ማኅበራዊ እሴቶች ሲናዱ መንግሥት ቆሞ እያየ ነው!

0
292

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በእጅጉ እየናረ መምጣት ከጀመረበት ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ እና የ21ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ጀምሮ ትርፍን ከሁሉም ነገር በላይ በማስቀደም የሚታወቀው የካፒታሊዝም ስርዓት ያለ ተገዳዳሪ እየናኘ መጥቷል። በዚህም የተነሳ አገሮች በኀያላኑ ተጽዕኖ ሥር በመውደቅ ወደዱም ጠሉም ይህንን መንገድ እንዲከተሉ እየተደረጉ ነው።

በአገራችንም የዚሁ ነፀብራቅ ብዙ ነው። ለዘመናት ተረጋግቶ የቆየው የሸቀጦች ዋጋ ኢትዮጵያ ነጻ ገበያን እንደምትከተል ከታወጀ ወዲህ ምን ያህል እጥፍ እንደጨመረ ማስላት እውነት የማይመስሉ ቁጥሮችን ይሰጣል። ቀደም ሲል ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ የነበሩ የመንግሥት ቢሮዎች እንኳን እንደ ዜጋ ሳይሆን እንደ ደንበኛ እንዲመለከቱን ስለተደረጉ ለምኑም ለምኑም እንዲያስከፍሉ ተደርገው ሕዝብን ለማራቆት የነጋዴው ዋነኛ አጋር ሆነዋል። በማኅበር መሬት እየተሰጠው ቤቶችን ይሠራ የነበረው ሕዝብ አሁን መሬት ጥቂትም ቢሆን ዶላር ለሚያመጣ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ነጋዴ ተሰጥቶ እኛው በባንክ ያጠራቀምነው ገንዘብ በብድር ይመረቅለት እና አንድ ክፍል ቤት በሚሊዮን ለእኛው ሊሸጥ ይነሳል።

በዚህም የተነሳ ጥቂቶች በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ሲያካብቱ አብዛኞቻችን ከወር ወር ለመድረስ ደፋ ቀና እንላለን፤ የከፋበት ደግሞ የቀን ጉርሱን ያሳድዳል። አገሪቱ ላይ የሚገኙት ከባድ ሚዛንም ሆኑ አነስተኛ ነጋዴዎች ዋጋን እጅግ በማናር የሕዝብ ኑሮ እየገደሉ እንደሆነ ለማወቅ ተንታኝ ኢኮኖሚስት አያስፈልገንም። በየዕለቱ በአካባቢያችን የምናየው ሁኔታ ነው። የዋጋ ውድነት የማይቀመስ ደረጃ ደርሶ እቃዎች በሳምንት ከአንዴ በላይ በሚጨምሩበት በዚህ ዘመን ትንሽም ብትሆን የንግድ ሱቅ ያለው ዶክትሬት ካለው በላይ ቢከበር አይገርምም።

በማኅበረሰባችን ውስጥ ለገንዘብ የሚሰጠው ቦታም እየናረ እንደመጣ እና ዕሴቶቻችንን እየሸረሸረ ለመሆኑ ብዙ ምልክቶች አሉ። ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘመን ጋር በዓለም ደረጃ ታይቶ ያው እንደተለመደው እኛም የኮረጅነው አንድ ወሳኝ ነገር የማኅበረሰብ አስተያየት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ የሚባሉት ሰዎች ምሁራን ሳይሆኑ በእውቀት የማይጠረጠሩ ታዋቂ አርቲስቶች እና ሀብታም ነጋዴዎች (ኢንቬስተሮች) ናቸው። በጣም ብዙ መረጃ በቀላሉ ለሕዝብ ተደራሽ በሚሆንበት በዚህ ዘመን ስለ በሽታ ሐኪም ቢያወራ የሚሰማው ስለሌለ ተብሎ ፊደል ያልቆጠር/ች የፊልም ተዋናኝ እንዲዘባርቅ ይደረጋል። መንግሥትም እነዚሁ አርቲስቶች እና ሀብታሞች ዋነኛ አጋሮቹ እንደሆኑ በማመን ለትንሹም ለትልቁም እነሱን ይዞ ያሽሞነሙናል። ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ እንዲህ ያለች ነች።

