የረመዳን ጾም ለእስልምና እምነት ተከታዮች ታላቅ የጾም ወር ነው። ስለምን ቢባል የረመዳን ትሩፋት ብዙ በመሆኑ ነው፣ እንደ ሃይማኖቱ አባቶች ገለጻ። የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼሕ አሊ መሐመድ ሺፋ የጾሙ መጀመሪያ ላይ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ ይህን አንስተው ነበር። እንዲህም አሉ፣
‹‹አላህ እንዲህ ብሏል፤ ‹አማኞች ሆይ! እናንተ ያመናችሁ ሆይ! የረመዳን ጾም ግዴታ ተደርጓል። ከእናንተ በፊት በነበሩ ሰዎች ላይ ግዴታ እንደተደረገ ሁሉ፣ በእናንተም ላይ ግዴታ አድርገናል።› ከእኛ በፊት የነበሩ እነ ነብዩ ኢሳና ሌሎች ብዙ ነብያቶች ናቸው። በእነርሱ ሁሉ ላይ ግዴታ ተደርጓል። አጿጿሙ ግን ይለያያል። የእኛ 30 ቀን ወይም 29 ቀን ነው። ይህም በጨረቃ አቆጣጠር ነው።››
የረመዳን ወር ድሆች የሚጠየቁበት፣ የድሆች ቤት የሚሞላበት ወር ነው። እንደ ሼሕ አሊ ገለጻ፣ በተለይ ያላቸው [ሀብት] ሰዎች እጅግ በጣም ብዙ ትርፍ የሚያተርፉበት ወር ነው። ትርፍ ሲባል ታድያ ከሞት በኋላ የሚገኝ ትርፍ ነው እንጂ በስጋዊ ሕይወት ብቻ አይደለም። ግን በስጋዊ ሕይወትም ቢሆን ሠርተው ያገኙት በረከት እንዲኖረው ይሆንላቸዋል።
በረመዳን ወር የጀነት በሮች ይከፈታሉ። ስምንት ገነቶች አሉ፣ እናም የእነርሱ ሁሉ በር ክፍት ይሆናል። በአንጻሩ ገሃነም የሚባሉት ሰባቱ ይዘጋሉ። በሥነ ፍጥረት የመጀመሪያ የሆኑት ሰዎች፣ አዳምን እና ሔዋንን ያሳሳተው ዲያቢሎስ ይታሰራል። እሱ ታሰረ ማለት ደግሞ አጠቃላይ የእርሱ ቡድኖችና አጫፋሪዎች አብረው ወደ እስር ቤት ይገባሉ። ይህም ረመዳን እስከሚያልቅ ድረስ ነው።
ለዛም ነው፣ ሼሕ አሊ እንደሚሉት፣ በእስልምና እምነት ውስጥ ያሉ ሰዎች፣ ሌላውም እምነት ተከታይ በዚህ የረመዳን ወር ጥሩ መንፈስ የሚታይባቸው።
የእስልምና መሠረት የሆነው ቅዱስ ቁርዓን የወረደው በረመዳን ወር ነው። በጨረቃ ቀን አቆጣጠር ዘጠነኛ ወር ላይ የሚውለው የረመዳን ወር። በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶችም ታድያ ረመዳን በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ የወራት ሁሉ ቁንጮ ተደርጎ ይታሰባል።
በተያያዘ በእስልምና እምነት ተከታዩ ዘንድ የረመዳን ወር በዓመተ ሒጅራ ካሉት ወራት መካከል ዘጠነኛው ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የተቀደሰ ወር የሚያሰኘው ሙሉውን የጾም ወር በመሆኑ ነው። ቀጣዩ ዐሥረኛ ወር ሸዋል ሲጀምር ነው የኢድ አልፈጥር በዓል የሚውለው። እንግዲህ ይህን ያህል ክብደት ከሚሰጠው፣ ታላቅ ከሚባለው የረመዳን ወር ማብቂያና የኢድ አልፈጥርን በዓል ተከትሎ ነው ሸዋል ኢድ፣ ትንሿ ኢድ የምትመጣው። በዐስረኛው ወር፣ በሸዋል ወር መግቢያ።
