‹‹የፖሊስ አባላት የእጅ መንሻ እየተቀበሉ እንደሆነ መረጃው አለኝ›› የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን

0
725

ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት በመንግሥት የወጣውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተግባራዊ ለማድረግ በሚንቀሳቀሱ የፖሊስ አባላት መካከል ችግሩን እንደ መልካም አጋጣሚ የሚጠቀሙ ፖሊስ አባላት የእጅ መንሻ (ጉቦ) እንደሚቀበሉ ጥቆማ እንደሚደርሰው እና መረጃውም እንዳለው የአዲስ አበባ ፖሊሲ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፣ ከመጠጥ ቤቶች ጋር በተያያዘ አንዳንድ የፖሊስ አባላት ሕግን በማስከበር ፋንታ ጉቦ እንደሚቀበሉ ከኅብረተሰቡም ጥቆማ እንደሚደርሰው አስታውቋል። ሕጋዊ አሰራርን መተግበርን ወደ ጎን በመተው ጉቦ እንደሚቀበሉ ከኅብረተሰቡ ጥቆማ እየደረሰው እንደሆነ እና ኮሚሽኑም ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድባቸውም ገልጿል።

በሥራ አፈፃፀም ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮች በተወሰኑ ፖሊስ አባላት ዘንድ ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን እነዚህን ችግሮች ከማሳለፍ እና የሕግ ጥሰቱ ተባባሪ ከመሆን በአካባቢያቸው ባለ ክፍለ ከተማም ሆነ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በመምጣት መረጃዎችን መስጠት ይቻላል ብለዋል።

ጉዳዮ በኮሚሽኑ ከታየ በኋላ የዲሲፕሊን ውሳኔ የሚሰጥበት ይሆናልም ብለዋል። የፖሊስ ሥራዎች ሲሠሩ ከሌላው በተለየ መልኩ የሥነ ምግባር ቁጥጥሩ ጠበቅ ያለ መሆኑን እና እጥፊ የሆኑ አባላቶችም በሠራዊቱ ደንብ እና መመርያ መሠረት አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል በማለት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሕዝብ ግንኙነት የሚድያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየት እንዳሳሰቡት፣ ኅብረተሰቡ ከሥነ ምግባር የወጡ የፖሊስ አባላት በሚያጋጥሙት ጊዜ የጤና ጉዳይ እንደመሆኑ ሊደራደር አይገባም ብለዋል። ‹‹እንደዚህ አይነት ችግሮችን ለመልካም አጋጣሚ የሚጠቀሙ ከሥነ ምግባር የወጡ ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ›› ያሉት ዋና ኢንስፔክተሩ፣ ነገር ግን የጉዳቱ መዘዝ ግለሰብን ብቻ ሳይሆን ቤተሰብንም እስከመበተን የሚያደርስ እንደመሆኑ፣ በዋናነት ኅብረተሰቡ ራሱን መጠበቅ እንደሚኖርበትም አሳስበዋል።
እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ፣ ይሄም ቢሆን በሳምንት ውስጥ ከመጠጥ ቤቶች ጋር ከመሰብሰብ ጋር በተያያዘ ግንቦት 16 እና 17/2012 በተደረገ አሰሳ፣ 1 ሺሕ 887 ግለሰቦች ተይዘው አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ እያደረገባቸው ነው።

የኮሮና ቫይረስ ኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። በተለይም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ክልከላ የቀጠለባቸው ጉዳዮች ውስጥ በመጠጥ ቤቶች አካባቢ እና በጣም በርካታ ሰዎች በሚሰበሰቡበት ቦታ ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በመጠጥ ቤቶች፣ በግሮሰሪዎች፣ በጠጅ ቤቶች እስከ ግንቦት 17/2012 በኹለት ቀናት ውስጥ ከተያዙት ውጪ፣ 1 ሺሕ 523 ሰዎች ላይ ሌላ ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝም ታውቋል።

እንደ ኃላፊው ገለፃ ከሆነ ደግሞ 641 የሚሆኑ ሰዎች በተጨማሪ ፍርድ ቤት ቀርበው እየተከታተሉ ሲሆን 74 የሚሆኑ ግለሰቦች ከ15 ቀን እስከ 3 ወር የሚደርስ እስራት ተቀጥተዋል። 556 የሚሆኑ ግለሰቦች ደግሞ እስከ 20 ሺሕ ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል ብለዋል።

በተያያዘም እንደ ዋና ኢንስፔክተር ማርቆስ ገለፃ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጠንካራ ሥራ ላይ በኅብረተሰቡ ውስጥ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ፈቃደኛ ያልሆኑ ግለሰቦች እንዳሉም ገልፀዋል። አክለውም ‹‹የሚሠሩ ሥራዎች ለፖሊስ ተብለው የሚሠሩ እስኪመስል ድረስ ከፖሊስ ጋር ድብብቆሽ ጨዋታ አርገውታል›› ሲሉ ጠቅሰዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መሰረት መደበኛ ሕግን የማስከበር ሥራ ነው እየሠራን የምንገኘው ያሉ ሲሆን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሕግ ሆኖ ወደ ሥራ እንደተገባ እና ፖሊስም ዋና ሥራው ሕግን እንዲከበር ማድረግ እንደመሆኑ መጠን፣ ተከታታይነት ባለው መልኩ እና ሕጉን ተላልፈው ሕገ ወጥ የሆነ ሥራ የሚሠሩት ላይ እርምጃ እየወሰድንም ነው ብለዋል። ኅብረተሰቡ የግንዛቤ እጥረት የለበትም የሚሉት ዋና ኢንስፔክትር ማርቆስ፣ በቸልተኝነት ግን የሚያጠፉ አሉ ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here