ንስር ማይክሮ ፋይናንስ የተበዳሪዎችን ንብረት ያለአግባብ እየወሰደ በመሆኑ ቅሬታ ቀረበ

0
1466

ከንስር ማይክሮ ፋይናንስ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ የነበሩ ደንበኞች በተቋሙ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ንብረታችንን እንድናጣ እየተደረግን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አቀረቡ።
ቅሬታ አቅራቢ ደንበኞች ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ከንስር ማይክሮ ፋይናንስ ብድር እንደወሰዱ እና የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ ብድራቸውን መክፈል እንዳይችሉ እንቅፋት ሆኖባቸው ነበር። በዚህም እንደ ማንኛውም ብድር ተበዳሪ አስተያየት ሊደረግልን ሲገባ፣ አስራ አምስት ቀናት የብድር መክፈያ ዕድሜ ብቻ ሰጥተውን እና ከተሰጠውም ጊዜ ባነሰ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለብድር መያዣነት ያስመዘገብነውን ተሽከርካሪ ተወስዶብናል ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ 20 የሚሆኑ ተበዳሪዎች ያለ አግባብ በንስር ማይክሮ ፋይናንስ አማካኝነት ለመያዣነት ያስመዘገቧቸው ተሽከርካሪዎች መነጠቃቸውን አዲስ ማለዳ ለማረጋገጥ ችላለች።
ተበዳዮቹ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ ያስያዙት መኪና ሲታሰርባቸው ለትራፊክ ፖሊስ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ አንድ ሺሕ ብር እንዲሰጡ ተገደዋል። ከዛም በተጨማሪ ተሽከርካሪው ከታሰረ በኋላ ደግሞ ከዚህ ቀደም በየሦስት ወሩ ይከፍሉ የነበረውን በመተው፣ በአንድ ጊዜ ያለባቸውን አጠቃላይ እዳ ካልከፈሉ ተሽከርካሪው ተይዞ እንደሚቆይ እንደተነገራቸውም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

‹‹በዚህም ምክንያትም ተደጋጋሚ አቤቱታ ለንስር ማይክሮ ፋይናንስም ሆነ ለፌዴራል ትራፊክ ጽሕፈት ቤት አቅርበናል። ሆኖም ምንም ዓይነት መፍትሄ ማግኘት አልቻልንም።›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

በተጨማሪ ትራፊክ ፖሊሶቹ ተሸከርካሪዎችን አስቁመው ወደ ተቋሙ ላደረሱበት እንዲከፈላቸው የሚደረገውን አንድ ሺሕ ብር ሙሉውን እነርሱ ራሳቸው እንዲሸፍኑ እንደተደረጉ እና ይህም በኅብረተሰቡ ዘንድ የተቋሙን ሥም የሚያጎድፍ ነው ብለዋል። አያይዘውም ‹‹ከዚህ በኋላም በተቋሙ ላይ ያለንን እምነት እንድናጣ የሚያደርግ ነው።›› በማለት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያያዞ የንስር ማይክሮ ፋይናንስ የማርኬቲንግ ማኔጀር ሄኖክ አበራ ‹‹ተቋሙ ብዙ አይነት አሰራር ይከተላል። ያበደርነውን ብድር እንውሰድ እና ጊዜ እናራዝም ብንል ያስቀማጮቹን ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ማሟላት አንችልም። ስለዚህ ይሄንን ለማድረግ ተገደናል።›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየት ይናገራሉ።

ብድር አገልግሎት ያገኙ የተቋሙ ደንበኞች ያስያዙት መኪና በመታሰሩ ስለሚነሳው ቅሬታ አንስተውም፣ ‹‹ይህን እርምጃ መውሰድ የጀመርንበት ምክንያት፣ ብድራቸውን መክፈል ካቆሙ በስድስተኛ ወራቸው የመጡትን እና ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ የሰጠናቸውን ላይ ነው እንደዛ አይነት እርምጃ መውስድ የጀመርነው ብለዋል።››

ይህንንም ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት ሄኖክ ሲያብራሩ፣ ‹‹ድንገት ካልሆነ እና መኪናችሁ ይያዛል ብለን ከተናገርን የማሸሽ እንቅስቃሴ ይኖራል። ስለዚህም ተፈላጊውን ነገር ማግኘት አንችልም›› ብለዋል። አክለውም በእነርሱ መስፈርት አንድ ተበዳሪ መክፈል የሚጠበቅበትን በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ መሆኑን አንስተው፣ መክፈል ከነበረበት ዘጠና ቀን ሲያልፍ ወደ ተበላሸ ብድር ይገባል ብለዋል። ‹‹በዛ መሰረት እርምጃ እንድንወስድ ከሚያስገድደን ነገር መካከል ይሄ በመሆኑ ነው።›› ብለዋል።

ነገር ግን ‹የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ በመጣበት ወቅት እና የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ በተቀዛቀዘበት ጊዜ መኪናችን ተይዞ ቀሪውን ሙሉ ክፍያ ካላመጣችሁ አይመለስላችሁም መባሉ ትክክል አይደለም› በማለት ለሚቀርበው ወቀሳ ምላሽ ሲሰጡ፣ ተቋሙ የኮቪድ 19 መግባት እና የኢኮኖሚው መጎዳትን ምክንያት በማድረግ በብድር አከፋፈሉ ላይ የተለያየ ዓይነት አስተያየቶችን አድርጓል ብለዋል። ‹‹ይህም ወለድ እስከመተው እና ከተበደሩት ብድር ለአንድ ዓመት ከፍያ ፈጽመው ቀሪ አንድ ዓመት የቀራቸውን ደግሞ ከሚከፍሉት እንዲቀንስ እስከማድረግ ነው።›› እንደ ሄኖክ አስተያየት።

‹‹ተሽከርካሪዎቹ እንዲያዙ ሲል ለትራፊክ ጽሕፈት ቤት ተቋሙ ይጽፋል። ይሄ ታርጋ በእኛ ተቋም ይፈለጋል ተብሎ ትራፊክ ጽሕፈት ቤት ደግሞ በተዋረዳቸው ይበትኑታል። በዚህም ተፈላጊው መኪና ተይዞ ይመጣል። መንግሥት ይሄን ሥራ ለሚሠሩበት ስለማይከፍል፣ ጊዜንም ስለሚያባክኑ፣ እኛ እንድንከፍል እንገደዳለን።›› ብለዋል። አክለውም ‹‹እኛ ደግሞ ስንከፍል በደምበኛው ሥም ነው የምንከፍለው። ይሄ የሆነው ደግሞ ተበዳሪያችን ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ በመሆኑ እንዲከፍል ይደረጋል።›› ሲሉ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 86 ሠኔ 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here