በዚህ የአዲስ ማለዳ ዕትም ሐተታ ዘ ማለዳ ላይ በሰፊው እንደዳሰስነው ይህ ሕዝብን በማስለቀስ የሚሰበሰብ ገንዘብ የሚጠፋው ማኅበራዊ እሴቶቻችንን በመበጣጠስ እና የገንዘብን ከሰው በላይ የመሆን እሳቤ በማስፋፋት ላይ ነው። አገሪቱ እንዲህ በኮሮና ወረርሽኝ ተወጥራ ባለችበት ጊዜ እንኳን እነዚህ የሕዝቡ አስተሳሰብ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያደርሳሉ የሚባሉ ጊዜ እንደፈለጉ እንዲሆኑ የፈቀደላቸው ሰዎች ቆይ ረገብ በሉ አሁን እንኳን የሚላቸው የለም።

ከተማዋ ውስጥ ታዋቂ የሆኑት ሀብታም ነጋዴዎች ሴት ሲጫረቱ ያመሻሉ የሚለው ዜና ከእነዚህ ሰዎች ጋር የጥቅም ትስስር ያለውንም ሰው ቢሆን ሊያስደረግጥ ይገባል። ወጣቶች ተምረው በትምህርታቸው ተስፋ ከመሰነቅ ይልቅ ወንዶቹ ሴቶችን ለሀብታም ነጋዴዎች ማቅረብን፣ ሴቶቹ ደግሞ ከፍ ያለ ገንዘብ የሚከፈላት ሴተኛ አዳሪነትን መምረጣቸው እንደማኅበረሰብ የደረስንበትን አዲስ የዝቅጠት ደረጃ የሚጠቁም ነው።

በዚህ ረገድ ታዋቂ ሴት አርቲስቶች (አንዳንድ ባለትዳሮችንም ጨምሮ) በሰፊው ይሳተፋሉ መባሉ ምን ያህል የሕዝብን አስተሳሰብ ለመምራት የሚሰጣቸው ቦታ እንደማይመጥናቸው የሚያሳይ ነው። በእነዚህ ሴቶች የተነሳ ብዙ ሕጻናት ሲያድጉ አርቲስት መሆንን ይመኛሉ። እነሱ የሚለቋቸው ፎቶግራፎችን፣ ቪዲዮዎችን እና አጭር መልዕክቶችን ሁሉ በመከተል ከፊልሙ በዘለለ ስለ እነሱ ማወቅ የሚያስጨንቃቸው ሕጻናት እና ተዳጊዎች ምን ዓይነት አደጋ ላይ እንዳሉ መታሰብ አለበት። እንዲህ ዓይነቱ ነገር ሲከሰትም የራሳቸው የኑሮ ምርጫ ብቻ እንደሆነ አድርጎ ማየቱ የሚያስኬድ አይደለም። የተግባራቸው ፍሬ ትውልድን የሚያመክን በመሆኑ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

ከዚህ ተግባር የፀዱ ሴትም ሆኑ ወንድ አርቲስቶች የወል መጠሪያው እኛንም ያካትታል በሚል ጉዳዩን ይፋ ያደረገችው አዲስ ማለዳ ላይ ሳይሆን መበሳጨት ያለባቸው ሙያው ማኅበረሰብን በሞዴልነት ለማገልገል የሚጥለውን ኃላፊነት መወጣት በማይችሉ ባልደረቦቻቸው ላይ ነው። ነገሩ ከዚህ በፊትም በስፋት ሲከሰት እያዩ እንዳላየ በመሆን ያለፉ ወይም በዚህ ተግባር ገንዘብ ካካበቱ ጋር ተጠግተው ሊጠቀሙ የሞከሩም ቢሆኑ አዕምሯቸው ሊወቅሳቸው ይገባል። ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የማኅበረሰቡ እና የመጪው ትውልድ አዕምሯዊ፣ መንፈሳዊ እና ሰብዓዊ ጤንነት እንጂ የጥቂት ከመስመር የወጡ ሰዎች ክብር አይደለም።

