በአዳማ ከተማ 77 ሺህ 575 ብር ሐሰተኛ የብር ኖት ከአሳታሚዎቹ ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የከተማዋ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።
የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኝነት ባለሙያ ረዳት ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልሜቻ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት አንዱ ግለሰብ ሐሰተኛ ኖት ይዞ ወደ ገበያ በወጣበት ወቅት ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ሲሆን ግንቦት 26 ቀን 2012 ዓ.ም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በአዳማ ከተማ ሉጎ ክፍለ ከተማ ቢቃ ቀበሌ ሁለተኛውና ዋነኛው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር እንዲውል ተደርጓል ብለዋል።
ፖሊስ ዋናው ተጠርጣሪ ተከራይቶ ከሚኖርበት አዱላላ ቀበሌ ሃጤ ሀሮሬቲ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ውስጥ ሐሰተኛ የብር ኖቶች ፣ ማተሚያ ማሽን ከነሙሉ እቃው ጋር በቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉን ረዳት ኢንስፔክተር ወርቅነሽ አስታውቀዋል።
በዚህም ባለ 100 ብር 75 ሺህ፣ ባለ 50 ብር 2 ሺህ 550 ብር፣ ባለ 10 ብር ሁለት፣ ባለ 5 ብር አንድ እንዲሁም የውጭ ሀገር ገንዘብ በቤቱ ውስጥ መገኘቱን ገልፀዋል ።
በአሁኑ ሰአትም የሁለቱ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ በምርመራ ላይ ሲሆን ምርመራው ሲጠናቀቅ ለፍርድ ይቀርባሉ ተብሏል።
በተመሳሳይ ዜና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ በአንድ ቤት ውስጥ በአዳማ ከተማ ሉጎ ክፍለ ከተማ ጋረ ሉጎ ቀበሌ ቀጠና 17 ተብሎ በሚጠራው ልዩ ቦታ 18 ሆነው ሲጠጡ የተገኙ ሰዎች መቀጣታቸውን ረዳት ኢንስፔክተሯ አያይዘው ገልፀዋል።
የቤቱ ባለቤቶች የሆኑ ባልና ሚስት እያንዳንዳቸው 1 ሺህ 500 ብር የተቀጡ ሲሆን የተቀሩት 16 ሰዎች እያንዳንዳቸው 1 ሺህ ብር መቀጣታቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዳማ ከተማ ቦኩ ክፍለ ከተማ በሬቻ ቀበሌ በቀን ትናንት ከሌሊቱ 8 ሰዓት አካባቢ የአንድ ግለሰብ ንብረት የሆኑ አራት ሱቆች መቃጠላቸውን ረዳት ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልጸዋል።
በእሳት አደጋው በአራቱ ሱቆች ውስጥ ያሉ ንብረቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን የገለፁት የህዝብ ግኑኝነት ባለሙያዋ፤ የአደጋው መንስኤ ኤሌክትሪክ መሆኑንም መናገራቸውንም ከኢዜአ ዘገባ ለማወቅ ተችሏል።



