የራያ ቆቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪና የወረዳው የሰላምና ደህንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ወቅት በተፈጸመባቸው ጥቃት ህይወታቸው ማለፉን የሰሜን ወሎ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ አስታውቋል።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ አሳዬ ተገኘ በትናንትናው ዕለት ለኢዜአ እንዳስታወቁት ሁለቱ የስራ ኃላፊዎች ጥቃቱ የተፈጸመባቸው በወረዳው 08 ቀበሌ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተከለከለውን ሰርግ ለማድረግ የተዘጋጁ ሰዎችን ድርጊት ለማስቆም ከደጋሾቹ ጋር ተነጋግረው ሲመለሱ መሆኑን ገልፀዋል።
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ስዩም መስፍንና የወረዳው የሰላምና ደህንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መንገሻ ሞላ በመንገድ ላይ ሳሉ የሰርጉ ታዳሚዎች በአንድ ባጃጅ በብዛት መሳፈራቸውን በማየታቸው አሽከርካሪውን አስቁመው ሲያናግሩ ከተሳፋሪዎች በተተኮሰ ጥይት የሁለቱም ህይወት ማለፉን አስረድተዋል።
ወንጀሉን ከቀትር በኋላ ከራያ ቆቦ ወረዳ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ 08 ቀበሌ ልዩ ስሙ አራዶ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ላይ የፈጸሙት ተጠርጣሪዎችም ታርጋ በሌለው ሌላ ባጃጅ ተሳፍረው ከአካባቢው መሰወራቸውን ተናግረዋል።
የዞኑ እና የወረዳው የጸጥታ ኃይሎችም በጋራ በመሆን የወንጀሉን ፈጻሚዎች በቁጥጥር ስር አውሎ ለህግ ለማቅረብ የተጠናከረ የክትትልና የአሰሳ ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙም ማስታወቃቸውን የኢ.ዜ.አ ዘገባ ያመለክታል።



