በአዲስ አበባ እርዳታ መከፋፈል ያለመጀመሩ ቅሬታ አስነሳ

0
629

በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ክፍለ ከተማዎች የሚገኙ ነዋሪዎች የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ መንግሥት አቅመ ደካማዎችን ለይቶ በመመዝገብ እርዳታ እንዲደርሰን እንደሚያደርግ ተነግሮን እየጠበቅን ቢሆንም ‹‹በእኛ ስም የሚደረገው ድጎማ ደርሶን አያውቅም ›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ቅሬታ አቀረቡ።
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ከሆነ የምግብ ድጋፉ እንዲደርሰን ተመዝግበን እየጠበቅን ቢሆንም፤ ‹‹በአንዳንድ ወረዳዎች ምሽት ላይ አህሎች ሲወጡ እንታዘባለን እኛ ግን ተጠቅመን አናውቅም›› ብለዋል።

የአዲስ አበባ አስተዳደር የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ነስረዲን አሕመድ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት የድጋፍ ማሰባሰብ ሂደቱ በተጠናከረ መልኩ እየተካሄደ ነው። በገንዘብ ስድስት መቶ ሚሊዮን ብር እና በዓይነት ደግሞ ሁለት መቶ ሚሊዮን ብር የሚገመት እርዳታ መሰብሰቡን ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
እርዳታው ይሰብሰብ እንጂ ድጋፍ ፈላጊ ተብለው ወደ ተለዩት የህብረተሰብ ክፍሎች ማከፋፈል እንዳልተጀመረ ነው የገለፁት።

ነስረዲን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት እርዳታውን ማከፋፈል በከተማዋ እንቅስቃሴዎች ይቁሙ ተብሎ ባለመወሰኑ ምክንያት እንዳልተጀመረ ተናግረዋል።
እስካሁን ባለው ሁኔታ የቀን ገቢ ጠብቀው የሚተዳደሩ እና የከተማ እንቅስቃሴ በተወሰነ መንገድ እንዲቀንስ በተደረገው መሰረትም 60 ሺህ ለሚጠጉ አባወራዎች ተለይተው የከፋ ችግር አለባቸው የሚለውን እና በአል ለማክበር አይችሉም ለተባሉ የፋሲካ በአልን እና የረመዳን በአልን ምክንያት በማድረግ ለምግብነት ሊውሉ የሚችሉ እህሎች እንዲደርሳቸው መደረጉን ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዛም በተጨማሪ እርዳታውን ለማከፋፈል የራሱ የሆነ ስርአት አለው፤ የሚሉት ዳይሬክተሩ ህብረተሰቡ ጋር ለመድረስ ዝቅተኛውን የመንግሥት አደረጃጀት በመጠቀም ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ህብረተሰቦች ይደርሳል ብለዋል። ነገር ግን ክፍለ ከተማዎች እራሳቸው የሰበሰቡትንም ምግብ ነክ ድጋፎች ማከፋፈል እየጀመሩ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ራሳቸውን ችለው የሚንቀሳቀሱ 1,357 የምግብ ባንኮች መከፈታቸውን ተናግረዋል። በእነዚህ የምግብ ባንኮች ውስጥም ምግቦች መከማቸት መጀመራቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

450 ሺህ የሚጠጋ የህብረተሰብ ክፍል እንደ ከተማ አስተዳደሩ በደረሳቸው መረጃ ድጋፍ ያስፈልገዋል መባሉን ገልፀው፤ ሊበላሽ የሚችሉትን የምግብ እርዳታዎች እና በአፋጣኝ ለአገልግሎት መዋል አለባቸው የተባሉትን ለይቶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይከፋፈላሉ ብለዋል።

‹‹በየወረዳዎች የአቅም ማነስ ያለባቸው ተብለን ብንለይም ድጋፍ እየደረሰን አይደለም። ነገር ግን ምግብ ነክ እህሎች ሌሊት ከወረዳዎች ሲወጡ እየተመለከትን ነው›› ሲሉ ነዋሪዎች ያነሱትን ቅሬታ እንደማያውቁት በመግለጽ፤ የአዲስ አበባ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ የተለያዩ ክትትሎችን እንደሚያደርግ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በተጨማሪ ይኼን መሰል ጥቆማ የአዲስ አበባ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ጋር መጥቶ አያውቅም ሲሉ ነስረዲን ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here