የወረርሽኙ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ ተጨማሪ የሕግ ማሻሻያዎች ሊደረጉ ነው

0
626

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ ተጨማሪ የሕግ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል እና መቆጣጠር የሚኒስትሮች ኮሚቴ አስተባባሪ ሴክሬታሪያት ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ።
የሚኒስትሮች ኮሚቴው ግንቦት 20/2012 ያካሄደውን መደበኛ ስብሰባ አስመልክተው ሚኒስትሯ በሰጡት መግለጫ፣ የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱንና አዳዲስ ባሕሪያትም እየተስተዋሉ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በተለይ የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ የሌላቸው እና በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የታወቀ ንክኪ ያላደረጉ ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙ መሆኑ አሳሳቢ መሆኑን ኮሚቴው ተመልክቷል ብለዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ሰዎች ጎላ ያለ የቫይረሱ ምልክት ሳያሳዩ በምርመራ ቫይረሱ እንዳለባቸው በመታወቁ ስርጭቱን ይበልጥ አሳሳቢ እንዳደረገው ኮሚቴው መገምገሙን ገልጸዋል።
ከአዲስ አበባ ጋር ተያይዞ ያለውን የወረርሽኝ ስርጭት ለመግታት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፣ ተጨማሪ ግብረ ኃይል በማቋቋም ባለፉት ቀናት በርካታ የዝግጅት ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን፣ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችሉ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ ብለዋል።
በተፈጠረው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱንና ቤሩት የሚገኙ 669 ዜጎቻችንን ለመቀበል ዝግጅት መጠናቀቁንም አመልክተዋል። ግንቦት 20/2012 ላይ 336 ዜጎች ወደ አገራቸው መግባታቸውንና፣ በዛሬው እለት (ቅዳሜ ግንቦት 22/2012) ደግሞ 333 ዜጎች ወደ አገራችን እንደሚገቡ ተገልጿል።
ከዚህ ቀደም መንግሥት በገባው ቃል መሠረት በቀጣይም በችግር ውስጥ ያሉ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ዜጎችን የመመለሱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሚኒስትሯ አመልክተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here