በቦሌ ክፍለ ከተማ የውሃ መስመር ለአርሶ አደር ልጆች ብቻ መዘርጋቱ ቅሬታ አስነሳ

0
881

በቦሌ ከፍለ ከተማ ስር ባሉ ኹለት ወረዳዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች ለአርሶ አደር ልጆች ብቻ የውሃ መስመር ዝርጋታ እየተከናወነ ነው፣ ክፍለ ከተማው በተገቢው መንገድ እያስተናገደን አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን አቀረቡ።

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 እና ወረዳ 01 ነዋሪ የሆኑት ቅሬታ አቅራቢዎች ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ክፍለ ከተማው ጉዳያቸውን ተመልክቶ እልባት እንዲሰጣቸው ተብሎ ከወረዳቸው የድጋፍ ደብዳቤ ለ75 በላይ አባ ወራዎች ቢያስገቡም አለመስተናገዳቸውን ተናግረዋል። አያይዘውም ለ20 ዓመታት በቦታው መኖራቸውን በመጥቀስ፣ በተለያየ መንገድ ካርታ እንዳልተሰጣቸው ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት የውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ክፍለ ከተማው ሊያስተናግዳቸው እንዳልቻለ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ‹‹የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ለሌላቸው እና የአርሶ አደር ልጆች ላልሆኑ ነዋሪዎች ማስገባት አንችልም፣ መመሪያው አይፈቅድም›› በማለት በተደጋጋሚ እየተጉላሉ መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል። ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ከ1997 እስከ 2003 በቦታው ከመቆየት ጋር ተያይዞ በአየር ካርታ ላይ የሚታይ ከሆነ የባለቤትነት ካርታ እንደሚሠራላቸው ሕጉ የሚፈቅድ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ የእነርሱም ይዞታ በአየር ላይ ካርታ ተነስቶ እንደሚታይ እና መመሪያውን እንደሚያሟሉ አስረድተዋል።

ለክፍለ ከተማው ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ‹‹በመመሪያው መሰረት ነው የምንሠራው›› በሚል ወደ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የተመሩ ሲሆን፣ ‹‹ከንቲባ ጽሕፈት ቤቱም መመሪያው አይፈቅድም በማለት ልኮናል። ይሁን እንጂ ግልፅ ባልሆነ መንገድ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እየሆኑ ያሉ ሰዎች እየታዘብን ነው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ ከዚህ ቀደም የውሃ አገልግሎት ሲያገኙ በነበረበት መንገድ ውሃ እንዳያገኙ በኮሮና ቫይረስ ኮቪድ 19 ምክንያት የመጠጥ ውሃ ማግኘት የማይቻልበት ደረጃ ደርሰናል ብለዋል። ‹‹እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ውሃ ከ5 ብር ጀምሮ በመግዛት እንጠቀም ነበር›› የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ ‹‹አሁን ግን እሱንም ተከልክለናል›› ሲሉ አሳውቀዋል።

‹‹ኮሮና ቫይረስ ስርጭቱ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱ እና ክፍለ ከተማው ደግሞ ተገቢውን አገልግሎት ሊሰጠን ባለመቻሉ ከፍተኛ ችግር ላይ እንገኛለን። ንክኪ እና ርቀት እንዲጠበቅ በታዘዘው መሰረት ከዚህ ቀደም ከ5 ብር ጀምሮ ውሃ ገዝተን እንጠቀም የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን ንክኪ እንዳይኖር በሚል ስጋት በግዢም መጠቀም እንዳንችል በመደረጋችን ችግሩን አባብሶብናል።›› ሲሉ ነዋሪዎቹ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ አሰምተዋል።

ከኹለቱ ወረዳዎች የቀረበውን ቅሬታ በሚመለከት ለአዲስ ማለዳ ምላሽ የሰጡት የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጥላሁን ፈቃዱ ‹‹የውሃ አገልግሎቱን የምንሰጠው ሦስት መንገዶችን በመጠቀም ነው›› ሲሉ ይጀምራሉ።

አንደኛው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ሲኖር እና በዛ ካርታ መሰረት ውሃ እንዲገባላቸው ተደርጎ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል። ኹለተኛው ካርታም ባይኖራቸው አርሶ አደር ለሆኑት የእርሻ ግብር ስለሚከፍሉ እነርሱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሲደረግ፣ ሦስተኛው በእንደዚህ አገልግሎቶች መጠቀም ለማይችሉ እና መመርያው ለማይፈቅድላቸው በጋራ እንዲጠቀሙ በሚል (ቦኖ) እንዲገባላቸው የሚደረግብት አሰራር አለ ሲሉ አብራርተዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ ከመመሪያው ውጪ ውሃ እንዲገባ እንደማይደረግ፤ ነገር ግን አንድ ላይ ጥያቄ ቀርቦ ተለይተው የተስተናገዱ ግለሰቦች አሉ የሚባለውን ነገር እንደማያስታውሱት አንስተዋል። ‹‹ምናልባት አርሶ አደር ሆነው ነገር ግን ደረሰኝ ሳይኖራቸው የገባላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። እሱም የሚስተካክል ነገር ነው›› ብለዋል።

አያይዘውም የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ከባድ እና የሚመከር እንዳልሆነ ግን አልካዱም። ነገር ግን ሕጋዊ የሆነ የይዞታ ማረጋገጫ ለሌላቸው እና ከ1997 እስከ 2003 የአየር ካርታ ላይ የማይታይ ሆኖ ሕጋዊ ባልሆነ ሰነድ የውሃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከተደረገ፣ ቦታው የግል ነው የሚል ክርክር ስለሚያመጡ ያንን ለመቀነስ በመታሰቡ ምክንያት አገልግሎቱ ሳይሰጣቸው እንደቀረ የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጥላሁን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here