በአማራ ክልል ለሚገኙ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሦስት ቢሊዮን ብር ብድር ተሰራጭቷል

0
770

በአማራ ክልል ለሚገኙ ኀብረት ሥራ ማኅበራት በተገባደደው በጀት ዓመት እስከ ግንቦት ወር 2012 ድረስ በክልሉ ለሚገኙ ነባር መሰረታዊ ብድርና ቁጠባ ኀብረት ሥራ ማኅበራት እና ከኅብረት ሥራ ማኅበራት ገንዘብ ቁጠባ ዩንየኖች ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ለአባላት ብርድ መሰራጨቱን የአማራ ክልል የገንዘብ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በበጀት ዓመቱ በ3 ሺሕ 519 ነባር መሠረታዊ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኀብረት ሥራ ማኀበራት ለአባሎቻቸው እስከ ግንቦት ወር ድረስ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ብድር ማሰራጨት መቻሉን እና በግንቦት ወር 2012 ብቻ 17 ሚሊዮን ብር ለአባላቶች መሰራጨቱን የአማራ ክልል ፋይናንስ ኅብረት ሥራ ማኅበራት አደራጅ ባለሙያ እና የዘርፉ ዳይሮክቶሬት ተወካይ ሽታው ይርሳው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በ27 ነባር የኀብረት ሥራ ማኀበራት የገንዘብ ቁጠባና ብድር ዩንየኖች እስከ ግንቦት ወር ድረስ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የተሰራጨ ሲሆን፣ በግንቦት ወር 2012 ብቻ 124 ሚሊዮን ብር ለአባል ኀብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየኖች መሰራጨቱን ሽታው ይርሳው አክለው ገልጸዋል።

ለኅብረት ሥራ ማኅበራቱ የተሰራጨው ብድር የአጭር ጊዜ ብድር ሲሆን፣ አብዛኛው በአንድ ዓመት ውስጥ የሚመለስ ብድር መሆኑን ሽታው ተናግረዋል። የብድሩ የወለድ መጠን በአማካኝ ከ10 እስከ 12 በመቶ ሲሆን፣ እንደየአካባቢው የብድሩ ወለድ መጠንም እንደሚለያይ ተጠቁሟል።

በክልሉ በየዓመቱ በገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ከኅብረት ሥራ ማኅበራት ገንዘብ ቁጠባ ዩንየኖች ለአባላት የሚሰራጨው ብድር በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱም ተጠቁሟል።
በብዛት የብድሩ ተጠቃሚ የሆኑ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሁለገብ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት መሆናቸውን ሽታው ጠቁመዋል። የብድር ማሰራጨቱ ሥራ ቅድሚያ ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት እንደተሰጠ ተገልጿል። ከሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ቅድሚያ የተሰጠበት ምክንያት፣ የገበያ ማረጋጋት ሥራ ለመሥራት እና በበቂ ሁኔታ ለኅብረተሰቡ ምርትና አገልግሎትን በተቀላጠፈ መንገድ ማቅረብ እንዲችሉ ታሳቢ ተደርጎ መሠራቱንም አስታውቀዋል።

በዚህም አሁን ላይ በክልሉ የሚገኙ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለማኅበረሰቡ በየአካባቢው በቂ ምርት ለማቅረብ በሙሉ አቅማቸው እየሠሩ መሆኑን እና ኮቪድ-19 የፈጠረውን ጫና ለማቃለል ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ሽታው አክለው ገልጸዋል።

ከወቅታዊ ኮቪድ-19 መከሰት ጋር ተያይዞ በክልሉ በሚገኙ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት እንዳጋጠማቸውም ሽታው አያይዘው ጠቁመዋል። የገንዘብ እጥረቱ የተከሰተበት ምክንያት ከወረርሽኙ መከሰት ጋር ተያይዞ የተበዳሪዎች የብድር ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ እና የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ያላቸው አቅም ከፍላጎቱ ጋር ባለመመጣጠኑ እንደሆነም ተወካዮ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በኮቪድ-19 መከሰት ከዚህ በፊት ብድር ወስደው በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ተበዳሪ አባላት የንግድ ሥራቸው በመቀዛቀዙ የወሰዱትን ብድር በወቅቱ መመለስ አለመቻላቸው ሌላው ችግር መሆኑም ተጠቅሷል።

መንግሥት ለገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት ብድር አለማመቻቸቱ በዘርፉ እንደሌሎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በሙሉ አቅም እንዳይሠራ እንዳደረገው የጠቆሙት ሽታው፣ በክልሉ የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ ለፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ በስልክ ማሳወቃቸውን እና ኤጀንሲው ችግሩን ለመፍታት መፍትሔ እንደሚያፈላልግ መጠቆሙን ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 86 ሠኔ 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here