የመሬት ወረራን ሳይቃጠል በቅጠል

0
547

ባለፉት ዓመታት በተለይም ከኹለት ዓመታት ወዲህ እየታዩ ግን ደግሞ የዕርምት እርምጃዎችም ከመወሰድ የተቆጠቡባቸው ሕገ ወጥ ተግባራት መኖራቸውን በርካቶቻችን የምንስማማበት ጉዳይ ነው። በየቤታችን፣ መኖሪያችን አካባቢ፣ በመስሪያ ቤቶቻችን ዙሪያ እና በዕለት ተዕለት ከምንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች እነዚህ ሕገ ወጥ ናቸው የሚባሉ ግን በአደባባይ እየተከወኑ ያለ ማንም ሀይ ባይነት የሚተገበሩ ጉዳዮች የነባራዊ ሁኔታው አንዱ አካል ናቸው።

ከጥቃቅኖቹ የኪስ ስርቆት እስከ ተደራጁ የወንጀል ድርጊቶች፣ ከነብስ ግድያ እስከ ተሸርካሪ ስርቆት እና ቤት ሰብሮ ስርቆቶች የመዲናችን አዲስ አበባ ከፍተኛ ራስ ምታት መሆን ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል። ዛሬም በጉልበተኞች እና በአጭበርባሪዎች የተወሰደባቸውን ንብረት ለማስመለስ ወይም ተከታትሎ ለመያዝ ሳይቻል ቀርቶ የብዙዎች ቤት ቀዝቅዟል፣ የበርካቶች ቅስም ተሰብሮም ሜዳ ላይ ፍትህን ፍለጋ ወጥተው ምናልባትም ፍትህን በራሳቸው መንገድ ለማግኘት አላስፈላጊ መንገዶችን ለመሔድም የሚያስቡ አይታጡም።

ከዚህ ሁሉ ባለፈ ደግሞ በመዲናችን አዲስ አበባ ከቀን ወደ ቀን እየተካረረ እና በጠራራ ጸሐይ ሲተገበር ሰው ምን ይለኛልን ወደ ጊን ባደረጉ እና ሕገ ወጥነትን በጉልበት ሕጋዊ ለማድረግ የሚጥሩ ግለሰቦችን ማየት የተለመደ እየሆነ ነው። ጥዋት ወደ ስራ ስንወጣ ባዶ ሆኖ የነበረውን የሰፈር አረንጓዴ ስፍራዎች መሽቶ ወደ ቤት ስንገባ መተላለፊያ ብቻ ሲቀር በሕገ ወጥ መንገድ ታጥሮ እና በምን አግባብ እንደተያዘ እንኳን በስፍራው ለሚኖሩ ነዋሪዎች ግልጽ ባልሆነ መንገድ የመኖሪያ ስፍራዎችን አረንጓዴ ስፍራዎች እና መተላለፊያ መንገዶች በማጠር ነዋሪዎችን መውጫ እና መግቢያ በማሳጣት የሕዝብን ምሬት እያባባሱት ይገኛሉ።

የተፈጠሩትን ችግሮች በተመለከተም ቅሬታቸውን ከአቅራቢያቸው በሚገኘው የወረዳ ጽሕፈት ቤት እስከ ከንቲባ ቢሮ ድረስ ሔደው አቤት ቢሉም ቅሬታ ማግኘት አለመቻላቸው ደግሞ የምሬታቸውን እና የፍትህ መጓደሎችን ሒደት በግልጽ የሚያስቀምጥ አካሔድ ለመሆኑ ማስረጃ ናቸው። ጉዳዩን ይበልጥ ውስብስብ የሚያደርገው ደግሞ በተደጋጋሚ ለዝግጅት ክፍላችን ጥቆማ የሚያደርሱን ቅሬታ አቅራቢዎች እንደሚናገሩት በመሬት አስተዳደር እና ተያያዥ መስሪያ ቤቶች ዘንድ ከፍተኛ የኃላፊነት ስፍራ ያላቸው ግለሰቦች በተዋናይነት መሳተፋቸው የነገሩን ክብደት እና ለቅሬታም በሚሔዱበት ጊዜ ጉዳያቸው መፍትሔ እንዳያገኝ ምክንያት እንደሆኑም ይናገራሉ። ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ አዲስ ማለዳ በተለያ አካባቢዎች በመዘዋወር በተለይም ደግሞ በቦሌ ክፍለ ከተማ ያስተዋለቻቸው የመሬት ቅርምቶች እና የነዋሪዎች ቅሬታ ደግሞ ለዚህ ማሳያ ነው።