ይህንን ተግባር ተቋማዊ ለማድረግ ከትምህርት ቤት፣ ከቢሮ እንዲሁም ከተለያዩ ሌሎች ቦታዎች መልማይ አሰማርተው፣ ለዚህ ርካሽ ተግባር ገንዘባቸውን የሚያፈሱ “ኢንቬስተሮችን” በመሳብ “ዘመናዊ” ንግድ ጀምረናል የሚሉትን ገንዘብ ያወራቸው ሰዎች መንግሥት እንደማይተባበራቸው ለሕዝብ ሊያሳይ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች። በሀብታም ነጋዴዎች እና በመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል ያለው የሙስና ግንኙነት እነዚህ ሰዎች እንደማይነኩ መተማመኛ ሆኗቸው ለዚህ ድፍረት እንደበቁ ባይጠረጠርም፣ ለለውጥ እየተንቀሳቀስኩ ነው የሚለው ብልጽግና ፓርቲ በእሴቶቻችን መናድ ላይ እንደማያንቀላፋ ሊያሳየን ይገባል።

በጽሁፉ ላይ በመጀመሪያ ደረጃ የተጠቀሰው ወሎ ሰፈር አካባቢ የሚገኘው ቤት መግቢያ የመንገድ መብራት የሌለው መሆኑ ከሰፈሩ ጋር የማይሔድ ነው። ነገር ግን የውስጥ ለውስጥ መብራት በሌለባቸው ሰፈሮች ላይ እንኳን ቤቶች የውጭ መብራት ያበራሉ። ይህ ሁሉ የሌለበት መሆኑ ወጣ ያደርገዋል።

በኹሉተኛነት የተጠቀሰው ብስራተ ገብርኤል አካባቢ ያለው ቤት ደግሞ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) 200 ሜትር የማይበልጥ ርቀት ላይ የሚገኝ ነው። ኤጀንሲው አገሪቱን ከዓለም ጥጋ ጥግ ከሚነሱ የበይነ መረብ ጥቃቶች ይከላከላል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከፍተኛ ጥበቃም እንደሚደረግለት ይታወቃል። ምንም እንኳን ይህንን መከታተል የኤጀንሲው ኃላፊነት ባይሆንም ጥያቄ ማስነሳቱ ግን አይቀርም።

በሦስተኛነት ቦሌ ከሚገኘው ራማዳ ሆቴል ገባ ብሎ የተጠቀሰው ቤትም የባለሥልጣናት መኖሪያ በመሆኑ ይታወቃል። በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ጥበቃ በአካባቢው አለ። ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ ተግባር እዚያው መካከል መካሔዱ የባለሥልጣኖች ከለላ ሊኖር እንደሚችል የሚያስጠረጥር ነው።

ከእነዚህ ሁሉ በተጨማሪ ግን በተደጋጋሚ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት መጠጥ ቤቶች በጊዜ እንዳይዘጉ ጉቦ በመቀበል ፊቱን ሲያዞር የቆየው ፖሊስ አሁንም ተጠያቂ ነው። ፖሊስ በተደጋጋሚ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንዳልሆነ አይተናል። የአፍና አፍንጫ ጭንብል አላደረግክም ብሎ ደሀውን ሕዝብ ሲደበድብ እና በእስር ሲያሳድር የከረመው ፖሊስ ይህንን ያህል ትልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰት ሲደረግ እንዳላየ ማለፉ የሚያሳፍር ነው።

አንድ እንጨት ተተከለ ብለው ቤት ድረስ በቅጽበት የሚደርሱት የቀበሌ ሰዎችም እንዲህ ዓይነቱን ጉድ እንዳላዩ ማለፋቸው ሊያስኮንናቸው ይገባል። አገራችን ሕግ ድሆች ላይ ብቻ የሚተገበርባት እና ሀብታሞች ከቁጥጥር ውጭ የሚሆኑባት ከሆነች ከርማለች። ነገር ግን እንደ ሕዝባችን እምነት አለን የሚሉት አዲሶቹ ባለሥልጣኖቻችን ይህንን ለመቀየር ጥረት እያደረጉ ቢሆን እንኳን የሚታይ አይደለም።

ቅጽ 2 ቁጥር 84 ሠኔ 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here