ሸዋል በሃይማኖታዊ አስተምህሮው
‹ኢድ› ደስታ ማለት ነው። ደስታ ደግሞ ምሉዕና ሙሉ የሚሆነው ለብቻ ሳይሆን ከወዳጅ ዘመድ፣ ከቤተሰብ ከጎረቤት ተሰባስበው ሲገናኙበት ነው። የ2012 ኢድ አልፈጥር በዓል ግን በዛ መልክ እንዳይከበር የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽ ክፉ ጥላውን አጥልቷል። ይህ ታድያ በኢድ አልፈጥር በዓል ብቻ ሳይሆን በሸዋል ኢድም የሚሆን ነው።
ሀረር እንደወትሮዋ ቢሆን ሸዋል ኢድን ለማክበር ዛሬ መሰናዶዋን ጨርሳለች፣ እንግዶቿንም ተቀብላለች። ዘንድሮ ግን በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ያ ሳይሆን ቀርቷል። አካላዊ መራራቅን ለመጠበቅና ወረርሽኙን ለመከላከል ሲባልም የኢድ አልፈጥር በዓልም ምዕመኑ በየቤቱ ምስጋናውን እንዲያደርስ፣ በየቤቱም እንዲሰግድ መታዘዙ የሚዘነጋ አይደለም።
ወዲህ ወደ ሸዋል እንመለስ። በረመዳን የጾም ወር ማብቂያ ላይ ተጨማሪ ስድስት የጾም ቀናት ያሉ ሲሆን፣ የእነዚህን ቀናት መጠናቀቅ ተከትሎ ነው የሸዋል ኢድ በዓል የሚከበረው። ይህ ይልቁንም በሐረሪ በድምቀት የሚከበር ነው። ዘንድሮም እሁድ እለት የዋለውን የረመዳን ጾም ማብቂያ የኢድ አልፈጥር በዓልን ተከትሎ በማግስቱ የጀመረው የሸዋል ጾም፣ ነገ እሁድ (ግንቦት 23/2012) ይጠናቀቃል።
ይህ በዓል ከሃይማኖታዊ ይልቅ ባህላዊ ትርክትና ስርዓቱ እንደሚያመዝን የሃይማኖቱ አዋቂዎች ይናገራሉ። በደቡብ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ መሐመድ ሙስጠፋ ሃይማኖታዊ መሠረቱን በሚመለከት እንዲህ አሉ። ‹‹ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የረመዳን 30 ቀን ጾም ሲያበቃ 6 ቀን ሸዋልን የጾመ ዓመቱን ሙሉ እንደጾመ ይቆጠርለታል ብለዋል።››
እንዲህ ነው፤ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ሰው መልካም ሥራ ሲሠራ፣ በአላህ ዘንድ በዐስር ይባዛል ተብሎ ይታመናል። ስለዚህ በዓመት 360 ቀናት አሉና፣ 30 ቀናት የረመዳን ጾም እንደ 300 ቀን፣ 6 ቀኑ ደግሞ እንደ 60 ይታሰባል። ‹ዓመቱን ሙሉ እንደጾመ ይቆጠርለታል› የሚለውን ከዚህ የተነሳ ነው።
ኡስታዝ መሐመድ አክለው እንዲህ አሉ፤ ‹‹ስለዚህ ሕዝበ ሙለስሊሙ ሸዋልን ይጾማል። የረመዳን ጾም ውስጣዊ የእምነት ጥንካሬ ስለሚገኝበት፣ ያ የተገኘው ጥንካሬ ሳይዳከም በጀመርንበት እንድጨርስ ሲባል ነው በኢድ ማግስት የሚጀመረው። ስርዓቱ የሚለው ከወሩ [የሸዋል ወር] ሙሉ ስድስት ቀን ጹሙ ነው።››
