የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ በ110 ሚሊዮን ብር ወጪ በተደጋጋሚ አደጋ ይደርስባቸዋል ተብሎ የተለዩ ቀለበት መንገዶችን እያጠረ እንደሆነ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ምክትል ኃላፊ ሰመረ ጀላሉ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ሥራው በአዲስ አበባ ከተማ በቀለበት መንገዶች፣ በድልድዮች፣ በአደባባዮችና በመታጠፊያ መንገዶች አካባቢ የሚከናውን ሲሆን፣ ይኸው በብረት የማጠር ሥራ አጠቃላይ 3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ይሸፍናል ብለዋል። ምክትል ኃላፊው አክለውም በቀጣይ ኹለት ወራት ውስጥ ማለትም እስከ ሰኔ 30/2012 ይጠናቀቃል ተብሎ እቅድ እንደተያዘለት ጠቅሰዋል።
ኤጀንሲው ሥራውን እያከናወነ የሚገኝባቸው ቦታዎች ከዚህ በፊት ከሌሎች ቦታዎች በተለየ መልኩ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ የሚከሰትባቸው ቦታዎች ሲሆኑ፣ እነዚህ የተመረጡ ቦታዎች በዓመት ከኹለት እስከ ሦስት ሰዎች ላይ የሞት አደጋ የሚከሰትባቸው መሆናቸውን ሰመረ ተናግረዋል።
በቀለበት መንገዶች ላይ የሚታጠሩ ብረቶች ጠንካራና የግጭት ሁኔታዎችን መቋቋም የሚችሉ ሲሆኑ ሊከሰቱ የሚችሉ የትራፊክ አደጋዎችን፣ በሰው ሕይወት በተለይም በእግረኞች ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ሊያስቀሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል። ጉዳቱ በሚደርስበት ወቅት ከንብረት ጉዳት ባለፈ በሰው ሕይወት እና የአካል ጉዳት እንዳይደርስ በቀላል የንብረት ግጭት እንዲያልፍ የሚያደርግ መሆኑንም ኤጀንሲዉ አስታውቋል።
የብረት አጥሮቹ በሚታጠሩበት አካባቢ እግረኞች የትራፊክ ሕግ እና ደንብን በመከተል ያለምንም ስጋት የእግረኛ መንገድን እንዲጠቀሙ የሚያደርግ ሲሆን፣ አሽከርካሪዎችም ድንገት እግረኛ ይገባብኛል የሚል ስጋታቸውን በመቀነስ ደኅንነቱ የተጠበቀ የትራፊክ ፍሰትና የእግረኛ እንቅስቃሴ እንዲኖር እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል። እግረኞችም በተሽከርካሪ መስመር ውስጥ በመግባት ፍሰቱን እንዳያስተጓጉሉም አይነተኛ መፍትሔ ነው ተብሎለታል።
እግረኞች የመንገድ ዳር አካፋዮችን በቀላሉ በመዝለል የሚያቋርጡ ሲሆን ይህም ለከፍተኛ የትራፊክ አደጋ የሚያጋልጥ መሆኑን ተጠቁሟል።
ከመንገድ ዳር አጥሮች ባለፈም በዓይነቱ ልዩ የሆነ እና በብዛት የትራፊክ አደጋ በሚከሰትባቸው ቦታዎች ላይ የሚሠራው ሥራ ከአሽከርካሪዎች ደኅንነት ጋር በተያያዘ ነው። ይህም ተሽከርካሪዎች ላይ ግጭት ወይም አደጋ በሚከሰት ጊዜ አሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችል ሴፍቲ ሮለር ሲሆን፣ በኃይሌ ጋርመንት አካባቢና በሲኤምሲ አደባባይ እየተተገበረ ይገኛል።
ነገር ግን የቀለበት መንገዶችን በብረት የማጠር ሥራው በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ የመሥሪያ ብረቶች ከውጭ ስለሚገቡ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በተያዘለት ጊዜ ላይጠናቀቅ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ ሰመረ ገልጸዋል።
ሴፊቲ ሮለሩን በሚመለከትም፣ በተለይ ለከባድ ተሽከርካሪዎች ቁልቁለታማ፣ ዳገታማ እና የመንገድ መታጠፊያዎች ላይ ጠቀሜታው የጎላ ሲሆን፣ በቀጣይም በከተማዋ መሰል መንገዶች ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል ተብሏል። እንዲሁም ተሸከርካሪዎች በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ሳያደርሱ ባሉበት አንሸራቶ ማቆም የሚችልና መስመር ስተው ከሆነ ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲገቡ ማድረግ የሚችል ነው።
ኤጀንሲው ከአየር ጤና ዘነበ ወርቅ መንገድን ጨምሮ በሌሎች የቀለበት መንገዶች የብረት አጥሮችን በመትከል ለትራፊክ አደጋ ተገላጭነትን በመቀነስ ላይ ይገኛል። አንደ ሰመረ ገለጻ ኤጀንሲው አሁን ላይ እያከናወነው የሚገኘው ሥራ ሲጠናቀቅ በቦታዎቹ ላይ ሊደርስ የሚችለውን የሰው ሕይወት ኅልፈት ማስቀረት እንደሚቻል ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በሚከሰት የመንገድ ትራፊክ አደጋ በቀን የ13 ሰዎች ሕይወት የሚያልፍ እንደሚልፍ ቀደም ብለው የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የአስፓልት መንገድ ሽፋን 14 በመቶ መሆኑን የሚጠቁመው ጥናቱ፣ 80 በመቶ የሚሆነው አደጋ የሚደርሰው በአስፓልት መንገድ ላይ መሆኑንም አመላክቷል።
ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012



