ቶክዮ የ2020 ኦሎምፒክ ውድድሮችን ለማከናወን ሁሉን አሰናድታ ዝግጅቷን ማልዳ ብትጨርስም፣ እንደ እንግዳ ደራሽ የሆነው ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ በመጨረሻው ሰዓት ድግሷን እንዳይሆን አድርጎታል። ይህም ብቻ አይደለም፣ ለውድድሩ ራሳቸውን በሚገባ እያዘጋጁ የነበሩ፣ ለድልም መንፈሳቸውን ያበረቱ አትሌቶችን ምኞትና ፍላጎት አደብዝዟል። ምንም እንኳ በ2021 ውድድሮች መካሄዳቸው አይቀርም ቢባልም፣ በአስጊነት ማማ ላይ የተቀመጠው ወረርሽኙ በቀጣይ ዓመትስ እንደማይኖር፣ እንደሚጠፋ ምን ዋስትና አለ እየተባለ ነው።
ታድያ የወረርሽኙ ስጋት አስቀድሞ ባጠላባቸው አውሮፓ አገራት እግር ኳሱም ተመሳሳይ እጣ ነው የገጠመው። ሁሉም በሚባል ደረጃ ጨዋታዎች የተቋረጡ ሲሆን፣ እስከ ቅርብ ጊዜም ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝመው ነበር። ውድድሮቹ የሚቋረጡ ከሆነ የዓመቱ አሸናፊ ማን ይሆናል? ከታችኛው ከሚባለው ምድብ (ዲቪዚዮን) የሚገኙና ለማደግ ብዙ ወጪ አውጥተው ዓመቱን የተጫወቱ፣ በሊጉ ደግሞ ባላቸው ዝቅተኛ ነጥብ ወደ ታችኛው ምድብ የሚወርዱና መሰል ኹነቶች በቫይረሱ ምክንያት ተዛብተዋል።
ታድያ ውድድሮች የሚሰረዙ ከሆነ ዓመቱ እንዳልነበረ ሙሉ ለሙሉ የማጥፋት ያህል የሚቆጠር ነው፣ ለእግር ኳስ ቤተሰብ። ይህ እንዳይሆንም ብዙ ሙግትና ክርክሮች የተካሄዱ ሲሆን፣ የአውሮፓ እግር ኳስ እንቅስቃሴ የጀመረ ይመስላል። የጀርመን ቡንደስ ሊጋም በዚህ ቀዳሚውን እርምጃ ወስዷል። ከኹለት ወር በኋላ በዘመነ ኮሮና የመጀመሪያውን የእግር ኳስ ጨዋታ በዝግ ስታድየም አካሂዷል። ቦርስያ ዶርትሙንድ እና ሻልካ ባደረጉት በዚህ ጨዋታም ዶርትሙንድ አራት ለባዶ አሸንፏል። ደስታው ግን እንደ ወትሮው አይደለም።
ይህን በሚመለከት ከቀናት በፊት አልጀዚራ ባስነበበው ዘገባ፣ የጀርመኑ ሊግ ውድድር ይጀምር እንጂ የቀደመ መልኩ ጠፍቷል። ተጫዋቾች ለብቻቸው እንጂ አብረዋቸው ወደ ሜዳ የገቡ ሕጻናት ልጆች የሉም፣ መነካካት አይታሰብም፣ ከዳኞች ጋር መጨባበጥም እንደዛው፣ ጎል አግብቶ መተቃቀፍ ቀርቷል። ጨዋታው ሲደረግ ከክለቦቹ አስፈላጊ ሰዎች፣ እሳት አደጋ ሠራተኞችና ጥቂት ፖሊሶች፣ የስታድየም ጠባቂዎችና ጋዜጠኞች ብቻ ግን ይገኛሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ማተናገድ በለመደው በግዙፍ ስታድየም ውስጥ ሦስት መቶ ሰዎች ብቻ ተገኝተዋል።
በሜዳው ጭንብል ከማድረግ ጀምሮ ተገቢው ጥንቃቄ ሁሉ እንዲደረግ ይጠበቃል። አሠልጣኞች ጮኸው መልእክት ማስተላለፍ ከፈለጉም 1.5 ሜትር ርቀት ላይ ሲሆኑ ብቻ አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብላቸውን ማውለቅ ይችላሉ። ተቀያሪ ተጫዋቾች ደግሞ ተራርቀው ይቀመጣሉ። ከዛም በላይ አንድም ደጋፊ በስታድየሙ ውስጥ አይገኝም። በጥቅሉ እግር ኳስ ውበቱን በወረርሽኙ ተነጥቋል ማለት ይቻላል። ግን እንዳሉት ከሆነ ምንም ጨዋታ ካለማድረግ እንዲህ ባለ መልኩም ቢሆን መቀጠሉ ይሻላል። በዚህ የማይስማሙ ብዙ ቢሆኑም።
