ደረጃ ዶት ኮም በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ቨርችዋል የሥራ ዐውደርዕይ ሊያካሂድ ነው

0
1247

የኢንፎ ማይንድ ሶሉሽንስ ቢዝነስ ክፍል የሆነው ደረጃ ዶት ኮም ሐምሌ 22/2012 በኢትዬጲያ ለመጀመሪያ ጊዜ ቨርችዋል የሥራ ዐውደርእይ ሊያካሂድ መሆኑን አስታወቀ።

ኢንፎማይንድ ሶሉሽንስ ኢትዮጃብስ የሚባለውን ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ እና የሠራተኞች የሥራ ማመልከቻ ተቀባይ ድረ ገፅን የሚያንቀሳቅሰው ድርጅት ነው።
ደረጃ ዶት ኮም (Dereja.com) ሰኔ 11/2012 ባደረገው የቪዲዮ ኮንፍረንስ ስብሰባ ከኢትዬጲያ ሥራ ፈጠራ ኮሚሽን እና ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በኢትዬጲያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሔድ ቨርችዋል የሥራ ዐውደርዕይ ማዘጋጀቱን የደረጃ ዶት ኮም ፕሮግራም ዳይሬክተር ሲሃም አየለ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ሲሃም አየለ እንዳሉት በኮቪድ-19 በተፈጠረው እክል ምክንያት በአዲስ አበባ እና በተመረጡ የክልል ከተሞች ላይ የገጽ ለገጽ የሥራ ዐውደርዕይ ለማዘጋጀት የነበራቸውን እቅድ ማስተካከል ግድ ሆኗል።በዚያ ምትክ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂን በመጠቀም እጩ ምሩቃንን፣ ድርጅቶችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በአንድ መድረክ ለማገናኘት እየሰራን ነው ብለዋል።

ደረጃ ዶት ኮም አገራችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስግባት እጩ ምሩቃንን ያለምንም አካላዊ ንክኪ ከቤታቸው በመሆን ስልካቸውን ወይንም ኮምፒዩተራቸውን በመጠቀም ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በሥራ እድል ዙሪያ እንደሚያገናኝ ሲሃም ጠቁመዋል።

ሲሃም አክለው ለመጀመሪያ ጊዜ የሚዘጋጀው ቨርችዋል የሥራ ዐውደርዕይ ላይ ከ10 ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ ከ5000 በላይ እጩ ምሩቃን ከ110 በላይ ተሳታፊ ቀጣሪ ድርጅቶች ጋር የመገናኘት እድል ይኖራቸዋል።

በዐውደርእዩ ላይ ከሚሳተፉ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ፣ ጅማ ዩኒቨርስቲ፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ፣ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ፣ አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ፣ መቀሌ ዩኒቨርስቲ እና ቅድስት ማርያም ዩኒቨርስቲ እንዲሁም ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ እንደሚገኙበት ሰሃም ገልጸዋል።
በ2012 የትምህርት ዘመን በኮቪድ-19 መከሰት ምክንያት ትምህርት በመቋረጡ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች እንደማይመረቁ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር መግለጹ የሚታወስ ነው።በዚህም ምክንያት በሥራ አውደርዕዩ ላይ የባለፈው ዓመት ተመራቂዎች እና በዚህ ዓመት ትምህርት በማቋረጡ ምክንያት መመረቅ ያልቻሉ ተማሪዎች በአንድነት እንደሚሳተፉ ሲሃን ገልጸዋል።

ማስተርካርድ ፋውንዴሽን ያንግ አፍሪካ ወርክስ በተሰኘ ፕሮግራሙ ከደረጃ ዶት ኮም ጋር በመተባበር የወጣቶች የሥራ እድል ክፍተትን ለማጥበብ እየሰራ እንደሚገኝም ፕሮግራም ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል።

ፕሮግራሙ እጩ ምሩቃንን በሥራ ዓለም ተፈላጊ በሆኑ ክህሎቶች በማሰልጠን የወጣቶችን ሥራ አጥነት ለመቀነስ በስፋት ይሰራል ተብሏል።ይህንንም ዓላማ ለማሳካት በተመረጡ ዩኒቨርስቲዎች ለሚገኙ እጩ ምሩቃን የሙያ ማበልጸጊያ ፕሮግራሞችን፣ የሥራ ዐውደርእዮችን እንዲሁም ልዩ የሥልጠና ፕሮግራሞችን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ሲሃም አመላክተዋል።

ደረጃ ዶት ኮም እሰከ አሁን አዲስ ተመራቂ ተማሪዎች የሥራ ክህሎት እንዲያዳብሩ ከማድረግ በተጨማሪ በ2010 ባካሄደው ዐውደርዕይ ከስድስት ሺህ በላይ ተማሪዎች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ያደረገ ሲሆን በ2011 ከአንድ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተመራቂ ተማሪዎች ይህንኑ ተግባር መከወኑን ሲሃም አስታውሰዋል።
ደረጃ ዶት ኮም አዲስ ተመራቂ ተማሪዎች የሥራ ፈጠራ ክህሎት እንዲያዳብሩ እና ብቁ የሥራ አቅም ገንብተው በቀጣሪ ድርጅቶች እንዲቀጠሩ ለማድረግ የተለያዩ የሥራ ፈጠራ እና የሥራ ፍለጋ ክህሎቶች ላይ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጥም ሲሃም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ከመንግሥትና ከግል የትምህርት ተቋማት በየዓመቱ አስከ 200 ሺህ የሚደርሱ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች እንደሚመረቁ መረጃዎች ይጠቁማሉ።ከነዚህ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዙት ተመራቂ ተማሪዎች ከመንግሥት ዩንቨርስቲ የሚመረቁ ሲሆኑ፣ በ2011 የትምህርት ዘመን በሀገሪቱ ከ32 የመንግሥት ዩንቨርስቲዎች 120 ሺህ ተማሪዎች ተመርቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 85 ሠኔ 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here