የዘንድሮ ግንቦት 20 በዓል ‘‘ሲዘከር’’

0
856

የዘንድሮው 29ኛ ዓመት የግንቦት 20 በዓል ብዙዎችን ከግራ ከቀኝ ሲያነጋግር እና ሲያወዛግብ ነበር ያለፈው፤ ንትረኩ አሁንም ቀጥሏል። የተቃርኖ አመለካከቶች በዕለቱ ዙሪያ ቢስተናገዱም በአመዛኙ ግን የግንቦት 20 በዓል ውግዘትን ማጠንጠኛ ያደረጉ አመለካከቶች መደበኛ መገናኛ ብዙኀንም ሆኑ ማኅበራዊ ትስስር መድረኮችን አጨናንቀው ከርመዋል።

ሕወሓት በዋዜማው ‘‘ኢትዮጵያ ዳግም የብሔርና ብሔረሰቦች እስር ቤት ፈጽሞ አትሆንም!! ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በማንም ምድራዊ ኀይል አይነጠቅም!!’’በሚል ርዕስ ባወጣችው ዘለግ ያለ መግለጫ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ግንቦት 20’ን የሚያከብሩት የወታደራዊ ፋሽስታዊ ደርግ አፍኝ ስርዓትን ላይመለስ ቀብረው በአራቱም የአገሪቱ አቅጣጫዎች የአርነት ችቦ አውለብልበዋል፤ የአገሪቱ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤቶች መሆናቸውን እና ቀጣይ የሕዳሴ ጉዞ ያወጁበት ቀን በመሆኑ ሁሌም በጉጉት ይጠብቁታል ስትል በአንክሮ ገልጻለች።

ይህንን የሕወሓት መግለጫ ያጠናከሩት የቀድሞው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ስዩም መስፍን በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው ዕለቱን በማስመልከት ተናገሩ የተባለው የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። ‘‘እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በየቤቱ በግንቦት 20 ፍቅር እየተቃጠለ ነው’’ ያሉት ስዩም በሥልጣን ኮርቻ ላይ የነበሩ ዘራፊዎች መኖራቸውን በመጠቆም በዓሉንም ምክንያት በማድረግ ሀብታቸውን ማስመዝገብ እንደሚፈልጉና በተመሳሳይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ይመዝገብልኝ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። በማኅበራዊ ትስስር ገፆች የስዩምን ጥሪ በቁም ነገር የወሰዱትን ያክል አንዳንዶች ደግሞ ተሳልቀውበታል፤ ‘‘ለምን ይህንን አሁን ሆነ?’’ ሲሉም ጥርጣሬያቸውን በጥያቄ ያስቀመጡም አልጠፉም።

ሌሎች የግንቦት 20 በዓል ደጋፊዎች ደግሞ ውለታን መዘንጋት አይገባም፤ ተወደደም ተጠላ ግንቦት 20 የታሪካችን አንዱ አካል እንዚህ በተቀዛቀዘ መልኩ ሳይሆን ሞቅ ደመቅ ባለና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መከበር ይገባዋል ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው በፌስቡክ ገጻቸው ላይ በዋዜማው ባስነበቡት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ግንቦት 20’ን ማክበር ያለብን በቀኑ ላይ ተቸክለን ሳይሆን ወደ ፊት እየሔድን የኋላውን እየገመገምን መሆን አለበት ብለዋል። ግንቦት 20 ግንቦት 19’ን መመለስ አልነበረም ያሉት ዐቢይ አገራችንን በሁሉም መመዘኛ ግንቦት 20’ን አልፋ፣ ግንቦት 21’ን ተሸግራ ፣ ወደ ግንቦት 22’ን መድረስ ነበር በማለት ቁጭታቸውን ያስነበቡት ዐቢይ ‘‘የግንቦት 20 ታጋዮችን ዓላማ የምናሳካው በሁለመናዋ ከግንቦት 19 የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት ከቻልን ብቻ ነው’’ ሲሉ ደምድመዋል።

በመንግሥታዊዎቹ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የቀረቡት በተለይ የጋምቤላ፣ የአፋር፣ የሶማሌ እና የቤኔሳንጉል ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች በበኩላቸው ግንቦት 20 የታለመለትን ግብ አልመታም ያሉ ሲሆን በተለይ የብሔር ብሔረሰቦች የራስን በራስ የማስተዳደር መብት ወደ ጎን በመተው በምስለኔዎች ተተክቷል፤ የአንድን ብሔር የበላይነት ለማንበርም በብርቱ ተሰርቷል ሲሉ የ27 ዓመታቱን የግንቦት 20 በዓላት ተችተዋል። ይሁንና ርዕሳነ መስተዳድሮቹ ከኹለት ዓመት በፊት የተፈጠረው ለውጥ ግን ተስፋ ሰጪ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ብርቱ የግንቦት 20 በዓል ተቃዋሚዎች ቀኑን ‘‘ጥቁር ቀን’’ ሲሉት ከአንድ አምባገነን ወደ ሌላ የከፋ ስርዓት የተሸጋገርንበት ነው በማለት ከእንዲህ ወዲህ ሊከበር አይገባም ሲሉ ጠንካራ ተቃውሞ አሰምተዋል። ለዘብተኛ ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ቀኑ መከበር ያለበት በድል በዓልነት ሳይሆን ሟችንም ገዳይንም ወንድማማቾች በመሆናቸው ኹለቱንም ወገኖች የሚዘክር ‘‘የመታሰቢያ በዓል’’ በማድረግ ነው የሚል ምክረ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።

ባልተኞች ደግሞ ግንቦት 20 ቀፋፊ ቀን መሆኑን ያረጋገጠልን ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ከኮቪድ 19 ወረርሺኝ ጋር በተያያዘ ባለሦስት አኀዝ ቁጥር 100 ያስመዘገበችበት እና ተጨማሪ የአንድ ሰው ሕይወት የተቀጠፈበት መሆኑ ነው ሲሉ ተሳልቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here