የበዓል አከባበር ስርዓቱ በጋራ መሰባሰብና መጨፈር፣ ስጦታ መሰጣጠትን የመሰለ ክዋኔን የሚያካትት ሲሆን፣ እንደ ኡስታዝ መሐመድ ገለጻ፣ ይህ በባህል ተለምዶ የሚካሄድ እንጂ በሃይማኖት ስርዓት መደገፊያ ያለው አይደለም።
ሸዋል ኢድ ስድስት ቀናትን ተከትሎ ለመከበሩ ሌላም አመክንዩ ይታከላል። ይህም በእስልምና አስተምህሮ ሴቶች በረመዳን ጾም ወቅት የወር አበባ በሚያዩባቸው ቀናት ጾሙን ስለሚያቋርጡ ያጎድሉትን የጾም ቀናት ለማካካስ እንዲችሉ ለማድረግ ነው የሚል ነው። ወንዶችም ታድያ ተጨማሪ ትሩፋት ለማግኘት ጾሙን አብረው ይጾማሉ።
የበዓሉ አከባበር
የሀረሪ ሕዝብ ክልላዊ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ድረ ገጹ ስለበዓሉ አከባበርና ስላሉ ባህላዊ ክዋኔዎች የተወሰኑ መረጃዎችን አካፍሏል። በዛም ላይ የሸዋል ኢድ በዓል ወጣቶች በይበልጥ የሚግባቡበትና የሚተጫጬበት እንደሆነ፣ ይልቁንም የሀረር ልጆች ደግሞ ባህልና አኗኗራቸውን የሚያንጸብርቁበት አጋጣሚ እንደሆነ ተጠቅሷል። ይህ የሆነው በዓሉ በሀረር ከተማ በድምቀትም ስለሚከበር ሲሆን፣ ‹‹የሀረሪ ብሔር ባህላዊ ኢድ› የሚሉትም አሉ።
ሀረር የሸዋል ኢድን በውብ አልባሳት፣ በዝኪርና ደባል (ጭፈራ) በተለየ ሁኔታ የምታከብር ሲሆን፣ ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር በጋራ በመሰባሰብ እንደሚከበር ተጠቅሷል። ‹‹አከባበሩ በታወቁ ሕዝባዊ መድረኮች በሸዋል ዝክር፣ ቆምታ በሌላው 24 ሰዓት ለሦስት ቀናት ይከበራል። ሕዝብ በከፍተኛ ቁጥርና ማራኪ ባህላዊ ቀለም አልባሳት ይደምቃል።›› እንደ ጽሕፈት ቤቱ ገለጻ።
ባለኅብረ ቀለሟና ውቧ ሀረር ክዋኔውን ለማየት የሚጎበኟትን ጎረቤቶቿን ስለምትቀበል፣ ብዙ ተመልካቾች ከተማዋን ያደምቋታል።
የበዓሉ አከባበር የሚጀምረው ከዋናው በዓል ኹለት ቀን ቀደም ብሎ ነው። በዚህም ዝክሪ ወይም መንዙማ ፈጣሪን በማወደስና በማመስገን ይቀርብበታል። ከላይ እንደተጠቀሰው በ24 ሰዓት ውስጥ በሚኖረው የአከባበር ስርዓትም በዓሉን ለማክበር ለተሰባሰቡ ሰዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ይስተናገዳሉ። በመስተንግዶውም ከሚቀርቡ ባህላዊ ምግብና መጠጦች መካከል ቀይ ወጥ የተዘጋጀ ፍትፍት (አቅሌል) እና ሐሸር ቃዋ (ከወተት ጋር የተፈላ ትኩስ የቡና ገለፈት)፣ ቁጢ ቃሃዋ (ደርቆ የታመሰ የቡና ቅጠል እንደ ሻይ ፈልቶና ከወተት ጋር ተቀላቅሎ)፣ ቡን ቀህዋ (ቡና በወተት) የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ።
