ኦ ኤም ኤን የኢትዮጵያ ስቱዲዮ ሙሉ በሙሉ ተዘጋ

0
555

የኢትዮጲያ ብሮድካስት ባለስልጣን የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ የቴሌቪዥን ጣቢያን ኢትዮጵያ ስቱዲዮ ሙሉ በሙሉ መዝጋቱን አስታወቀ። ባለስልጣኑ በኹለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይም ከባድ ማስጠንቀቂያ አስተላልፏል።

ባለስልጣኑ ውስጥ አዲስ ማለዳ ምንጮች እንዳስታወቁት በኢትዮጵያ ያለውን የኦ ኤም ኤን ስቱዲዮ ቢዘጋም ቀጥታ ፕሮግራሙ በሳተላይት ከሚተላለፍበት ቦታ ከአሜሪካ ሜኒሶታ ግዛት ለማቋረጥ ከፍተኛ አቅም የሚጠይቅ እንደመሆኑ ያንን ማድረግ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡
ከኦ ኤም ኤን የቴሌቪዥን ጣቢያን ከመዝጋት ባለፈም በአስራት ቴሌቪዥን እና በድምጸ ወያነ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ደግሞ ባለስልጣኑ እያስተጋቡ ያለው ተገቢ ያልሆኑ መረጃዎችን እንዲያስተካክሉ ግን ካልሆነ እስከ መዝጋት የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው የሚገልጽ ከባድ ማስጠንቀቂያ እንደተላለፈባቸውም ከምንጮች የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ከዛም በተጨማሪ (OMN) ዋናው ጣቢያው አሜሪካ ስለሆነ በሳተላይት ማስተላለፉን የቀጠለ ቢሆንም ከዚህ ግን እርምጃ ተወስዶበታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የተቀሩት ሁለቱ ጣቢያዎች ላይ ግን ማስጠንቀቂ እንደተሰጣቸው ነው ተገለጸው፡፡
እንደሚታወቀው መንግስት የጥላቻንን ንግግሮችን እና አርስ በእርስ የሚያጋጩ ንግግሮችን የሚያስተላልፉ ሚዲያዎች ላይ እርምጃ እወስዳለው ብሎ በተናገረው መሰረት ሶስቱ ጣቢያዎች OMN ላይ በሃገር ውስጥ ለውን ስርጭት በማቋረጥ እና , DW ,ASRAT ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ የጸደቀውን የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት እና የጥላቻ ንግግር አዋጅን በተመለከተ ተግባራዊ የሆነው ሕግ በሦስቱ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ክልከላን እንደሚጥል ከብሮድካስት ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የጀዋር መሐመድ ንብረት የሆነው እና ከጅማሬው ጀምሮ ጃዋር መሐመድ ወደ ፖለቲካ ፊታቸውን አዙረው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲን እስከተቀላቀሉበት ድረስ በዋና ስራ አስኪያጅነት ሲመሩት መቆየታቸው ይታወሳል።
የቴሌቪዥን ጣቢያውን መዘጋት እና በቀሪዎቹ ኹለት ጣቢያዎች ላይ ደግሞ የተላለፈውን ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ በተመለከተ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋዜጠኝነት እና ተግባቦት አስተማሪ ሆኑት ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት ዶክተር ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፤ ‹‹መንግስት እርምጃ መውሰድ ከነበረበት ጊዜ እጅግ ዘግይቷል።›› ሲሉ ይጀምራሉ።
አያይዘውም በመንግስት እና በሚዲያ ዘንድ ያለውን ርቀት እና ነጻነት በአንጻሩም ቢሆን ቢደግፉም ነገር ግን በነጻነት ሰበብ ጽንፈኝነትን የሚሰብኩ እና አንድን ብሔር በአደባባይ በመዝለፍ እና በሌላው ብሔር ላይ በማነሳሳት መርሃ ግብራቸውን ሲያሰራጩ መታዘብ ግን ከመንግስት ወገን በአፋጣኝ እርምጃ መውሰድ የሚገባ ተግባር እንደነበር ይጠቁማሉ።
‹‹ምናልባትም እስካሁን የተፈጠሩት ችግሮች በአንጭጩ በቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ ቢወሰዱ ኖሮ ይህ ያህል ጉዳት ላይደርስም ይችል እንደነበር መገመት ይቻላል›› ሲሉ ይናገራሉ። አስተያየት ሰጪው እንደሚናገሩት አሁንም ቢሆን በውጭም ሆነው የጥላቻ ንግግራቸውን መንዛታቸው እንደማይቀር እና መንግስት እስከ መጨረሻው ድረስ ተከታትሎ መዝጋት እንደሚኖርበትም አሳስበዋል።
ሕዝብን ከሕዝብ ጋር በሚጋጩ እና ሀሰተኛ መረጃዎችን ያሰራጫሉ በተባሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የተጠቀሰ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ተጠቃሽ ሆነው አስራት ቴሌቪዥን ከማስጠንቀቂያው ኹለት እና ከዛ በላይ ሳምንታትን አስቀድሞ አገልግሎት መስጠት ያቆመ ሲሆን ማስጠንቀቂያውም የደረሰው በሌሎች ምክንያቶች አየር ላይ ከጠፋ ከሳምንታት በኋላ መሆኑን የጣቢያው ጋዜጠኞች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ሰራተኞች ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት በአጭር ቀናት ውስጥ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ወደ ስራ እንደሚመለስ እና በብሮድካስት ባለስልጣን በኩል የተላለፈው ማስጠንቀቂያም እኛን እንደጋዜጠኛ አይወክለንም ሲሉም ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here