አልጀዚራ ታድያ በዘገባው እንዲህ ሲል አስፍሯል፣ ‹‹ደጋፊ በሌለበት ባዶ ስታድየም ጎል ማግባት ይጨንቃል። ተጫዋቾችም ስሜታቸውን እንዲገቱ ነው የሚመከሩት››
በኢንግሊዝ ፕሪምየር ሊግም ጨዋታዎች በዝግ ስታድየሞች በቅርቡ ይጀመራሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ቡድኖችም ወደ ልምምድ ገብተዋል። እንደውም ከሰሞኑ በወጣው መረጃ መሠረት የዋትፎርድ እና በርንሌይ ቡድኖች ውስጥ ቫይረሱ ያለባቸው ተጫዋቾች ተገኝተዋል።
ቢቢሲ እንዳስነበበው ከሆነ አንድ ረዳት አሠልጣኝን ጨምሮ ስድስት ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው በምርመራ ተረጋግጧል። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን አግልለው ለቀናት እንዲቀመጡ ተመክረው በራቸውን ዘግተዋል። በድምሩም በሊጉ 748 ተጫዋቾችና የቡድን አባላት ከ19 ክለቦች ምርመራ ተደርጎላቸዋል። እንዲያም ሆኖ ለቤተሰባቸው በመስጋት በቤት ውስጥ ልምምዶችን ማድረግን እንመርጣለን ያሉ ተጫዋቾች ጥቂት አይደሉም።
ታድያ ይህ መሆኑ ምንአልባት በቅርቡ የሚለውን የሊጉን መጀመሪያ ጊዜ ሊገፋውና ራቅ ሊያደርገው ይችላል እየተባለ ነው።
በኢትዮጵያስ?
ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካ አገራት የውድድር ዓመቱን በመሰረዝ ስፖርት ጉዳይ አጀንዳ እንዳይሆን አድርገው ቋጭተውታል። በአፍሪካ ደረጃ የሚደረጉ የሻምፕዮን ውድድሮች የሁሉንም የአፍሪካ አገራት ውሳኔ የሚጠብቁ በመሆናቸው፣ እንደ ስምምነቱ አገራት ውሳኔያቸውን አሰምተዋል።
ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊጉን ጨምሮ ሁሉንም ውድድሮች ሙሉ ለሙሉ መዝጋቷ የሚታወስ ነው። ይህም ብዙ ውዝግቦችን እያስነሳ ቢሆንም፣ እስከ ውሳኔው ጊዜ ድረስ ከዚህ የተሻለ አማራጭ አልተገኘም። በዚህም ታድያ ብዙ የእግር ኳስ ቡድኖች የሚከስሩ መሆናቸው ግልጽ ነው። በተለይም ከገንዘብ ጋር በተገናኘ የሚኖሩ ኪሳራዎች ቀላል የሚባሉ አይሆኑም።
ከዛም ውጪ ውድድሩ ሙሉ ለሙሉ መቋረጡና የዓመቱ አሸናፊ እገሌ ነው አለመባሉ፣ የአፍሪካ ሻምፕዮና የሚካሄድ ከሆነ በሊጉ የነጥብ ሰንጠረዥ ቀዳሚ ላይ ያለው ቡድን ይሄዳል ወይስ ምን ይደረጋል የሚለውም አንዱ መነጋገሪያ ጉዳይ ነበር። በአንጻሩ የግብጽ ፕሪምየር ሊግ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ሙሉ ለሙሉ የተሰረዘ ቢሆንም፣ የሊጉ ክለቦች በመስማማት በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ መሪነት ላይ የሚገኝ ቡድን በአፍሪካ መድረክ ይወክለናል በማለት ተስማምተዋል።
የአገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ከቡድኖቹ ጋር ተወያይቶ አል አህሊና አል ሞካዉሎ የተባሉ ቡድኖች በአፍሪካ ሻምፕዮና፣ ፒራሚድና ዛማሌክ ደግሞ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ላይ ይሳተፋሉ ብለዋል። ይሁን እንጂ የአፍሪካ ሻምፕዮናም ሆነ የኮንፌዴሬሽን ውድድሮች መካሄድ አለመካሄድቸው ላይ ገና የተባለ ነገር የለም።
በኢትዮጵያም የእግር ኳስ ቡድን አመራሮች ተመሳሳይ ውይይት ማድረግ ይገባል የሚል አስተያየትን ሲሰጡ ይሰማል። አንዱ ውሳኔ ተያያዥ የሆኑ ጉዳዮችን ስለሚያስነሳና ብዙ ውሳኔን የሚፈልግ ጉዳይም ስለሚከተል፣ ሰፋ ያለ ውይይት ማስፈለጉ ጥርጥር የለውም። ይህ በእንዲህ እንዳለ ታድያ የሚታየው መደጋገፍም ቀላል የሚባል አይደለም።
በቅርቡ የወጣ ዘገባ እንደሚያስረዳው የቡና እግር ኳስ ክለብ አባላት ያልተከፈላቸውን የአንድ ወር ደሞዝ ቡድኑ እንዲይዘውና የኹለተኛውን ወር ደግሞ ግማሹን ብቻ እንዲከፍላቸው መስማማታቸው ይፋ ሆኗል። ከዛም አልፎ ቫይረሱን ለመከላከል በሚደረግ ጥረት የበኩላቸውን በማድረግም እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተስተውሏል።
የፌዴሬሽኖች ፈተና
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ከስፖርት ኮሚሽን ጋር በመሆን 70ኛውን የፊፋን ስብሰባ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ነበር። ይህም አሁን ባለንበት ግንቦት ወር ይካሄዳል የተባለ ነው። በእርግጥ ይኸው ዓለም ዐቀፍ የእግር ኳስ ጉባኤ በቪዲዮ ሊካሄድ መወሰኑ ከሰሞኑ ተሰምቷል። ይህንንም ፌዴሬሽኑ በይፋዊ ድረ ገፁ ላይ አስፍሮታል።
የእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን ታድያ አትሌቴክስ ፌዴሬሽንም ቢሆን ለ2020 የቶክዮ ኦሎምፒክ በዝግጅት ዋዜማ ላይ ነበር። ይሁንና ኦሎምፒኩም ቢሆን ለ2021 ተራዝሟል። በ2021 ራሱ የሚካሄደው ቫይረሱ የጠፋ እንደሆነ እንጂ፣ በዚህ ከቀጠለ ውድድሮ ፈጽሞ ሊሰረዝ ይችላል የሚል ግምት ከወዲሁ እየተሰጠ ነው።
ባሕሩ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዳሉት ከሆነ፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ብዙ ነገር ተቀይሯል። ወረርሽኙም የአመራሩን የዓመቱን እቅድ በሙሉ ነው ያዛባው ብለዋል። የሊግ ውድድሮች በጠቅላላ ታግደዋል። ‹‹ወደ መደበኛ የጊዜ ሰሌዳችን መቼ እንደምንመለስ አናውቅም። በጥቂት ሳምንታት ክረምቱም ይገባል። ሌላ መፍትሄ ካልተገኘ በቀር ሊጉን መጨረስ ከባድ ነው›› ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል።
እንደ ፌዴሬሽኑ ከሆነ የዓመቱ አሸናፊ ማን እንደሆነ ሳይታወቅ፣ ከየዲቪዝዮኑ አላፊና ወዳቂው ሳይለይ ሊጉን ማቆም የመጀመሪያ አማራጭ መሆን የለበትም ነበር። ይሁንና ከዛ ውጪ አማራጭ የተገኘ አይመስልም።