የከተማ አስተዳደሩ በተደጋጋሚ በሕገ ወጥ መንገድ የተወረሩ እና የተያዙ መሬቶችን ወደ መሬት ባንክ እንደገባ ቢነግርም ግን ቅሉ በተደጋጋሚ አዲስ ማለዳ በተዘዋወረችባቸው አካባቢዎች እና ለዝግጅት ክፍላችን በሚደርሰው ቅሬታ አማካኝነት ሕገ ወጥ የመሬት ወረራው እጅግ ተጠናክሮ መቀጠሉን ማስተዋል ይቻላል። ይህ በሆነበት ሁኔታ ደግሞ ከኹሉም የሚብሰው ደግሞ በአንድ ሰው የተያዘ እና የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታን በሕጋዊ መንገድ የወጣበትን መሬት አንዳንዴም ግንባታም የተጀመረበትን ስፍ በላዩ ላይ በሌላ ሰው ስም ካርታ በማዘጋጀት ያልተለፋበትን ንብረትና መሬት ለመውሰድ የሚደረጉ ሙከራዎችንም እየተስተዋሉ ለመሆኑ ምስክሮች ጥቂቶች አይደሉም።

እነዚህን እና ሌሎች ተጓዳኝ ሕገ ወጥ ወረራዎችን በተመለከተ አዲስ ማለዳ የሚመለከታቸው አካላት በጊዜ ጉዳዩን እልባት እንዲሰጡት እና ይህም ስር ሳይሰድ በአጭር እንዲቀጭ መደረግ እንደሚገባው ታሳስባለች። የመሬት ወረራው ከወረራም ባለፈ እጅግ በተጋነነ ዋጋ ለሦስተኛ ወገን ተላልፈው የከተማውን ማስተር ፕላን ባልጠበቀ መልኩ ግንባታ ሲደርግባቸውም አዲስ ማለዳ ታዝባለች። ይህም ነገ በከተማው አስተዳደር ሕጋዊ አካሔድ መሰረት እንዲፈርስ ወይም ሌላ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው በሚደረግበት ወቅት ሰዎችን ለኪሳራ መነግስትንም ለተጨማሪ ወጪ እንደሚዳርጉ አያጠራጥርም። በመሆኑም እዛ ላይ ሳይደረስ መንግስት ከወዲሁ ጉዳዩን ሳይቃጠል በቅጠል ሊለው ግድ ነው ስትል አዲስ ማለዳ ሀሳቧን ትሰነዝራለች። በተለይም ደግሞ አስቀድሞ አርሶ አደሮች መሬት እንደነበረ የሚነገርላቸው መሬቶች ግን ደግሞ በጊዜው ከስፍራው ሲነሱ ካሳ ተከፍሎበት የተወሰደው መሬት እንደገና በሕገ ወጥ መንገድ እየተያዘ ለተጨማሪ የካሳ ክፍያ መንግስትን ከፍ ሲልም ነዋሪዎችን እንዲከፍሉ እየተደረጉ ለማን አቤት እንደሚሉም የተቸገሩበት ሁኔታ ውስጥ መግባታቸውንም አዲስ ማለዳ ታዝባለች። ይህም ታዲያ ሕዝብን በምሬት እንዲነሳ እና በቁጭት እንዲኖር ከማድረጉም ባለፈ በመንግስት እና በሕግ አስከባሪው አካል ላይ የሚኖረውን አመኔታ እንዲያጣ የሚያደርግ ነው። ስለሆነም የችግሩን ጥልቀት እና አካሔድ ከወዲሁ ተገንዝቦ አፋጣኝ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

