በአማራ ክልል ከአራት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከ2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

0
904

የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ዐስር ወራት ውስጥ ከአራት የኅብረት ሥራ ማኅበራት 32 ሺሕ ኩንታል የተለያዩ የግብርና ምርት ውጤቶችን ወደተለያዩ አገራት በመላክ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።

በዐስር ወራት የተገኘው 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ፣ ካለፈው ዓመት 2011 ተመሳሳይ በጀት ዓመት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር የተያዘው በጀት ዓመት ሊጠናቀቅ ገና ከአንድ ወር በላይ ጊዜ እየቀረው የአንድ ሚሊዮን ዶላር ልዩነት እንዳለው የኤጀንሲው የግብይት ዳይሬክተር ዓለምዘውድ ሥሜው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ኤጀንሲው በባለፈው 2011 በጀት ዓመት 27 ሺሕ ኩንታል ምርት በመላክ በዓመቱ መጨረሻ ከውጭ ግብይት ያገኘው ገቢ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር እንደነበርም አስታውሰዋል።

ኤጀንሲው በበጀት ዓመቱ ከባለፈው ዓመት የተሻለ ገቢ ማግኘት የቻለው በኮቪድ-19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት የምግብ ውጤት የሆኑ ምርቶች ተፈላጊነታቸው በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመምጣቱ ነው። እንዲሁም በክልሉ ያሉ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ከባለፈው ዓመት በተሻለ መጠን ጥራት ያለው ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ በመቻላቸው መሆኑንም ዳይሬክተሩ አክለዋል።

በዐስር ወራት የተገኘው ገቢ በራስ ጋይንት ሁለገብ ገበሬዎች ኀብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒዬን፣ በፀሐይ ሁለገብ ገበሬዎች ኀብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒዬን፣ በአማራ ቡና አምራቾች ኀብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒዬን እና ታቦር ሁለገብ ገበሬዎች ኀብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒዬን አማካኝነት ነው።

በጥቅሉም ከማኅበራቱ ነጭ ቦሎቄ 15 ሺሕ 720 ኩንታል፣ ሰሊጥ 2 ሺሕ 660 ኩንታል እና ቡና 240 ኩንታል፣ በድምር 18 ሺሕ 620 ኩንታል የግብርና ውጤቶች ወደ ተለያዩ የዓለም አገራት ተልከዋል። የተላከባቸው አገራት ቤልጅየም፣ ግሪክ፣ ጀርመን፣ ቻይና፣ አሜሪካ እና ጣልያን ሲሆኑ፣ በዚህም 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ለክልሉ ማስገኘት መቻሉን የኤጀንሲው የግብይት ዳይሬክተር ተናግረዋል።

የዚህ ዓመት አፈጻጸም በክልሉ ከዚህ በፊት ተሳክቶ እንደማያውቅና በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ወደ ውጭ ለመላክ ምቹ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው አፈጻጸሙ ከፍ እንዲል ምክንያት እንደሆነውም ጨምረው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በክልሉ የሚገኙ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የኮቪድ-19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በክልሉ ሊያስከትል የሚችለውን የምግብ እጥረት ለመፍታት ከአምራቾች ምርት እየሰበሰቡ መሆኑን ዓለምዘውድ ገልጸዋል። እስከ አሁን በክልሉ በሁሉም ቦታዎች 787 ሺሕ ኩንታል የግብርና ውጤት ምርት ማለትም ጤፍ፣ ስንዴና በቆሎ የመሳሰሉ ምርቶች መሰብሰቡንም ዓለምዘውድ ጠቁመዋል።

የተሰበሰበው ምርት ከዚህ በፊት ከነበረው የግብይት ሂደት በተለየ ሁኔታ የግብይት ስርዓቱ ለሸማቹ ኅብረተሰብ አጭር በሆነ የግብይት ሰንሰለት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል። ከተሰበሰበው ምርት እስከ አሁን ከ81 ሺሕ በላይ ኩንታል እህል በክልሉ እና ከ12 ሺሕ ኩንታል በላይ እህል ለአዲስ አበባ አጋር ሽማቶች ማሰራጨቱን አንስተዋል።

ኤጀንሲው ለአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ማኅበራት 19 ሺሕ ኩንታል የምግብ እህል ለመሸጥ ውል መግባቱንም ዓለምዘውድ አያይዘው ተናግረዋል።
በክልሉ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከተሞች ዝግ በሚሆኑበት ጊዜ የግብርና ውጤቶችን በተለይም የአትክልት ምርቶቸን በየቤታቸው፣ በዝቅተኛ ዋጋ በቀጥታ ከአምራች ወደ ኅብረት ሥራ ማኅብራት ሲደርሱ አንደነበር ተገልጿል።

አሁን ላይ በከልሉ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እስካሁን ከተሰራጨው ውጭ 281 ሺሕ ኩንታል የተከማቸ ምርት እንዳለም ተነስቷል። ከዚህም ውስጥ ጤፍ 33 ሺሕ እና ስንዴ 61 ሺሕ ኩንታል መሆኑ ተገልጿል።

በኅብረት ሥራ ማኅበራቱ የተከማቸ የበቆሎ ምርት በከፍተኛ ደረጃ የገበያ መዳረሻ በመጥፋቱ፣ የተከማቸው እየተሸጠ እንዳልሆነም ዓለምዘውድ ጠቁመዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here