ወረርሽኙን ለመቋቋም የተሰባሰበውን እርዳታ ጥቅም ላይ ማዋል ሊጀመር ይገባል!

0
332

አዲስ አበባ ከተማ በኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝ መናኸሪያ መሆኗ በዚህ ሳምንት ከመቼውም ይልቅ በጉልህ ተለይቷል። በአገሪቷ እስከ ከትናንት ወዲያ (ሐሙስ ግንቦት 20/2012) ከተያዙት 831 ሰዎች ውስጥ 552 ያህሉ ከአዲስ አበባ ናቸው። ከተማዋ የአገሪቱ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ መዲና መሆኗ ዓለም ዐቀፍ እንቅስቃሴዎች እንዲበዙባት አድርጓል። ይህም በወረርሽኙ መጀመሪያ እንደታየው የውጭ ዜጎች ቫይረሱን ወደ አገር እንዲያስገቡ እድሉን የከፈተ ነው።

ከዚህም ባሻገር ከአራት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ እንዳላት የተለያዩ ምንጮች የሚጠቁሙላት አዲስ አበባ፣ ሰዎች ተጠጋግተው የሚኖሩባቸው ብዙ ቦታዎች አሏት። ለዘመናት በችግርነት ቢነሳም እስከ አሁን እልባት ያላገኘው የቆሻሻነቷ ጉዳይም ለቫይረሱ ስርጭት መጨመር ምቹ ሁኔታ ከሚፈጥሩ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው። ምንም እንኳን በጥናት የተረጋገጠ ባይሆንም ረጅም ጊዜ ሥልጣን ያለውን አካል ያለማመን አዝማሚያ አሁን ለሚታየው የመንግሥትን የጤና ምክር በጥብቅ ለመተግበር ያለመቻል ችግር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይገመታል።

ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ከኹለት ወራት ዘገምተኛ መስፋፋት በኋላ አሁን ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ በአገራችን የሚተላለፍበትን ደረጃ አንድ እርከን ከፍ አድርጓል። ከዚህ በፊት ከውጭ የሚገቡ ሰዎች በዋነኛነት ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሆነው የቆዩ ሲሆን፣ አሁን ይህ እውነታ ተቀይሯል። በቫይረሱ የተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ቁጥርም አሁን አሁን የጉዞ ታሪክም ሆነ ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ከሌላቸው ሰዎች ቁጥር እጅጉን እያነሰ ነው።

ይህንንም ተከትሎ የጤና ሚኒስቴር ባለሥልጣናትም ሆኑ ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት የማኅበረሰብ ውስጥ መስፋፋት (community spread) ደረጃ ላይ እንደደረሰ ገልፀዋል። በዚህ ሳምንት ውስጥ አብነት በሚል ሥያሜ የሚታወቀው ሰፈር አካባቢ የሚወጣም ሆነ የሚገባ ሳይኖር ለ14 ቀን እንዲለይ መደረጉም ይህንን የሚያረጋግጥ ነው። የስርጭቱ መጠንም እጅጉን ጨምሮ በድምሮ አንድ መቶ ለመሙላት ኹለት ወር የፈጀው የታማሚዎች ቁጥር፣ ባሳለፍነው ሳምንት እንደታየው የአንድ ቀን ተያዦች ቁጥር ወደ መሆን ተሸጋግሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሳምንታት በፊት ኮቪድ 19ን ለመከላከል የተቋቋመውን የሚኒስትሮች ኮሚቴ ባናገሩበት ወቅት፣ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ከዐስር ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆዩ እንደተደረገ ገልፀው ነበር። ምንም እንኳን በሚያዝያ 30 ላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 194 የነበረ ቢሆንም፣ ከውጪ የሚመጡ እና ቫይረሱ ከተገኘባቸው ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች በመሆናቸው በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ የተደረጉ ሰዎች ቁጥር የተጠቀሰውን አሃዝ ያህል ነበሩ ማለት ነው።

ከዚያ ወዲህ ባሉት ኻያ ቀናት ብቻ ግን 637 ተጨማሪ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። ይህም ጭማሪ የዚህ ወር መጀመሪያ ድረስ ከተያዘው ሰው ቁጥር ከሦስት እጥፍ በላይ ነው። በተለይ ከውጭ የሚገባው የሰው ቁጥር ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ በፊት ጀምሮ እጅጉን አናሳ ሆኖ የቆየ መሆኑ ግምት ውስጥ ሲገባ፣ በለይቶ ማቆያ እንዲገባ የሚደረገው የሰው ቁጥርም በእጅጉ እንደሚንር መገመት ይቻላል።

የቫይረሱ የመዛመት ኃይል እየጨመረ የመጣ መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ ሲገባ ደግሞ መንግሥት ለ14 ቀናት ለይቶ የሚያቆየው ሰው ቁጥር ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሰዎች መለየት አዳጋች እየሆነ እንደሚሄድ ግልጽ ነው። ለዚህ ተግባር ሊመደብ የሚገባው የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እና የሰው ኃይልም በጣም እየጨመረ ይሄዳል። ይህንን ለማሟላት ኢትዮጵያ ያላት አቅም ደግሞ እንደሚታወቀው ዝቅተኛ ነው።

