ባለፉት ቀናት በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ምክንያት በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የሕዝብ እንቅስቃሴዎች መገታታቸው ተከትሎ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በአርቲስቱ ሞት የተዘጉ መንገዶችን በማስከፈት ላይ መሆኑን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ እንደገለጸው በተለያዩ ቦታዎች ለመደበኛ እንቅስቃሴ ዝግ የሆኑ መንገዶችን ለማስከፈት ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በጋራ በመተባበር ላይ መሆኑን ገልጿል።
ኮሚሽኑ እያከናወነ ባለው የተዘጉ መንገዶችን የማስከፈት እንቅስቃሴ ኅብረተሰቡ እና ወጣቱ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል። በተፈጠረው ችግር በአዲስ አበባ ከተማ እንቅስቃሴዎች ወደ መደበኛ ሁኔታቸው ትናንት አርብ ሠኔ 26/2012 የተመለሱ ሲሆን፣ በዕለቱም በከተማዋ አገልግሎት ሰጪ የሆኑ ተቋማት ክፍት ሆነው ውለዋል።
በአንጻሩ በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች የመደበኛ እንቅስቃሴዎች አሁንም ድረስ ዝግ መሆናቸው ተገልጿል። በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በመዲናዋ አዲስ አበባ ኅብረተሰቡ ያለ ምንም የፀጥታ ስጋት በነፃነት እንድንንቀሳቀስ ጥሪ አቅርቧል። ኮሚሽኑ በከተማዋ አስተማማኝ የፀጥታ ጥበቃ እንደሚያደርግም ገልጿል።
ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012