ሪፖርተር ጋዜጣ በ2011 ረመዳን እና ሸዋል ኢድን በሚመለከት ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያለውን ጽሑፍ አስነብቧል። በዚህም ጽሑፍ ሸዋል ኢድ በዓል አከባበርን በሚመለከት ካሉ ክዋኔዎች መካከል ዝክሪ ወይም መንዙማን በሚመለከት ሰፋ ያለ ማብራሪያን እንደሚከተለው አስፍሯል።
‹‹እንደ ሀረሪዎች አገላለጽ ዚክሪ በምስጋና መዝሙሮች የተሞላ አላህ፣ ነቢዩ መሐመድና ቅዱሳን የሚመሰገኑበት የጸሎት ሥነ ስርዓት ነው። ቃሉም የምስጋና መዝሙሩ ወይም መንዙማ የሚል መጠሪያ ሆኖም ያገለግላል ይላል። የዚክሪ ክዋኔ በግጥም፣ በዜማ የሚያወጡ ሸኾች እና ዚክሪውን በሚቀበሉ ታዳሚዎች እየተመራ በድቤ (ከረቡ) እና ከእንጨት የተሠሩ ማጨብጨቢያዎች (ከበል) የሚታጀብ ነው። ተሳታፊዎች እየተነሱ ክብ ሠርተው በመጨፈር ያደምቁታል።
ዚክር የተለያየ ቋሚ የሆነ ዜማ ያለው እና በቅዱስ ቁርዓን ውስጥ የተጻፉ የምስጋና ግጥሞች የሚዜሙበት ቢሆንም፣ አንዳንድ ጊዜ ከማኅበረሰቡ ሕይወት ጋር የተያያዙ ተጨማሪ ሐሳቦች ሊካተቱበት ይችላል። ይህ ክዋኔ በዋናነት የሚቀርበው በዓረብኛ ሲሆን አልፎ አልፎም በሀረሪ፣ አማርኛ፣ ኦሮምኛና ሌሎች ቋንቋዎች የተደረሱ ዚክሪዎች ሊገቡ ይችላሉ።
ዚክሪ በሚደረግበት ወቅት ጫት እየተቃመ፣ ሻይ፣ ቡና እንዲሁም ከቡና ቅጠልና ሐሸር ቀሕዋ የሚዘጋጁ ባህላዊ ትኩስ መጠጦች እየተጠጡ ክዋኔው ለረጅም ሰዓት ይደረጋል።
ዚክሪ በአብዛኛው ከመውሊድ ጋር አብሮ በጸሎት ወቅት፣ በበዓላትና ማኅበራዊ አጋጣሚዎች በሚኖሩበት የሚከወን ቢሆንም ለብቻው የሚዜምባቸው ጊዜያት አሉ። ከዚህ በተጨማሪም ለተለዩ ሁኔታዎች በተለየ መልክ የሚደረጉ የዚክሪ አይነቶች አሉ።››
መተጫጫ
በዓሉን አንድም ባህላዊ ይዘት እንዲኖረው ያደረገው ይህ የመተጫጫ ስርዓት መኖሩ ነው። በክርስትናው ጥምቀትን መሠረት ያደረጉ ማኅበራዊ ትስስሮች እንደሚከተሉ ሁሉ፣ በእስልምናው ሸዋል ኢድን ተከትለው እነዚሁ ማኅበራዊ ክዋኔዎች ይታያሉ። የሀረሪ ክልል የሕዝብ ግንኙነት ቢሮ በገጹ ይህን አስፍሯል፤ ‹‹በዓሉን ባህላዊ የሚያደርገው ጉዳይ ወጣቱ ወጣቷ ላይ ዐይኑን የሚጥልባት፣ ወደ ክቡር ጋብቻ የሚጓዝበት የወርቃማ ጉዞ የመጀመሪያ እርምጃ አጋጣሚ ስለሚሆን ነው። በዚህም ሸዋል ኢድ ይበልጥ ውበቱ ይደምቃል። የሀረሪ ወጣት ከሌሎች በአላት ይበልጥ ሸዋል ኢድ ይስበዋል። የሕይወት ጓደኛ ፍለጋ ሂደትም በዓሉን ሞቅ ደመቅ ያደርገዋል።››
የሸዋል ኢድ አከባበር እየተቀዛቀዘ መሄድ እንደሚስተዋልበት በተለያየ ጊዜ የተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ሲያነሱ ተሰምቷል። ነገር ግን ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የሕይወት አጋርን ወይም እጮኛን የመምረጥ ባህሉ ግን እንዳልቆመ ነው የሚነሳው። እናም ታድያ ለመታጨት የደረሱ ልጃገረዶች በዓሉን ተከትሎ በሚኖሩ ሦስት ተከታታይ ቀናት ሥራ አይኖራቸውም። የገንዘብ መዋጮ በማድረግም ድግስ ያዘጋጃሉ። በየቤታቸው እየዞሩም ያዘጋጁትን በመመገብ እንዲሁም በመጨፈር ነው በዓሉን የሚያከብሩት።
