በአማራ ክልል ከ400 ሺሕ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ ተጠቅተዋል

0
956

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት በክልሉ የሚገኙ 400 ሺሕ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መጠቃታቸውን አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ለአዲስ ማለዳ በሰጠው መረጃ እንደገለጸው፣ በዚህ ዓመት ቁጥራቸው እጅግ የበዛ ሰዎች በወባ ለመጠቃታቸው እና በክልሉ ለተከሰተው የወባ በሽታ ስርጭት መስፋፋት ምክንያቶች ውስጥ በኅብረተሰቡ ዘንድ እንዲሁም በመንግሥት ተቋማት የተፈጠረ ትኩረት ማጣት ነው ሲል አስታውቋል። የኢንስቲትዩቱ የወባ በሽታ የቡድን መሪ ማስተዋል ወርቁ ለአዲስ ማለዳ ሲያስረዱ፣ የተጠቂዎች ቁጥር ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 73 በመቶ መጨመሩን አስታውቀዋል።

በ2011 ተመሳሳይ ወቅት በክልሉ በወባ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 238 ሺሕ እንደነበርና አሁን ላይ ከ400 ሺሕ በላይ ከፍ እንዳለ ከኢንስቲትዩቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በክልሉ ባለፉት አምስት ዓመታት የወባ በሽታ ስርጭት ቀንሶ እንደነበር እና ይህንንም ምክንያት አድርጎ በኅብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋት ተፈጥሮ መቆየቱ፣ ለወባ መከላከያ የተሰጡ ግብአቶችን በአግባቡ አለመጠቀም፣ የኅብረተሰቡ አካባቢን በንቃት የመቆጣጠር ሥራ መዳከም እና ምልክቶች ሲታዩ ወደ ሕክምና ተቋም አለመሄድ ለበሽታው መስፋፋት እንደ ዋና ምክንያት ቀርበዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ከጤና ሚኒስቴር የሚገኙ የሕክምና ግብአቶች እጥረት በመኖሩ በተለይም በአቅርቦት እጥረት ምክንያት የቤት ለቤት ርጭት ሽፋን መዳከሙ፣ የወባ ክትባት ችግርና በኮቪድ-19 መከሰት ለወባ በሽታ የተሰጠው ትኩረት በማነሱና መዘናጋት መፈጠሩ ሌሎች ተጠቃሽ ምክንያት ናቸው። እንዲሁም በክልሉ ያሉ አንዳንድ ጤና ጣቢያዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ወደ ጤና ተቋማት የሚመጣ ሰው (ታካሚ) የለም በሚል ዝግ ሆነው መገኘታቸው፣ የበሽታው ስርጭት እንዲሰፋ አድርጎታል ሲል የክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

የስርጭት መጠናቸው ከሌሎች ቦታዎች በተለየ ሁኔታ የሰፋባቸው 53 ወረዳዎች ተለይተው የቤት ለቤት ኬሚካል እርጭት እየተከናወነ መሆኑን ማስተዋል ጠቁመዋል። የበሽታው ስርጭት ወደፊት ከዚህም በላይ ሊጨምር የሚችልበት ሁኔታ እንደሚኖር የገለጹም ሲሆን፣ በአካባቢው ያለው የአየር ሁኔታ ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ማስተዋል እንዳሉት እስከ አሁን በሰሜን ጎንደር ዞን የኹለት ሰዎች ሕይወት በበሽታው ሲያልፍ፣ በዚህ ዓመት የበሽታው ተጠቂዎች ቁጥር እጅግ ለመጨመሩ ዋነኛ ምክንያቱ ሰፊ ትኩረት የተሰጠው ለኮሮና ቫይረስ በመሆኑ ነው። በገጠሩ የኅብረተሰብ ክፍልም ተዘዋውረን እንዳየነው ስርዓት የጎደለው የአጎበር አጠቃቀም ነው ያለው ሲሉ ገልጸዋል።

ከፌዴራል መንግሥት 260 ሺሕ ኪሎ ግራም የሚሆን ፀረ-ወባ ኬሚካል እንደተመደበ የገለፁት ማስተዋል፣ በአሁኑ ጊዜ ለወባ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ የክልሉ አካባቢዎች በጤና ቢሮ በኩል በተዋቀረ ቡድን የቤት ለቤት ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ካለው የበሽታው ስርጭት አንጻር በክልሉ ለመከላከል የሚረዱ ግብአቶች በቂ አለመሆናቸውን ማስተዋል ጠቅሰዋል። በመሆኑም አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ከጤና ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በየእለቱ እየተነጋገሩ እንደሆነም አክለዋል።

ማስተዋል ኅብረተሰቡ የወባ መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ ራሱን ከበሽታው እንዲከላከል አሳስበዋል።
በክልሉ ከዚህ በፊት የወባ በሽታ ክትባት የሆነውን ሃይድሮኪሎረኪንን ለኮቪድ-19 መድኃኒት ነው በሚል ከመድኃኒት ቤቶች በመግዛት ኅብረተሰቡ እየተጠቀመ መሆኑና ወደፊት በክልሉ የወባ በሽታ ቢከሰት የክትባት መድኃኒት እጥረት ሊጋጥም እንደሚችል አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም መዘገቧ የሚታወስ ነው። ማስተዋልም ክስተቱ አሁን ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩን ተናግረዋል። በመሆኑም የክትባት ግብዓት እጥረት አጋጥሟል ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here