በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ልዩ ቦታው ጎብቻ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ራሱን ‹የኦሮሞ ነፃ አውጭ ተዋጊ› ብሎ በሚጠራ አካል የቅስቀሳ እና ማስፈራሪያ መልዕክት የያዘ ወረቀት መሰራጨቱን የጉጂ ዞን ፖሊስ መምሪያ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ወረቀቱ የተበተነው የዞኑ ዋና ከተማ ከሆነችው ነገሌ ቦረና ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ ገጠራማ አካባቢ ነው ብሏል። ይሁን እንጂ የአካባቢው ነዋሪዎች ወረቀቱ የተበተነው በከተማዋም ጭምር እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
የቅስቀሳ እና የማስፈራሪያ መልዕክት ያዘለው ወረቀት የተበተነው እና የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ያረጋገጠው ሰኔ 17/2012 ሲሆን፣ ይህም የማስፈራሪያ፣ ቅስቀሳ እና ዛቻ መልዕክቶችን የያዙ ወረቀቶች በአካባቢው መበተኑን ከኅብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ነው። ወረቀቶቹም በአሁኑ ሰዓት በዞኑ ፖሊስ መምሪያ እጅ እንደሚገኙም የጉጂ ዞን ፖሊስ መምሪያ የኮምዩኒኬሽን ዘርፍ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር በቃሉ በለጠ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ለአካባቢው ማኅበረሰብ እንዲደርስ የተበተነው መልዕክት አዘል ወረቀት በኦሮምኛ የተፃፈ እንደሆነ እና ዋና ይዘቱም ኢንስፔክተር በቃሉ ከኦሮሞኛ ወደ አማርኛ ቋንቋ ተርጉመው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ‹‹የፌዴራል መንግሥት የኦሮሞን ሕዝብ ትግል ለማቀጨጭ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚያደርገው ግድያ እና እስር እየባሰ ስለመጣ ከጎኔ እንድትሆኑ›› የሚል ነው።
አዲስ ማለዳ ከአካባቢው ነዋሪዎች ባገኘችው መረጃ መሰረት፣ የደብዳቤው መልዕክት ማስፈራሪያ ጭምር እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል። በአካባቢው እንዲህ አይነት የማስፈራሪያ መልዕክት የያዙ ወረቀቶች በአካባቢው መበተን የጀመሩት ካለፉት ኹለት ሳምንታት ወዲህ መሆኑንም ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች የኦነግ ሽኔ ደጋፊ ናችሁ በሚል ሰበብ ያለ ምንም ጥፋት ለኹለት ወር ያክል እንደታሰሩ የአዲስ ማለዳ ምንጮች አረጋግጠዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በአካባቢው በተደጋጋሚ ሰዎች ተገድለው እንደሚገኙ እና ኃላፊነቱን የሚወስድ አካል አለመኖሩ ደግሞ ጉዳዩን የከፋ እንደሚያደርገው ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ባሳለፍነው ሳምንት በተከታታይ ቀናት ሦስት ሰዎች ሌሊት ላይ በከተማዋ ተገድለው መገኘታቸውንም የዐይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ተሰባስበው በሚኖሩባት በዚህ አካባቢ፣ ኦነግ ሽኔ ጥቃት እያደረሰ እንደሆነ ነው የአካባቢው ነዋሪዎች የሚጠቁሙት። የአካባቢው ነዋሪዎች በተጓዳኝ ወረቀቱ ማስፈራሪያ እና ዛቻ የታከለበት ነው ቢሉም የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ‹‹ማስፈራሪያው ተራ ማስፈራሪያ ከመሆን የዘለለ አይደለም›› ሲል አጣጥሎታል።
በአካባቢው ተሰራጨ የተባለው ወረቀትም ምንም አይነት ማህተም እንደሌለው እና በአካባቢው ሕዝብ ላይ ስጋት ለመፍጠር የተደረገ ሙከራ ነው ሲሉ ኢንስፔክተር በቃሉ ገልጸዋል። የደብዳቤው ባለቤት ‹ኦሮሞ ነፃ አውጭ ተዋጊ› በማለት በተበተነው ወረቀት ላይ እንደተገለጸው እና የደብዳቤው አሰራጭ ‹የደቡብ ዞን 7ኛ ሻለቃ› ተብሎ አድራሻው መገለጹን ኢንስፔክተር በቃሉ ጠቁመዋል።
የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ለአካባቢው ሕዝብ የተበተነው መልዕክት ምንጭ ማን እንደሆነ እስከ አሁን የተደረሰበት ነገር እንደሌለ እና ምንጩን ለማግኘት ወደ ሥራ ለመግባት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ኢንስፔክተር በቃሉ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
ኦንስፔክተር በቃሉ እንደሚሉት፣ ጉዳዮ ከዞኑ ፖሊስ የሚያልፍ እንዳልሆነ እና ከማስፈራራት እና ሕዝቡን ስጋት ውስጥ ከመክተት ውጭ ወደ ተግባር የሚቀየር ጉዳይ አይደለም ሲሉ የነገሩን ክብደት አቃለውታል። ነገር ግን ጉዳዩ የሙከራ ሥራ በመሆኑ በችልታ የሚታለፍ እንዳልሆነ እና አሁን የተሞከረው ሙከራ ነገ እራሱን አሳድጎ እንዳይመጣ ምንጩ ተጣርቶ እንደሚገታ ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ ነዋሪዎች በበኩላቸው በስፍራው የተሰራጨው የማስፈራሪያ መልዕክት የሰዎች ሥም ዝርዝር ያለበት ሲሆን በነገሌ ቦረና ከተማ ማዘጋጃ ቤት ጀርባ መገኘቱንም ጨምረው ገልጸዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 86 ሠኔ 20 2012



