ግሪክ ስኩል ያሉ መምህራን ደሞዝ እንደተቀነሰባቸው ተናገሩ

0
505

በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙት የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የግሪክ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት በውስጥ ከያዛቸው ሰራተኞች ውስጥ የመምህራን ደሞዝ ላይ ብቻ ቅናሽ ማድረጉ ተገለጸ፡፡
መምህራኖቹ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ትምህርት ቤቱ ይህንን የደሞዝ ቅናሽ ያደረገበት ምክንያት ደጋግመን ብንጠይቅም ምንም አይነት መላሽ ሊሰጠን አልቻለም ሲሉ ተናግረዋል።
በትምህርት ቤቱ ቅጥር ውስጥ ካሉት ሰራተኞች መካከል መምህራን ብቻ 200 ያህል እንደሆኑ መምህራኑ ለአዲስ ማለዳ የገለጹ ሲሆን፤ ለምን ተቀነሰብን ብለን ቅሬታ ብናቀርብም ስራ ላይ ባለመሆናቸሁ ምክንያት ነው ብለው መልስ እንደሚመልሱላቸውም ተናግረዋል። ውሳኔውም ሲወሰን እንዳላወያዩአቸው እና ውሳኔውንም ሳያሳውቋቸው ደሞዛቸው በባንክ ሲገባ ማወቃቸውን አስረድተዋል።
ከዛም በተጨማሪ ለምን ተቀነሰ ብለን በመጠየቃችን ምክንያት ማስፈራራት እና እንደውም ሙሉ ደሞዛችሁን ልታጡት ትችላላቹ ሁኔታው በዚሁም ከቀጠለ ስራችሁንም ልታጡት ትችላላችሁ እያሉ እንደሚመልሷቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ከዛም በተጨማሪ የተማሪዎቹ ወላጆች ሙሉ የወር ክፍያ እየከፈሏቸው እንደሆነ እና ተማሪዎቹም ይህን በመደረጉ ምክንያት ትምህርታቸው በኦንላይን ተከታትለው የመጨረሻ እና የአመቱን ማጠቃለያ ፈተና እንዲፈተኑ ተደርጎ ሰርተፍኬት እንደተዘጋጀላቸው መምህራኖቹ ገልፀዋል።
ነገር ግን ትምህርት ቤቱ ምንም አይነት የገቢ እጥረት ሳያጋጥመው አጋጣሚውን በመጠቀም ደሞዝ ላለመክፈል እና ለመቀነስ እየጣሩ መሆኑን እየታዘብን ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ኮሮና ከገባ ወደ አራተኛ ወር እየሄደ መሆኑን ተናግረው ነገር ግን ሦስት ወሩን ሙሉ እየከፈሉ ነበር ብለዋል።አኛ እንደምናውቀው ገቢ ማጣት ሳይኖር ካለ አግባብ የአስተማሪዎችን ብቻ ለመቀነስ ለምን እንደተፈለገ ግልጽ አይደለም ሲሉ መምህራኖቹ ይገልፃሉ።
ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ያነጋገርናቸው የግሪክ ስኩል ስራ አስኪያጅ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ከሆነ የደሞዝ ቅናሽ እንዳልተደረገባቸው እና ነገር ግን የትምህርት ቤቱ ገቢ በመቀነሱ ምክንያት ጥቅማጥቅም እንዲቀነስባቸው መደረጉን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት ከሆነ ይህ የሆነበት ምክንያት አስተማሪዎቹ አብዛኛዎቹ እቤት መሆናቸውን እና ስራ ገብተው ስለማያውቁ ከዚህ አንፃር ጥቅማ ጥቅሙ ቢቀር ጉዳቱ አሁን እየተመላለሱ እየሰሩ ካሉት እረፍት ላይ የሆኑት ይሻላል በማለት እንደሆነ ተናግረዋል።
ወሰን እንደሚሉት እርሳቸው ስራ አስኪያጅ ሆነው ከመጡ 5 አመት ሆናቸው ሲሆን አሁን እንዳለው የትምህርት ቤቱ ገቢ ወርዶ አያውቅም ብለዋል። ከዛም በተጨማሪ ወላጆችም ቢሆን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የትምህርት ቤት ክፍያውን ከፍለው እንደማያውቁ እና ትምህርት ቤቱ ያለውን ጊዜ በማገናዘብ በትብብር እየቀጠሉ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዛም በተጨማሪ ከደሞዝ ቅነሳ ጋር በሚነሳው ምንም አይነት ነገር ካለ ውይይት አልተደረገም የሚሉት ወሰን ይሄም ከመደረጉ በፊት የትምህርት ቤቱ ገቢ እንደቀነሰ እና ከአቅም በላይ እየከፋለቸው መሆኑን ተነግሯቸው ነበር ብለዋል።
ወሰን ጨምረውም አሁን ላይ ጥቂት የሚባሉ ሰራተኞች ፅዳት ሰራተኞችን ጨምሮ በስራ ገበታቸው ላይ እንደሚገኙ ተናግረው የእነርሱ እንቅስቃሴ እያደረጉ በመሆናቸው ምክንያት ጥቅማ ጥቅሙ አለመቀነሱን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
እንደ ወሰን ገለጻ ትምህርት ቤቱ ለሰራተኞቹ ከደሞዛቸው በተጫመሪ እንደ ጥቅማ ጥቅም ያስቀመጠው ጭማሪ ክፍያ የመጓጓዣ እና መሰል ወጪዎችን እንዲሸፍኑ የሚያደርግ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። ይህም ምምህራን በቤታቸው ሆነው የወረርሽኙን ጊዜ እያሳለፉ ስለሚገኙ ወደ ትምህረት ቤት ካለመምጣታቸው ጋር ተያይዞ ጥቅማ ጥቅሙ መቅረቱንም ወሰን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here