አስራ አንደኛ ክልል በመሆን በቅርቡ በክልል ደረጃ የተዋቀረው ሲዳማ ክልል በአዲሱ የክልሎች በጀት ድልድል ወቅት ከፌደራል መንግሥት ታሳቢ ተደርጎ አለመካተቱ እና በቅርቡ ሕዝባዊ ውሳኔ ተካሒዶበት በክልልነት ከተደራጀ በበጀት ድልድሉ አለመካተቱ የሕዝብን ድምጽ መናቅ ተደርጎ ይቆጠራል የሚል ተቃውሞ ተሰምቶበታል።
በተመሳሳይም የምክር ቤት አባል የሆኑት ጴጥሮስ ወልደሰንበት የሲዳማ ጉዳይ ቀድሞ ያለቀ ጉዳይ እንደመሆኑ መጠን ለቀጣዩ ዓመት የበጀት ድልድል ወቅት ለምን ሳይካተት ቀረ የሚል ጥያቄም ለገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ አቅርበዋል።
ዛሬ ሰኔ 4/2012 የቀጣዩን ዓመት 2013 በጀትን በተመለከተ ረቂቅ የቀረበ ሲሆን በወቅቱም የገንዘብ ሚኒስቴር አሕመድ ሽዴ ከምክር ቤቱ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። ሚንስትሩ በምላሻቸውም በጀቱ የተሰራው ከፌደሬሽን ምክር ቤት ተሰርቶ በሚመጣ ቀመር ሲሆን ከፌደሬሽን ምክር ቤት ሲዳማ ክልልን ያካተተ ቀመር ባለመሰራቱ በረቂቁ ላይ አለመካተቱን እና የፌደሬሽን ምክር ቤት ሲዳማ ክልልን ያካተተ ቀመር በላከ ጊዜ ድልድሉን መስራት እንደሚቻል አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ለመጪው በጀት ዓመት 2013 ለዘጠኝ ክልልች እና ለኹለቱ ከተማ አስተዳደሮች ከዚህ ቀደም እንደነበረው የቀረበ ሲሆን ለሲዳማ ክልል ሳይሆን ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በጠቅላላው 36 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መመደቡ ከምክር ቤቱ ጥያቄ ተነስቶበታል። የፌደራል መንግስት ለዘጠኙ ክልሎች እና ለኹለቱ ከተማ አስተዳደሮች የመደበኛ በጀት፣ የካፒታል በጀት እና ለክልሎች የሚሰጥ ድጎማ በጀት እንዱሁም ለዘላቂ ልማት በሚል በጠቅላላው 476 ነጥብ 12 ቢሊዮን ብር መመደቡ ታውቋል።
የመደበኛ በጀት 133 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ሲሆነ ይህም በ2012 ከተደለደለው የ16ነጥብ 7 በመቶ ቅናሽ እንደሚያሳይ ለምክር ቤቱ የቀረበ ሲሆን ከበጀቱም ውስጥ 34 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆነው ለደሞዝ አበል እና ልዩ ልዩ ክፍያዎች እንደሚውል ተገልጿል።የካፒታል በጀት 160 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ለክልሎች የሚሰጥ ድጎማ 176 ነጥብ 3 ቢሊዮን እንዲሁም የመጨረሻው ለዘላቂ ልማት የሚውል 6 ቢሊዮን ብር መሆኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።
በአሕመድ ሽዴ ለሕዝብ ተወካዮች የቀረበው ሪፖርት እንደሚያመለክተው በ2013 በጀት ዓመት የፌደራል መንግስት ከአገር ውስጥ የገቢ ምንጮች እንዲሁም ከውጭ ዕርዳታ በድምሩ 350 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደሚሰበስብ በዕቅዱ መያዙም ታውቋል። በቀጣዩ ዓመት የበጀት ዕቅድ ውስጥ በፌደራል መንግስት ገቢ እና ወጪ በጀት መካከል 126 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት መታየቱ የተገለጸ ሲሆን ይህም ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት 3 በመቶ እንደሚይዝ ታውቋል።
የ2013 በጀት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ዕድገት ቢኖረውም ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ወጪ ፍላጎት እንደሚጨምር ታሳቢ ተደርጎ እና ከአገሪቱ የልማት ፍላጎት አንጻር በቂ ነው ሊባል እንደማይችልም አሕመድ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል። የቀጣ ዓመት በጀት ማለትም 2013 ከቀዳሚው ዓመት 2012 በ30 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወይም የሰባት በመቶ እድገት እንዳለውም ተገልጿል።
ለምክር ቤቱ በቀረበው ሪፖርት ላይ በዚህ ዓመት ሊሰበሰብ የሚችለው የታክስ መጠን 200 ቢሊዮን ሊበልጥ እንደማይችል መተንበዩን አሕመድ ገልጸው ይህም ለ2013 የታክስ ትንበያ እንደመነሻ መደረጉንም ለማወቅ ተችሏል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውይይት የቀረበው የቀጣዩ ዓመት በጀት ረቂቅ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።
ቅጽ 2 ቁጥር 84 ሠኔ 6 2012



