ዕለታዊው የኮሮና ቫይረስ የሟቾች ሪፖርት ችግር አለበት ተባለ

0
658

ጤና ሚኒስቴር የሚሰሩ ማንታቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሕክምና ባለሙያ በአደጋ እና ሌሎች መንስኤዎች የሚሞቱ ሰዎች በአስከሬን ምርመራ ኮሮና ቫይረስ እንደነበረባቸው ሲረጋገጥ በኮቪድ-19 እንደሞቱ ተደርጎ የ24 ሰዓት የኮሮና ቫይረስ ሪፖርት ውስጥ መካተታቸው ተገቢ እንዳልሆነ ገለጹ።
በትራፊክ አደጋ ሕይወቱ አልፎ የአስከሬን ምርመራ ሲደረግለት ኮሮና ቫይረስ የተገኘበት ሰው ቤተሰቦች ለአዲስ ማለዳ እንደጠቆሙት በ24 ሰዓት የኮሮና ቫይረስ ሪፖርት ውስጥ በኮሮና እንደሞተ ተደርጎ ተካቷል።

ይህም ተገቢ እንዳልሆነ እና የሞቱ መንስኤ ኮቪድ-19 ሳይሆን የትራፊክ አደጋ መሆኑ እየታወቀ እንዲህ ዓይነቱ ጥሰት መሰራቱ ትክክል አይደለም ሲሉ ቤተሰቦቹ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

የሟች ቤተሰቦችን ቅሬታ አንስታ ማንነታቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉትን የሕክምና ባለሙያ ስታናግርም በአደጋ የሞተውን እና በሌላ በሽታ የሞተውን ሰው በኮሮና ቫይረስ እንደሞተ አድርጎ ማውጣቱ ቁጥር ከመጨመር እና ህብረተሰቡ ላይ ጭንቀት ከመፍጠር ባሻገር ጠቀሜታው የተገደበ ነው ያሉት።
የሕክምና ባለሙያው አላስፈላጊ የሆነ ጭንቀት እና ከመጠን ያለፈ ጭንቀት ለጥንቃቄም ለጤናም አይጠቅምም ‹‹ከጥቅሙ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው›› ሲሉ የድርጊቱን ስህተትነት አጽንኦት ሰጥተውታል።

እንደ እርሳቸው አባባል ሊደረግ የሚገባው ህብረተሰብ ተገቢውን ያህል ጥንቃቄ እንዲወስድ ማድረግ እና ከዚያ አልፎ በበሽታው ተጠቂ ከሆነ ደግሞ የማገገም አቅሙ ከፍተኛ እንደሆነ ማሳወቅ ነው ብለዋል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከሦስት ሳምንት በፊት በደቡብ ክልል ከፋ ዞን በድንገት በተፈጠረ ጠብ ምክንያት ሕይወቱ ያለፈ አንድ ግለሰብ አስከሬን ለምርመራ ተልኮ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሆኖ በመገኘቱ የሞቱ መንስኤ ኮሮና ቫይረስ ነው ተብሎ ተዘግቦ ነበር።

በተመሳሳይ መልኩ ከሳምንት በፊት በአዲስ አበባ አየር ጤና ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በትራፊክ አደጋ ሕይወቱ ያለፈ ሰው የአስከሬን ምርመራ ኮሮና ቫይረስ እንደነበረበት የተጠቆመ መሆኑን ተከትሎ ግለሰቡ በቫይረሱ ሳቢያ ነው የሞተው ተብሎ በ24 ሰዓት ሪፖርት ውስጥ ተካቶ ነበር።

በሌላ ምክንያት የሞተው የአስከሬን ምርመራቸው በኮሮና ቫይረስ ተይዘው እንደነበር ያረጋገጣቸውን ሰዎች ሪፖርት ውስጥ ስለማካተት የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት መግለጫ እንደሚሰጥ ከጤና ሚኒስትር የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ዮርዳኖስ አለባቸው ገልጸዋል።

በኢትዮጲያ የኮሮና ቫይረስ የመመርመር አቅም ከፍ እያለ መምጣቱን እና በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ በቀን ከ8ሺኅ በላይ የሚጠጉ ሰዎችን መመርመር እንደሚቻል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሪፖርት ሲያደርጉ ጠቅሰው ነበር።

በቫይረሱ ከተያዙት በተጨማሪ የሟቾች ቁጥር ከፍ እያለ ለመገኘቱ አስክሬን ምርመራውም ተጠናክሮ መቀጠሉ አንደ ምክንያትነት ይጠቀሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 85 ሠኔ 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here