በማን አለብኝነት የመሬት ወረራውን የሚያከናውኑ ጥቂት ሰዎችም ተገቢውን ቅጣት ወይም ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስደባቸው እና የተወሰዱት መሬቶችም ወደ መሬት ባንክ እንዲመለሱም አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ይሁን እንጂ በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች በከተማ አስተዳደሩ ዘንድ በሚነገሩ መረጃዎች መሰረት ከፍተኛ የመሬት ቅርምት እንዳለ እና ይህንም ተከትሎ አሁን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣው መመሪያ ቅርምቱን ወደ ሌላ ደረጃ እንዳያሸጋግረው ተፈርቷል።

በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ባንክ ልማት ድርጅት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ እና ሥማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ሰው ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፤ በመንግሥት ደረጃ ተግባራዊ የሆኑ እና ከዚህ ቀደም በወረራ ተይዘው ነገር ግን በተደረገ ዘመቻ ወደ መሬት ባንክ የተመለሱ እንዳሉ ሁሉ በጥቅም ትስስር አሁንም ቁጥራቸው የበዙ መሬቶች መሰብሰብ አልተቻለም።

በተለይም ደግሞ በቅርቡ በጠቅላይ ሚነስትሩ በኩል የተላለፈው እና በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ መሬቶችን የማረስ እና ምርት የማምረት እርምጃ ይህን ነገር ለማባባስ ትልቅ አቅም እንደሚኖረው እና ይህ ወቅት ሲያከትም እና መልካሙ ጊዜ ሲመጣ መንግሥት ተጨማሪ ዙር ካሳ ከፍሎ ሊያስነሳቸው እንደሚችል አልሸሸጉም።

መንግሥትን ለአላስፈላጊ ወጪ ከሚዳርጉት እና የመንግሥትን ዋነኛ ሀብት ከማሟጠጥ ባለፈ ካዝናን ባዶ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች እንደሚሆኑም ኃላፊው ጠቁመዋል። ‹‹መሬት በዋናነት የመንግሥት ትልቁ ሀብት ነው። ይህን ሀብት መንግሥት በአግባቡ የማይጠቀምበት ከሆነ ትልቅ አገራዊ ቀውስ ውስጥ ነው የሚገባው። ምክንያቱም መንግሥት ትልቁ ገቢው ከመሬት የሚገኘው እንደመሆኑ መጠን ያን ገቢውን በአንድም በሌላም ያጣዋል ማለት ነው›› ሲሉ ይገልጻሉ።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በቦሌ ለሚ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪ ይህንን ሐሳብ በሚገባ ይጋሩታል። መንግሥት በሌላ አገራዊ እና ዓለማቀፋዊ ጉዳይ ላይ በተጠመደበት ወቅት ይህን የመሬት ወረራ እየተፈጸመ እና እርሻ እየተካሄደ ባለበት ሁኔታ፣ ቦታውን እንዲለቁ በሚደረግበት ወቅት ድጋሚ ካሳ የሚጠይቁ እና የሚከፈላቸው ከሆነ ብልሹ አሰራሮችን አሁንም መቀረፍ አለመቻላቸው ምልክት እንደሆነ ያስረዳሉ። ይህም ታዲያ ተጨማሪ ወጪን እና ብልሹ አሰራሮችን ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ከማድረግ የበለጠ ምንም አይነት ነገር ባለመኖሩ ከወዲሁ ሀይ ሊባል ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ ትናገራለች።

ከዚህ ቀደም በደህና ሲኖር የተቆየባቸውን አካባቢዎች ነገር ግን የተፈጠረውን ለውጥ እና መንግስታዊ አዲስነትን በመጠቀም የሚደረግ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ከወዲሁ ሳይቃጠል በቅጠል ሊባል ይገባል። ምክንያቱ ደግሞ በአሁኑ የተጀመረው ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዋናነት የሚተውኑባቸው ግለሰቦች ውሎ እና አድሮ ከሕግ እና ከመንግስት ያፈነገጡ ጡንቻቸውን አፈርጥመው ለተጨማሪ አገራዊ ስጋት እና ለሕግ የማይገዙ መሆናቸው የማይቀር ነው። በመሆኑም ይህ አካሔድ ጉዳዩን ወደ ፊት በመውሰድ አገርን ለማፍረስ የማይቻልበት ምንም ምክንያት ባለመኖሩ ይህ ጉዳይ በአፋጣኝ ሊቆም እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ሐሳቧን ትደመድማለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 86 ሠኔ 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here