የበርሃ አንበጣ ምላሽ ፕሮጀክት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እቅድ ባዘጋጀው ፕሮጀክት፣ የበረሃ አንበጣውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዩ ምድቦችን ያወጣ ሲሆን፣ ለዚህም ማስፈጸሚያ የሚሆን የ63 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል።
ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012