በዚህ ፈተና ላይ አሁን እያየን እንዳለነው በቀን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እየተያዙ የሚቀጥል ከሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ ደካማው የአገራችን የጤና ስርዓት በማይችለው የታማሚ ቁጥር እንደሚጥለቀለቅ እሙን ነው። ይህም በሌላው ዓለም ስናየው የቆየነውን የወረርሽኙን ገፅታ ወደ አገራችን ያመጣዋል። ይህ ሁኔታም በየቀኑ እየቀረበ መሆኑ እሙን ነው።

በመሆኑም በዓለም ዙሪያ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ፍቱን የሆነ ምላሽ ሆኖ የተገኘውን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የከተማውን ክፍሎች የመዝጋት እርምጃ ሊታሰብበት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ አጽንኦት ትሰጣለች። የእንቅስቃሴ መቀነስ የቫይረሱን መዛመት የሚገድብ በመሆኑ የሚቻለውን ያህል ለመቀነስ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል መዝጋቱ ጥሩ አማራጭ ነው።

በተደጋጋሚ እንደሚሰማው ይህንን ማድረግ እጅግ አዳጋች የሚሆነው የየእለት ጉርሱን ለማግኘት የሚሯሯጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ከተማ ውስጥ መኖሩን ነው። ነገር ግን ቫይረሱ ወደ አገር ገባ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ፌዴራል መንግሥትም ሆነ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር መጠነ ሰፊ ዝግጅቶችን ሲያደርጉ እንደነበር ይታወቃል። እርዳታ ማሰባሰቡም በተለያዩ ደረጃዎች ሲካሄድ ቆይቷል። በአዲስ አበባ አስተዳደር የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ነስረዲን አሕመድ ለአዲስ ማለዳ እንደጠቀሱት፣ በአዲስ አበባ ብቻ 600 ሚሊዮን ብር በገንዘብ እንዲሁም በዓይነት 200 ሚሊዮን ብር የሚገመት እርዳታ ተሰብስቧል።

የከተማው መስተዳድር ከዚህ በፊት 160 የምግብ ባንኮች በሁሉም ክፍለ ከተሞች እንዳቋቋመም አሳውቆ ነበር። ይህም በየክፍለ ከተማው 16 የምግብ ባንክ ማለት ነው። የችግሩን አሳሳቢነት በማየትም በፌዴራል መንግሥትም ሆነ በሌሎች የክልል መንግሥታት እርዳታ፣ ያለውን የምግብ ድጋፍና ክምችት መጨመር ያስፈልጋል።
ነገር ግን በዓለም ዙሪያ እንዳየናቸው አገሮች ችግሩ ከቁጥጥር ውጭ ከመውጣቱ በፊት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ከተማውን ዘግቶ የተሰባሰበው እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የሚሰጥበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል። እየተሰበሰበ ያለው እርዳታ የትኛው የቫይረስ ስርጭት ደረጃ ላይ ሲደረስ ጥቅም ላይ እንደሚውል በግልጽ ስላልተቀመጠ፣ በወረርሽኙ ማኅበረሰባዊ ስርጭት ላይ በቀን መቶዎች የሚያዙበት ሁኔታ ሲመጣ ልንጠቀመው ይገባል ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ጥቅም ላይ በማይውሉበት ሁኔታ የተሰባሰቡት የምግብ እርዳታዎች ሊበላሹ የሚችሉበት አጋጣሚም እየታየ ስለሆነ ይህ ከመሆኑ በፊት ሰዎች በቤታቸው እንዲቆዩ ቢመደብላቸው የተሻለ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ጥቅም ላይ የማይውሉበት ጊዜ እየጨመረ ሲሄድ ደግሞ የሚበላሸው ምግብ መጠን እየጨመረ ስለሚሔድ በየቀበሌው እርዳታው የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች በመለየት ቤታቸው እንዲቆዩ ለማድረግ ጥቅም ላይ ሊውል ይገባል።

መበላሸቱ ብቻ ሳይሆን እርዳታውን ማከፋፈል ባልተጀመረበት ሁኔታ ከአንዳንድ የእርዳታ ማሰባሰቢያ ማእከላት በመኪኖች እየተጫነ እንደሚወጣ ጥቆማዎች ስላሉ፣ ይህንንም መስመር ማስያዝ ከከተማው አስተዳድር የሚጠበቅ ነው። የዜጎችን በሕይወት የመቆየት እድል የሚወስን ሀብት እንዲሁ በቀላሉ እንዲባክን ማድረግ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ጥሩ የሕዝብ ተቀባይነትን እያተረፈ የመጣውን የከተማውን አስተዳድር የሚያሳጣ ነው።

በመሆኑም ወደ ሌላ ደረጃ የተሸጋገረውን የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚደረገው እርምጃ ከወረርሽኙ መጠናከር ጋር አብሮ መጠናከር አለበት። በዚህም መሠረት ወረርሽኙን የመዋጋቱ ሥራ አንድ እርከን ከፍ ብሎ ዜጎች እንቅስቃሴያቸውን የሚገድቡበትን መንገድ የሚያመቻች እና የተሰበሰበው እርዳታ ጥቅም ላይ የሚውልበት ደረጃ ላይ መድረስ ይገባዋል ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። ከዚህም ጋር ተያይዞ እርዳታ የማሰባሰቡ ሒደት ተጠናክሮ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ከሚገኙ ምንጮች አስፈላጊው ምግብ ነክም ሆነ ሌላ ዓይነት እርዳታ እንዲሰባሰብ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here