ሜቴክ ሠራተኞቹን ሊቀንስ ነው

0
558

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በሚቀጥሉት ኹለት ወራት ውስጥ ሠራተኞችን ለመቀነስ አዲስ የኮርፖሬሽኑን የአደረጃጀት ሥራ እየሠራ መሆኑ ተገለጸ።
በኮርፖሬሽኑ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ አጠቃላይ ተቋማዊ ለውጥ እያደረግሁ ነው ማለቱን ተከትሎ፣ ያለውን የሰው ኃይል አደረጃጀት እንደ አዲስ ማደራጀት የተቋማዊ ለውጥ አንዱ አካል በመሆኑ፣ ሠራተኞቹን በሚቀጥሉት ኹለት ወራት ውስጥ እንደሚቀንስ መረጃው ደርሷቸዋል።
ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ጊዜ ጠቅላላ ሠራተኞቹን በመመዝገብ ላይ እንደሚገኝ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋል።

ሠራተኞች የሚመዘገቡት እንደ አዲስ ፈተና እንዲፈተኑ እንደሆነ እና የሚቀነሱ ሠራተኞችን እና በሥራቸው ላይ የሚቀጥሉ ሠራተኞችን ለመለየት ያለመ መሆኑንም ሠራተኞቹ ጠቁመዋል።
ሜቴክ ከዚህ በፊት አሉበት የተባሉ ጠቅላላ ችግሮችን በሚፈታ መልኩ ሙሉ በሙሉ የአደረጃጀት ለውጥ ላይ እንደሆነ የገለጹት የድርጅቱ የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ሞላልኝ ከሳቴብርሃን፣ ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ጊዜ ሠራተኞችን እየመዘገበ እንደሆነ ተናግረዋል። የሠራተኛ ድልድል ሥራው ገና በሂደት ላይ እንዳለ የገለጹት ሞላልኝ፣ የሠራተኞች የአደረጃጀት ሥራው ገና በሂደት ላይ በመሆኑ የሚቀነሰው የሠራተኛ መጠን በውል እንዳልታወቀ እና በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ መጨረሻ ውጤቱ እንደሚታወቅ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

ኮርፖሬሽኑ ለዓመታት የነበሩበትን ችግሮች እና ኪሳራዎች በሚቀይር ሁኔታ በአጠቃላይ አዲስ አደረጃጀት፣ አዲስ ቅርጽ እና አዲስ አሰራር በማዘጋጀት ሂደት ላይ እንዳለ እና ወደ አዲስ አሠራር ለመሸጋገር ሰፊ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ሞላልኝ ጠቁመዋል። አክለውም የሠራተኞች አደረጃጀትም የዚሁ አካል መሆኑን እና በአሁኑ ጊዜ የሠራተኞቹን ቅነሳ ማረጋገጥ አይቻልም ሲሉ ተናግረዋል።
የአዲስ ማለዳ ምንጮች የጠቆሙት፣ ኮርፖሬሽኑ እስከ 3000 የሚደርሱ ሠራተኞችን ሊቀንስ እንደሚችል ነው።

ኮርፖሬሽኑ ያዘጋጀው የሠራተኛ ፍላጎት መዋቅር ለዋና መሥሪያ ቤቱ እና በስሩ ላሉ ዘጠኝ ፋብሪካዎች ለእያንዳንዳቸው በተናጠል በዘርፉ ላይ በተሰማሩ የመንግሥት ድርጅቶች የሠራተኛ አደረጃጀት መዋቅር እንዳስጠና ተጠቁሟል። በመንግሥት ድርጅቶች ተጠንቶ የቀረበው አዲሱ የሠራተኛ ምደባ አደረጃጀት ላይ፣ በኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች ቅሬታ እንደቀረበ ሞላልኝ አመላክተዋል።
ለኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር የገባው የቅሬታ ደብዳቤም አዲሱ የኮርፖሬሽኑ የሠራተኛ ፍላጎት መዋቅር የሠራተኛውን ጥቅምና መብት የማያስከብር፣ ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበ፣ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጁን ያልተከተለ እንዲሁም መነሻውና ግቡ ግልጽ ያልሆነ ነው በሚል ትችት እንደቀረበበት ተጠቁሟል።

የሠራተኞቹ ደብዳቤ በተጨማሪም የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች ቀድሞ በነበሩ አመራሮች ስግብግብነት የተበዘበዘ እንዲሁም መጣ በተባለው ለውጥ ተስፋ ያደረገ ቢሆንም አሁን የተዘጋጀው መዋቅር እንዳሳዘናቸው ሠራተኞቹ ገልጸዋል።

የመከላከያ ምርቶችን ከሚያመርቱ ፋብሪካዎች ተለይቶ ዘጠኝ ፋብሪካዎችን በስሩ ይዞ የተደራጀው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ በስሩ ዐስር ሺሕ የሚሆኑ ሠራተኞችን አቅፎ ይዟል። ነገር ግን ኮርፖሬሽኑ አዲስ ያወጣው የሠራተኛ ፍላጎት መዋቅር ብዙዎችን ከሥራ ገበታቸው የሚያፈናቅል ነው የሚል ቅሬታ በሠራተኞች ቀርቦበታል።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ በስሩ ከሚያስዳድራቸው መካከል በማኑፋክቸሪንግ መስክ ከአምስቱ ድርጅቶች፣ ባሳለፍነው በሩብ በጀት ዓመት 41.76 ሚሊዮን ብር ትርፍ በማስመዝገብ አትራፊ ከተባሉ ድርጅቶች የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ከቀዳሚዎቹ ተርታ መሰለፍ ችሏል።

ኮርፖሬሽኑ በ2011 ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ውስጥ ገብቶ እንደነበረ፣ ነገር ግን መንግሥት ልዩ ክትትል በማድረጉና ጠንካራ የቦርድ አመራሮችን መድቦ ተቋሙን ለመታደግ በመንቀሳቀሱ፣ ዘንድሮ ከኪሳራ ለመውጣት ችሏል።

ሜቴክ ከኹለት ዓመታት በፊት በከፍተኛ ብልሹ አሰራርና ኪሳራ ውስጥ የነበረ የመንግሥት የልማት ድርጅት ሲሆን፣ በነበረው ብልሹ አሰራር ከፍተኛ የመንግሥት ሀብት ያለ አግባብ እንደወደመበት በመረጋገጡ አመራሮቹ ፈጽመዋል በተባሉት ብልሹ አሰራር እና ኪሳራ በሕግ ቁጥጥር ስር ውለው ተጠያቂ እንደሆኑበት የሚታወስ ነው።

ሜቴክ ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ እንዳለበት መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚህ ዕዳ ውስጥ 57 ቢሊዮን ብር በዕዳ መያዙ ቀርቶ ወይም ተሰርዞ ወደ ካፒታል እንዲዞርለት ጥያቄ አቅርቦ ውድቅ እንደተደረገበትም ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 86 ሠኔ 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here