የጤና ሚኒስቴር በሰሞኑ እንቅስቃሴ የኮቪድ-19 ስርጭት ሊጨምር እንደሚችል ስጋቱን ገለጸ

0
259

በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሞት ሀዘናቸውን ለመግለጽ ሰሞኑን በወጡ ሰዎች በነበረው ጥንቃቄ የጎደለው እንቅስቃሴ ወደ ፊት በኮቪድ-19 ተጠቂዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ጤና ሚኒስቴር ስጋቱን ገለጸ።
በዚሁ ምክንያት እንቅስቃሴ በመገታቱ የጤና ሚኒስቴር ከዚህ በፊት ሲያከናውነው ከነበረው የኮቪድ-19 የላብራቶሪ ምርምራ በእጅጉ ያነሰ መጠን ያለው ቁጥር መመርመሩን ገልጿል። ባለፉት ሦስት ቀናት ውስጥ ያከናወነው የላብራቶሪ ምርመራ ከዚህ በፊት በአንድ ቀን ሲያከናውነው ከነበረው ቁጥር መብለጥ አልቻለም።
ሰሞኑን በነበረው ጥንቃቄ የጎደለው እንቅስቃሴ ላይ ዋናኛው ወረርሽኙ መከላከያ ዘዴ የሆነው ርቀትን የመጠበቅ እና የአፍ መሸፈኛ ጭንብል መጠቀም በከፍተኛ ሁኔታ መዘንጋታቸውን መታዘብ ተችሏል። በኢትዮጵያ እስከ አሁን ለ258 ሺሕ 390 ሰዎች የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን፣ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 6217 መድረሱን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም አገራት ዳግም በማገርሸት የዓለም ፈታኝ በሽታ መሆኑ አሁንም ቀጥሏል። ስለሆነም መዘናጋት እንደማይገባ እና በጤና ባለሙያዎች የሚመከሩ ምክረ ሐሳቦችን ማከናወን እንደሚገባ የጤና ባለሙያዎች በስፋት እየገለጹ ይገኛል።

ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here