ታድያ የበዓሉን ማኅበራዊ ፋይዳ ላጤነ፣ ከሀረር ውጪ የሚኖሩ የሀረር ልጆች እንዲሰባሰቡ ምክንያት መሆኑን ሳያነሳ አያልፍም። በዓሉ በድሬዳዋ እንዲሁም በአዲስ አበባም የሚከበር ሲሆን፣ የሀረር ተወላጆች እንዲሰባሰቡም አንድ አውድ ሆኖ አገልግሏቸዋል።
ተጓዡ ጋዜጠኛ ሔኖክ ስዩም በድሬ ትዩብ ያስነበበው አንድ ጽሑፍም ይህን የሸዋል ኢድ በዓል ያነሳልና እናውሳው። ሔኖክ በዚህ ‹ዛሬ ሸዋል ኢድ ነው› የሚል ርዕስ በሰጠው ጽሑፍ፣ ሸዋል ኢድ በኢትዮጵያ በመስቃን ጉራጌ ስልጤዎችና ሀረሪዎች በስፋት የሚያከብሩት በዓል መሆኑን አንስቷል። ‹‹ትልቁን ኢድ የማትጋፋ፣ በሥሟም በተግባሯም ያነሰች፤ ግና በአገራችን ልዩ ቦታ የሚሰጣት ሸዋል ኢድ፣ ትንሿ ኢድ ብትሆንም በድምቀት ትከበራለች። ዝግጅት ተደርጎ በብዙ ባህላዊ እሴቶች የምትደምቅ ቀን ናት።›› ይላል።
ታድያ በተለያዩ አካባቢዎች ያለውን ልዩነትም ጠቅሶ፣ ሸዋል ኢድ በስልጤዎች ዘንድ ትዳር የያዙ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ቤተሰቦቻቸውን የሚጠይቁበት ቀን ነው። ወለኔዎች ደግሞ የኢድ ማግስት ጾም ስለሆነ ኢድ አልፈጥርን ብዙ አይዘጋጁበትምና ከስድስቱ ቀናት ጾም ፍቺ በኋላ የምትመጣው የሸዋል ኢድ ሰፊ ዝግጅት ይደረግባታል ይላል።
በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት ስለማስመዝገብ
አዲስ ማለዳ በአንደበት ገጿ በእንግድነት ካስተናገደቻቸው አንጋፋና ብርቱ ግለሰቦች መካከል ገዛኸኝ ግርማ አንዱ ናቸው። እኚህ ሰው የማይዳሰሱ ቅርሶችን በማስመዝገብ በኩል ከገዳ ስርዓት ጀምሮ፣ ከኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በፊት፣ መጨረሻ ላይ እስከተመዘገበው የጥምቀት በዓል ድረስ በሁሉም ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ነበራቸው።
ታድያ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ ከተነሳላቸው ጥያቄ አንዱ ቀጣይ የቤት ሥራ ምንድን ነው የሚል ነበር። እርሳቸውም ሻደይ፣ አሸንድዬና አሸንዳን ለማስመዝገብ የሚያስችል ሰነድ ባለፈው ዓመት መጋቢት 2011 ላይ መላኩን አስታውሰው፣ ሰነዱ ላይ መሟላት አለበት የሚለውን ዩኔስኮ አስተያየት በ2012 እንደሚሰጥ ጠቅሰው ነበር።
