የፌዴራል የከተሞች ሥራ እድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለስጋት የተጋለጡ በድህነት ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍ ለስድስት መቶ ሺህ ሰዎች ከቤታቸው ሆነው ራሳቸውን እንዲመግቡ በማሰብ የሦስት ወር ደሞዝ መክፈሉን አስታወቀ።
ኤጀንሲው በአካባቢ ልማት ላይ ተሰማርተው ክፍያ ያገኙ የነበሩ እና ከድህነት ወለል በታች ያሉ ሰዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ወጥተው መሥራት ባለመቻላቸው፣ ጊዜውን ከቤታቸው በመሆን እንዲያሳልፉ በማሰብና እራሳቸውን እንዲመግቡ ሲል በቤታቸው እንዲቀመጡ ማድረጉን የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቦዘነች ነጋሽ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ኤጀንሲው የከተማ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ላይ በ11 ከተሞች ላይ እየሠራ እንደሚገኝ የገለጹት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ፣ ከድህነት ወለል በታች ያሉ ዜጎች በተለይ በአሁኑ ስዓት ያሉት በ11 ከተሞች ብቻ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።
ከዚህ በተጓዳኝ ኤጀንሲው ‹የኮቪድ-19 ስርጭት ምላሽ ሰጭ ፕሮጀክት› በሚል አዲስ ፕሮጀክት ነድፎ የድጋፍ ሥራውን ወደ 22 ከተሞች ለማሳደግ እቅድ አዘጋጅቶ እንዳጠናቀቀ ተገልጿል።
በዓለም ባንክ ድጋፍ በሚተገበረው በዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ ይሆናሉ የተባሉ ዜጎች በኮቪድ-19 ምክንያት ሥራቸውን ያጡ፣ በእለት ሥራ የተሰማሩ፣ በትንንሽ ንግድ ተሰማርተው የነበሩ እና መንገድ ላይ ቡናና ሻይ የመሳሰሉትን በመሽጥ የሚተዳደሩ ናቸው። እንዲሁም የጎዳና ተዳደሪዎችን፣ ሴተኛ አዳሪዎችንና በልመና የሚተዳደሩ ዜጎችን እንደሚያካትት አቦዘነች አስረድተዋል።
የፕሮጀክቱ እቅድ በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነ የጠቆሙት አቦዘነች፣ ድጋፍ የሚሹት በየከተማ አስተዳደሮች ተለይተው በሚቀጥለው አንድ ወር ውስጥ ክፍያ እንደሚፈጸምላቸው ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በኤጀንሲው የአምስት ዓመት እቅድ መካከል፣ በ2013 በጀት ዓመት የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና እቅድ ዋና ዋና ግቦች እና የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ከ22 ከተሞች ወደ 72 ከተሞች ማፋት እንደሚገኝበት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ ጠቁመዋል።
በመነሻ እቅዱ ላይ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በከተሞች 7 ሚሊዮን የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዷልም ተብሏል። ከዚህም ውስጥ በቀጣይ 2013 በጀት ዓመት የሚፈጠረው የሥራ እድል 1 ሚሊዮን 403 ሺሕ 860 እንዲሆን መነሻ እቅድ ተቀምጧል። ከዚህ ውስጥም 75 በመቶ ወጣቶች እና 50 በመቶ ሴቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ።
ምግብ ዋስትና ፕሮግራምን በተመለከተ እስከ አሁን በ11 ከተሞች ላይ ሲተገበር የቆየ ሲሆን፣ ከመጪው ሐምሌ ወር ጀምሮ ወደ 72 ከተሞች ለማስፋት በቂ ዝግጅት መደረጉ ተገልጿል። በአጠቃላይ በ83 ከተሞች ላይ የሚገኙ 513 ሺሕ 512 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ይጠበቃል። በዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም በመታቀፍ ድጋፍ የሚያገኙ ደግሞ 280 ሺሕ 930 ቤተሰቦች ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ 9 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በየወሩ ለክፍያ ወጪ እንደሚደረግ በአምስት ዓመቱ መነሻ እቅድ ላይ ቀርቧል።
የመነሻ እቅዱ በቀጣይ በየደረጃው እንዲናበብና እንዲዳብር ተደርጎ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል። በጥቅሉ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት በከተሞች 7 ሚሊዮን የሥራ እድል ለመፍጠር የመነሻ እቅድ መቅረቡ ተመላክቷል።
የኤጀንሲው ኃላፊነት ሥራ አጥ ዜጎችን በጥቃቅንና አነስተኛ አደራጅቶ በከተማ ሥራ ፈጠራ ማሰማራት ሲሆን፣ ከድህነት ወለል በታች ያሉ ዜጎችን በልማት በማሳተፍ እንዲሁም በቀጥታ ድጋፍ በማድረግ መደገፍ መሆኑን አቦዘነች ገልጸዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012



