በአሶሳ ኮሮናን ለመከላከል ተጨማሪ መናኸሪያና የግብይት ቦታዎች ተዘጋጁ

0
653

በአሶሳ ከተማ ኮሮናን በመከላከሉ ሂደት የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት ተጨማሪ መናኸሪያና የገበያ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ።
የከተማ አስተዳዳሩ ከንቲባ ዑመር መሐመድ እንደገለፁት፣ አስተዳዳሩ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በትኩረት እየሠራ ነው። ይሁንና አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ረገድ ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ ተደጋጋሚ ትምህርት ቢሰጥም የሚፈለገውን ያክል ለውጥ አልመጣም ብለዋል።
ከዛም በተጨማሪ ችግሩን ካሰፉት እና የኅብረተሰቡ ቸልተኝነት ከበዛባቸው ቦታዎች በግብይት፣ በአገልግሎት መስጫ፣ በትራንስፖርትና መሰል ቦታዎች እንደሚጠቀሱ አስረድተዋል። በከተማዋ ችግሩን ለመቅረፍ ከፍተኛ ሕዝብ ሲያስተናግድ ከነበረው ብቸኛው የከተማ አውቶቡስ መናኸሪያ በተጨማሪ የመለስተኛ አገር አቋራጭ ጊዜያዊ መናኸሪያ ማዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
የኅብረተሰቡን አሰፋፈር፣ የትራንስፖርትና ሌሎችንም መሠረታዊ አገልግሎቶችን ባማከሉ ቦታዎች ሦስት ጊዜያዊ የግብይት ሥፍራዎች ተዘጋጅተው የፊታችን ቅዳሜ ሥራ ይጀምራሉ ተብሏል።
ሁኔታዎች በዚህ መልኩ ከተመቻቹ ቀጣዩ የአስተዳደሩ ሥራ አዋጁን በሚገባ ማስተግበር ነው ያሉት ዑመር፣ ከዚህ በኋላ በተለይም አካላዊ ርቀትን በማይጠብቁ ሰዎች ላይ ተገቢው እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here