ክለቦች ታድያ ሁኔታው አልቀለላቸውም። ደሞዝ ለመክፈልም እየታገሉ ይገኛሉ። የክለብ ስፖንሰሮችም ቢሆኑ ከገበያ መቀዛቀዝ ጋር ተያይዞ ስምምነት ለመፈራረም ጊዜውን እያራዘሙ በመሆኑ ክለቦች ገንዘብ ማግኛ ምንጫቸው ሁሉ እየነጠፈ ነው። እንዲያም ሆኖ እንደምንም መክፈላቸውን ቀጥለዋል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ፌዴሬሽኑ ካለው ላይ ቀንሶ 500 ሺሕ ብር ቫይረሱን ለመከላከል ለሚደረገው እንቅስቃሴ ድጋፍ አድርጓል። ተጫዋቾችም በቤታቸው ውስጥ ሆነውም እንቅስቃሴ ከማድረግ እንዳይቆጠቡ እያሳሰበም ይገኛል።
የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስጋት ደግሞ ከዚህ ይለያል። ኦሎምፒክን ጨምሮ ሁሉም ዓይነት ውድድሮች በጊዜ ተሰርዘዋል። ከፍተኛ የአትሌቲክስ ሕክምና ባለሞያና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጸረ ዶፒንግ ክፍል ተጠሪ ቅድስት ታደሰ እንደሚሉት፣ ይህ መሆኑ አትሌቶቹን እንዲሁም የአትሌቲክስ አገር የሆነችውን ኢትዮጵያን ይጎዳል። በእነዚህ ውድድሮች አለመሳተፋቸውም አትሌቶችን ብዙ እድል ያሳጣቸዋል። እንቅስቃሴያቸውን እንዲሁም ገቢያቸው ጭምር ይጎዳል።
ውድድሮች ሰውነታቸውን እንዲጠብቁ ያግዛቸው ነበር የሚሉት ቅድስት፣ እንደ አገርም በዓለም ዐቀፍ መድረክ ልንታይ የምችልበትን እድል ነው ያጣነው ብለዋል። ከዛ የሚብሰው ደግሞ አትሌቶች ለቫይረሱ የበለጠ የመጠቃት እድል ያላቸው መሆኑ ነው።
እንደ ዓለማቀፉ የስፖርት ሳይንስ ባለሞያዎች አስተያየት ከሆነ፣ አትሌቶች በውድድርና በከባድ ሥልጠና ውስጥ ከሆኑ ቫይረሱን የመከላከል አቅማቸው ይዳከማል። ቅድስትም በዚህ ላይ ሐሳባቸውን ሲጨምሩ ከመተንፈሻ አካል ጋር ለሚገናኝ በሽታ ተጋላጭ መሆናቸውን ነው ያነሱት። ‹‹አትሌቶቻችን በሩጫ ጽናታቸው ይታወቃሉ። ይህም የመተንፈስ አቅማቸውን እስከ ጥግ እንዲጠቀሙበት የሚያደርግ ነው። በዚህ ምክንያት ነው ቫይረሱ ምን ያህል ሊያጠቃቸው እንደሚችል መረዳት ያለባቸው›› ብለዋል።
የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ታድያ ያለውን የአትሌቶች ትግል እንዲሁም ያለባቸውን ፈተና በመመልከት ዝቅተኛ ተከፋይ ለሆኑ የሥልጠና ቡድን አባላት፣ 4 ሚሊዮን ብር እና አስፈላጊ የተባሉ የሥልጠና ቅሳቁሶችን አሰራጭቷል። ‹‹ሁሉም 211 ብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድኖችና 56 አሠልጣኖች እያንዳንዳቸው 15 ሺሕ ብር ይከፈላሉ። ይህም ለማበረታቻና ባሉበት ጸንተው ራሳቸውንም እየጠበቁ እንዲቆዩ ነው ለማገዛ ነው።›› ብሏል፣ ፌዴሬሽኑ ባወጣው መግለጫ።
ከአዲስ ማለዳ እህት መጽሔት ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው በዐቢይ ወንድይፍራው የተጻፈውን መነሻ በማድረግ ፣ ወቅታዊ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበት የተዘጋጀ
ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012