አያይዘውም ታድያ በ2012 የሐረሪ ብሔር የሸዋል ኢድን በዓል አከባበር ለማስመዝገብ ጥረትና ሥራ መጀመሩን አንስተዋል። ‹‹እስከ አሁን የክርስትናው ላይ ነው የሠራነው፤ አሁን የሙስሊሙን እንይ በሚል እንዲሁም ከእነርሱም ጥያቄ ይቀርብልን ስለነበር፤ ያንን ተመልክተን ቅርሱን ለማስመዝገብ የማስመረጫ ሰነድ መረጃ የማሰባሰብ ሥራ እየሠራን ነው።›› ብለዋል።
የሸዋል ወር የስድስት ቀን ጾም ሌላውም አካባቢ እንደሚጾም ያነሱት ገዛኸኝ፣ ግን በዓሉ ሀረር ላይ እንደሚከበረው አይደለም ብለዋል። አያይዘውም፣ ‹‹ይህን ከሌሎች የሀረር እሴቶች ጋር አድርገን ለማስመዝገብ ነው። አሁን በቀጣይ ሥራዬ ሸዋል ኢድ ነው። አንድ ባልደረባዬም አለች፤ እንደ አዲስ ልምድ ለማካፈልም ከእርሷ ጋር ነው የሄድነው።›› ብለዋል።
የሀረሪ ሕዝብ ክልላዊ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ይህን በሚመለከት በድረ ገጹ ካነበባቸው ዜናዎች መካከልም ይኸው የሹዋል ኢድ የአከባበር ሥነስርዓት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም ዩኔስኮ ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ መጀመሩን ነው። ይህንኑ በተጨማሪ ያስታወቀው የሀረሪ ክልል ባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ፣ የእስልምና እምነት ጋር ተያያዥ የሆነው ይህ የሸዋል በዓል ከ1999 ጀምሮ በክልል ደረጃ በክልላዊ በዓልነት መከበር እንደጀመረም መግለጻቸውም ተጠቅሷል።
በእርግጥ አሁን ላይ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት አካሄዱ እንደሚዘገይ ግልጽ ነው። ይሁንና ይህም ጊዜ ማለፉ ስለማይቀር ሐሳብን ከዛም ላይ ሳያነሱ ጊዜን መጠበቅ አስፈላጊ ነው። ሃይማኖትን መሠረት ቢያደርጉም ማኅበራዊ ትስስሮችን የሚያጠብቁ እነዚህ ክዋኔዎች፣ የበለጠ ለእነዚህ የማይዳሰሱ ሀብቶች ዋጋ የሚያሰጧቸው መሆኑ ጥርጥር የለውም።
ባሳለፍነው ዓመት (2011) ታድያ በአዲስ አበባ የሚገኙ የሀረር ተወላጆች በዓሉን በአዲስ አበባ በድምቀት አክብረውት እንደነበር ይታወሳል። በእለቱ ታድያ በክብር እንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ዑማ ሲናገሩ፣ ‹‹ሀረር ከተማ ወስጥ ያለውን ውበትና ታሪክ በዋና ከተማችን ካልደገምን ታሪኩ የአንድ ወገን ብቻ ይሆናል፤ ግን ታሪኩ የሀረር ታሪክ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ነው። በዋና ከተማችን ይህን ስናመጣ የበለጠ ድምቀት፣ ውበት እንዲሁም ለቱሪዝም ገቢ ይሆናል። የማንነታችን መገለጫና ማሳያም ነው።›› ብለው ነበር።
ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012



