የኢትዮጵያ የአዕምሮ ሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ማህበር አባላቱ የተለያዩ የአዕምሮ ህሙማን መድኃኒቶች እጥረት በመፈጠሩ እና ዋጋቸው በመጋነኑ ታካሚዎች እየተቸገሩ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ፡፡
የአዕምሮ ሕክምና ተጠቃሚዎች የህመም ዓይነታቸው የተለያየ ሲሆን በቂ የሚባል የመድኃኒት አቅርቦት ማግኘት ባለመቻላቸው እና የዋጋ ጭማሪ በመከሰቱ አንዳንዶች መድኃኒት መውሰድና ክትትል ማድረግ ማቆማቸውን የአዕምሮ ህክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት የወይንሸት ብርሃን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል፡፡
ምክትል ፕሬዝዳንቷ እንደሚሉት በኢትዮጵያ የአዕምሮ ሕክምና ላይ ግንዛቤ ባለመኖሩ የአዕምሮ ህሙማን በተለያየ ሁኔታ ተጎጂ ይሆናሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከኮቪድ-19 መከሰት ጋር ተያይዞ ችግሩ እየተባባሰ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም የአዕምሮ ታማሚዎች በአሁኑ ጊዜ መድኃኒቶችን አገር ውስጥ ባለማግኘታቸው እና የመድኃኒት ዋጋ በመጨመሩ የሕክምና ክትትል እየተቋረጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ማህበሩ ችግሩን ለጤና ሚኒስቴር በደብዳቤ ቢያሳስብም እስከ አሁን ለችግሩ ተጨባጭ ምላሽና መፍትሔ አንዳልተሰጠው ምክትል ፕሬዝዳንቷ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡ ማህበሩ ችግሩን ለጤና ሚኒስቴር ካሳሰበ በኋላ ማየት እንደተቻለው ሒደቱ ቢሮክራሲ የበዛበትና ችግሩ ደግሞ አፋጣኝ ምላሽና ትኩረት የሚያሻው መሆኑን እንደተገነዘቡ፣ ነገር ግን በቶሎ ምላሽ አለመሰጠቱን የወይንሸት አክለው ገልጸዋል፡፡
ማህበሩ ህሙማኑ በመድኃኒት እጥረት ምክንያት እየተቸገሩ መሆኑን አስመልክቶ ጉዳዮን ለጤና ሚኒስቴር በደብዳቤ አሳውቆ ያገኘው ምላሽ የመድኃኒቱ ግዢ በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ቀደም ሲል እንደተከናወነና መድኃኒቱን ለጠየቁ ሆስፒታሎች እየተሰራጨ መሆኑን የሚገልጽ እንደሆነ የወይንሸት አስረድተዋል፡፡
ነገር ግን መድኃኒቱ አገር ውስጥ መግባቱ ትልቅ የምስራች ቢሆንም በተለያየ ደረጃ በሚታይ የመረጃ ክፍተት ምክንያት የመድኃኒቱ ተጠቃሚዎች እየተጎዳን እንገኛለን ሲሉ ወቀሳቸውን አቅርበዋል፡፡
የአዕምሮ ሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ዮናስ ዘለቀ የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ወዲህ የአዕምሮ ታካሚ ህሙማን በተለያዩ ምክንያቶች ሕክምና አቋርጠው እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ እንደ ማሳያነት በአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሕክምናቸውን ይከታተሉ የነበሩ ታማሚዎች በእንቅስቃሴ ገደቡ ምክንያት ወደ ሆስፒታሉ መምጣት እንዳቆሙ ዶ/ር ዮናስ ጠቁመዋል፡፡
ዶ/ር ዮናስ የአዕምሮ ህሙማን በአሁኑ ወቅት የሰዎች ማህበራዊ እገዛ እንዳጡ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊት ህሙማኑን የሚደግፉ ሰዎች በአሁኑ ወቅት በራሳቸው ችግር በመጠመዳቸው ያንን ማድረግ አልቻሉም ሲሉም ያለውን ችግር ያስረዳሉ፡፡
የአዕምሮ ሕክምና ታማሚዎችን ከሌላ የበሽታ ዓይነት ህሙማን ለየት የሚያደርጋቸው ነገር እራሳቸውን እንደሌሎች ህሙማን መቆጣጠርና ነገሮችን የመረዳት አቅም የላችውም፣ ስለሆነም እንደ የካንሰርና የልብ ህሙማን የለመዱት እንክብካቤና እንቅስቃሴ ሲቀርባቸው በኮቪድ-19 መሆኑን አይረዱም ይላሉ፡፡ በመሆኑም ለህሙማኑ አስፈላጊው ትኩርት መደረግ እንዳለበት እና የመድኃኒት አቅርቦት ችግር መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ ዶ/ር ዮናስ ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም በፍኖተ ሰላም ሆስፒታል የአዕምሮ ህሙማን ተኝቶ መታከሚያ የነበሩ አልጋዎች ለኮቪድ-19 ይፈለጋሉ ተብለው በመወሰዳቸው በሆስፒታሉ ይታከሙ የነበሩ የአዕምሮ ታካሚዎች ሕክምና ማግኘት እንዳልቻሉ ተጠቁሟል፡፡
የአዕምሮ ሕክምና መድኃኒቶች አገር ውስጥ መገኘት አለመቻላቸው ትልቁ ችግር መሆኑን የአዕምሮ ሐኪሙ ዶ/ር ዮናስ ተናግረዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ የጤና ተቋማት እና ህብረተሰቡ ሰፊውን ትኩረታቸውን ለኮቪድ-19 በማድረጋቸው ሌሎች በሽታዎች የሚያሻቸውን ትኩረት ያጡበት እና ታማሚዎችም ሕክምና ለማግኘት እየተቸገሩ እንደሆነ በሚያሳይ መንገድ አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም የልብ እና የኤች አይ ቪ ኤድስ ህሙማንን ችግር መዘገቧ ይታወሳል፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 85 ሠኔ 13 2012



